የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ
እሑድ፣ ጥር 11 2017
ጥምቀት የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ዓርአያ ለመሆን እና የሰው ልጆችን የሃጥያት ዕዳ ለማጥፋት በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ የሚከበርበት ሲሆን፣ ጥምቀት ለሰው ልጆች ደግሞ "ልጅነትን" የሚያገኙበት ስለመሆኑ በቤተ ክርስትያን የታመነ ነው። ኢትዮጵያ የምታከብረው የጥምቀት ክብረ በዓል ሺህ ዓመታትን የዘለቀ ሲሆን በሥርዓቱ ላይ ለፈጣሪ የሚቀርበው ሕብር ዝማሬው፣ መወድሱ፣ ምስጋናው፣ ጣዕመ ዝማሬው፣ የልዩ ልዩ አልባሳቱ ተውህቦ፣ በዓሉ ድንቅ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በመንግሥታቱ ድርጅት በ2012 ኮሎምቢያ ላይ እንዲመዘገብ አድርጎታል።
መጋቢ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ በቤተ ክርስትያኗ የአብያተ ክርስትያናት ታሪክ ተመራማሪ እና የሥራ ኃላፊ ናቸው። "ጥምቀት የሃይማኖት በዓል ነው" የሚሉት እኒሁ ሰው ለባህል ዕድገት ግን "አስተዋጽዖ አበርክቷል ይላሉ።
ጥምቀት በኢኮኖሚ ፣ በማህበራዊ ዘርፎችና በገጽታ ግንባታም ከፍተኛ ዋጋ ያለው በመሆኑ "መንግሥታዊ ጥበቃም ያለው" ስለመሆኑ ይገልፃሉ። የአምልኮ ሥርዓቱም እየደመቀ እየሠፋ የሄደ፣ ቤተ ክርስትያኗም "ታላቅነቷን፣ እምነቷን፣ ባህሏን፣ ሥርዓቷን የምትገልጽበት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው ብለዋል።
የ 83 ዓመቱ የበዓሉ ታዳሚ አቶ ተስፋዬ ተክሉ በበዓሉ ተደስተዋል። ግን ስለሀገር ሰላም መቀራረብ ቢኖር ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብዑዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት ምድር ያላትን ሀብት "ለጦርነትና እልቂት ከምናውለው ለልማት ብናውለው ችግር እና እጦት በጠፋ ነበር" ብለዋል ።
በክብረ በዓሉ ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጎብኝዎችም ታድመዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ