1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችየመካከለኛው ምሥራቅ

የጤና ዕክል ላለባቸው የጋዛ ነዋሪዎች ሕይወት አስቸጋሪ ሆኗል

03:35

This browser does not support the video element.

ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2016

ጦርነት ከበረታበት ሰሜናዊ ጋዛ ወደ ደቡብ የሸሹ ፍልስጤማውያን ፋታ አላገኙም። የኤሌክትሪክ እና የሕክምና ግብዓቶች እጦት የጤና ዕክል ያለባቸው የጋዛ ነዋሪዎችን ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎታል።

ከጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ከተፈናቀሉ ወዲህ ሐና አቡ ዛይድ ኑሯቸው በደቡባዊ ጋዛ ኻን ዩኒስ በድንኳን ውስጥ ሆኗል። የ55 ዓመቷ ወይዘሮ ለረዥም ዓመታት የሚያማቸው አስምን ጨምሮ የጤና ችግር አለባቸው። በየቀኑ አተነፋፈሳቸውን የሚያግዛቸውን መሣሪያ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል። 

ሐና አብዱ ዛይድ ኃይለኛ የትንፋሽ እጥረት አለባቸው። ሕይወታቸው ለአተነፋፈስ በሚያግዛቸው መሣሪያ ላይ ጥገኛ ነው። የሚኖሩበት ድንኳን ሞቃታማ እና እርጥበታማ በመሆኑ “ማታ መተኛት አልችልም። ጎረቤቶቼ ለማብሰል እጨት ባያያዙ ቁጥር አተነፋፈሴ ይረበሻል” ሲሉ የገጠማቸውን ፈተና ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም በተባበሩት መንግሥታት በኩል በየወሩ በነበራቸው ቀጠሮ ሕክምና ያገኙ የነበረ ቢሆንም ጦርነት ተቀስቅሶ ሲፈናቀሉ ተቋርጧል። 

የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያው እጅግ የተፋፈገ ነው። በቦታው 27 ሺሕ ሰዎች ይኖራሉ። በቂ የሕክምና ተቋማት እና ኤሌክትሪክ ባለመኖሩ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ሐና በየቀኑ ለበርካታ ጊዜያት የአተነፋፈስ ዕገዛ ለሚያደርገው መሣሪያ ኤሌክሪክ ፍለጋ በእግራቸው ይጓዛሉ። “ባትሪው በቂ ኃይል ከሌለው ሔጄ ቻርጅ ማድረግ ይኖርብኛል” የሚሉት ሐና ግማሽ ኪሎ ሜትር ለመጓዝ “ሁለት እርምጃ በተራመድኩ ቁጥር ቆሜ ማረፍ አለብኝ” ሲሉ ተናግረዋል። “ለአተነፋፈሴ የሚያግዘኝን መሣሪያ በቀን ቢያስን አስር ጊዜ መጠቀም አለብኝ። ለኔ በጣም ሩቅ ነው። በጣም ደክሞኛል። ኤሌክትሪክ ያስፈልገኛል። እርዳታ እፈልጋለሁ” ሲሉ ይማጸናሉ። 

በመጠለያው ውስጥ የጤና ማዕከል ቢኖርም ሕሙማኑ የሚፈልጉትን ዕገዛ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም የለውም። ነገር ግን በማዕከሉ የሚገኙ ዶክተሮች እና የሕክምና ባለሙያዎች ባላቸው አቅም ለሕሙማኑ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ይጥራሉ። 

“በአካባቢ እና የውኃ ብክለት እንዲሁም በኢንፌክሽን ምክንያት በርካታ ሕሙማን እንቀበላለን” የሚሉት የሕክምና ባለሙያው ባካም ዛካውት በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ሐና እንደሌሎች የታመሙ ተናቃዮች ሁሉ በድንኳኑ ውስጥ ኤሌክትሪክ አገኛለሁ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። አተነፋፈሳቸውን የሚያግዛቸውን መሣሪያ የሚያስፈልገውን ኤሌክትሪክ ማግኘት በሕይወት የመቆየት ትግላቸው አንድ አካል ነው። 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW