የጣና ሐይቅ እና የተደቀኑበት ችግሮች
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13 2011የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ስራና የፍሳሽ ማስወገድ ተግባራት ያለማቋረጥ ሊሰራ እነደሚገባ ደግሞ የአማራ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን አሳስቧል፡፡ የፌደራል መንግስት ባለድርሻ አካላትም ከሐይቁ ከመጠቀም ውጪ ለሐይቁ ህልውና የሚያደርጉት ድጋፍ የለም ተብሏል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ተንሳፋፊ የእምቦጭ አረም የጣና ሐይቅን በስፋ በመውረሩ የሐይቁ ህልውና ጥያቄ ላይ ወድቋል፡፡ አረሙን ለማጥፋት እየተሰራ ነው ቢባልም የቅንጅትና የቁርጠኝነት እጦት በሐይቁ ላይ የደቀነው ሁሉ አቀፍ ችግር ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የሐይቁን ህልውና የሚፈታተኑ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች እተበራከቱ መጥተዋል፡፡
በስነምህዳርና ብዝሓይወት ዙሪያ ተመራማሪ የሆኑት እና በጣና ሐይቅ ህልውና ዙሪያም በርካታ የምርምር ሥራዎች ያካሄዱት ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ደለልና የፍሳሽ ቆሻሻ ተፈጥሯዊ የሆነውን የጣና ሐይቅ እየበከለ፣ እንዲሁም፣ ወንዞች ከእርሻ ማሳ ይዘውት የሚመጡት ማዳበሪያ አዘል ደለል በሐይቄ ላይ ሄቪ ሜታል ስለሚፈጥሩ በሰዎች ላይ የጤና ችግር፤ አጠቃላይ በሀይቁ ብዛ ሕይወት ላይ ደግሞ ጥፋት እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ስነ ምህዳር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘው ተቋማቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የአካባቢ ችግርን በሚፈታ መልኩ መሰራታቸውን መቆጣጠር መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ ከፍተኛ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ፍሳሽ ወደ ሐይቁ በሚለቁ አካላት ላይ ደግሞ ርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ገልጸዋል። ጣናን ለማዳን የአንድ ወገን ጥረት ውጤት አያመጣም ያሉት አቶ መዝገቡ በተላይ የሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ተሳትፎ የለም ነው ያሉት፡፡
ዓለምነው መኮንን
አርያም ተክሌ