1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥምቀት በዓል አከባበር በአዳማ

ቅዳሜ፣ ጥር 11 2016

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው አዳማ ከተማ የጥምቀት በዓል ዛሬ በደማቁ ተከብሮ ውሏል። የዶይቼ ቬለው ሥዩም ጌቱ የኃይማኖት አባቶች እና ምዕምናን በማነጋገር የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

የጥምቀት በዓል በአዳማ ከተማ
የጥምቀት በዓል በአዳማ ከተማ በርካታ ምዕምናን በተገኙበት ተከብሯልምስል Seyoum Getu/DW

የጥምቀት በዓል አከባበር በአዳማ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በደማቁ በመላው አገሪቱ የሚከበረው ይህ የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን በመታሰቢያነት በመያዝም ነው፡፡

በበዓሉ አከባበር ወቅት የሃይማኖት አባቶች ለምዕመናቱ ባስተላለፉት መልእክት ስለ ሰላምና አንድነት አጉልተው አስተጋብተዋል፡፡

“የጥምቀት በዓል አከባበር መነሻው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ከጌሊላ ተነስቶ ወደ ባህረ ዮርዳኖስ በመጠመቅ እንድንጠመቅ ባዘዘን መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓቱን ሳታጎድል ምዕመኗም እንደምንመለከተው በጉጉት የሚጠመቁበት ክብረ በዓል ነው” ሲሉ መጋቢ አዲስ አባ ገ/ጻዲቅ መኮንን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የከተራ በዓል በአዳማ ከተማ

“ይህ በዓል አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንጡራ ሃብት ከመሆንም አልፎ የዓለም ቅርስ የሆነ ትልቅ ክብረ በዓል ነው” በማለት ስለ በዓሉ አከባበር ለዶይቼ ቬለ ያብራሩት መጋቢ አዲስ አባ ገ/ጻዲቅ መኮንን የምስራቅ ሸዋ አገረ ስብከት ወንጌል ክፍል ኃላፊና የአደባባይ በዓላት ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡

በአዳማ ከተማ የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሯልምስል Seyoum Getu/DW

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ የተጠመቀበትን እለት በማስታወስ በደማቅ ስነስርዓት የምታከብረው ይህ በዓል በሃይማኖቱ ተከታዮች ትልቅ በረከት የሚገኝበት በሚል ይታመናልም፡፡ ዛሬ በአዳማ የተከበረው ይህ ዓመታዊ ክብረ በዓል ቁጥራቸው እጅግ የበዛ የሃይማኖቱ ተከታዮች በተገኙበት እና በደመቀ ስርዓት ነው፡፡

በበዓሉ መታደምና ሃይማኖታዊ አንድምታው

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የእምነቱ ተከታዮች ሃማኖታዊ ትርጉሙ “እጅግ የላቀ” ያሉት ይህ ክብረ በዓል ሃሴት እንደምሰጥም ነው የገለጹት፡፡ “በሃይማኖታችን ይህ በዓል ሲከበር አምላካችን ከሰማይ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማሪያም ተወልዶ የተነጠቅነውን ልጅነታችን ልመልስ የእዳ ደብዳቤያችንን በዮርዳኖስ በመጠመቅ የቀደደበት በመሆኑ በጥልቅ ደስታ የምናከብረው ነው” ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ የጥምቀት በዓል የአንድነትና በፍቅር የመሰባሰብ ሲሉም ገልጸውታል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የጥምቀት በዓል ሲከበር በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ተገኝተዋል። ምስል Seyoum Getu/DW

ጥምቀት እና አንድነት-ሰላም

 አስተያየት ሰጪ ምዕመናኑ በዓሉን በሚያከብሩበት ወቅት በተለያዩ የጸጥታ ችግር ውስጥ ሆነው እያሳለፉ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ማስታወስም ተገቢነቱ የጎላ ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ “የምናየው አንድነት ደስ ይላል፡፡ ሰላምን የሚያመጣልንም መስላል፡፡ በዚህን ወቅት እንደኛ በኣሉን በደስታ ማሳለፍ እየፈለጉ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ይኖራሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላሟን እንድመልስ ነው ልመናችን” ብለዋል።

የከተራ በዓል በአዲስ አበባ

የምስራቅ ሸዋ አገረ ስብከት ወንጌል ክፍል ኃላፊና የአደባባይ በዓላት ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢው መጋቢ አዲስ አባ ገ/ጻዲቅ መኮንንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስለ ሰላም እና አንድነት መስበክ የሰርክ ተግባሯ ነው ብለዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስለሰላም፣ ስለእርቅ፣ የተራቡትን ስለማብላት፣ የታረዙትን ስለማልበስ ትሰብካለች” ያሉት የሃይማኖት አባቱ በተለይም ስለሰላም ማስተማርና መጸለይ የቤተክርስቲንቱ የሁል ጊዜውም ስራ ነው ሲሉ ገልጸውልናል፡፡

በአዳማ ከተማ ሶስት የስርዓተ ጥምቀት መከወኛ ቦታዎች ስኖሩት 21 ታቦታት የሚሰባሰቡበትና በዓሉ እጅጉን የሚደምቅበት አዳማ መስቀል አደባባይ እጅጉን በህዝብ ተጨናንቆ ነበር፡፡ በዓሉ ሰላማዊና የእምነቱ ተከታዮች መረጋጋት የታየበትም ነው።

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW