1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥምቀት በዓል አከባበር በአዲስ አበባ

ሐሙስ፣ ጥር 11 2015

በጃን ሜዳው ክብረ በዓል መጠናቀቂያ ወቅት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ አብርሃም በተወካያቸው በኩል "ፖለቲከኞች ወደ ቤተ ክርስትያን ስትመጡ የፖለቲካ ካባችሁን አውልቃችሁ የቤተ ክርስትያንን ካባ ለብሳችሁ መገልገል ትችላላችሁ" የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

 Addis Ababa Timket Celebration
ምስል Solomon Muchie/DW

ፖለቲከኞች ቤተ-ክርስቲያን ለፖለቲካ እንዳይጠቀሙ ተጠየቁ

This browser does not support the audio element.

የጥምቀት በዓል አዲስ አበባ ጃንሜዳ ላይ በሚዘጋጀው ጥምቀተ ባሕር በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ ውሏል። በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያንና የሐገሪቱ መንግሥት ተወካዮች የፍቅር፣ የአንድነትና የሰላም መልእክቶችን አስተላልፈዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ከትናንት ከከተራው እለት ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫ በበዓሉ ድባብ ከፍተኛ ድምቀት ውስጥ ትገኛለች። 

በጃን ሜዳው ክብረ በዓል መጠናቀቂያ ወቅት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ አብርሃም በተወካያቸው በኩል "ፖለቲከኞች ወደ ቤተ ክርስትያን ስትመጡ የፖለቲካ ካባችሁን አውልቃችሁ የቤተ ክርስትያንን ካባ ለብሳችሁ መገልገል ትችላላችሁ" የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ከትናንት ከከተራው እለት ጀምሮ ደምቃለች። አደባባይና ጎዳናዎቿ ተውበዋል። የጥምቀተ ባህሩ የተከተረበት ጃንሜዳ በምእመናን ተሞልቶ ከንጋቱ ጀምሮ በመንፈሳዊ ዝማሬዎች፣ በወረብና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች አገልግሎት ተውቦ፣ በውጭ ዜጎች ታጅቦ ተከብራል።
ለበዓሉ ማማር ፀጥታ በመጠበቅም ይሁን መድረኩን በማሳመር ምስጋና የቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሆን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት በሕብረት እንቁም የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ጥምቀትንም ሆነ ሌሎችን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶችን ለመጠበቅ በብርቱ እየተሠራ ነው በማለት የባህልና ስፓርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ተናግረዋል።
ለሕዝበ ክርስትያኑ ቃለ ቡራኬ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁእ አቡነ ማትያስ "ሕዝባችን ክፉኛ ተጎድቷል"ና በፍትሕ እና እኩልነት መልሰን ልንገነባው ይገባል በማለት ሕዝብ ለመልካም ነገር ሁሉ እንዳይሰንፍ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም ቤተ ክርስትያን ላይ የሚደርሰውን ማዋከብ አስመልክተው በተወካያቸው ተከታዩን መልእክት አስተላልፈዋል።
"ፖለቲከኞች ወደ ቤተ ክርስትያን ስትመጡ የፖለቲካ ካባችሁን አውልቃችሁ የቤተ ክርስትያንን ካባ ለብሳችሁ መገልገል ትችላላችሁ። የቤተ ክርስትያን ቆይታችሁን አጠናቃችሁ ስትመለሱ ደግሞ የቤተ ክርስትያንን ካባ አውልቃችሁ የፖለቲካ ካባችሁን ለብሳችሁ መሄድ ትችላላችሁ። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቤተ ክርስትያን የፖለቲካ መታገያ መሠረታችን ናት ይላሉ። ይህንን ሲገልጹ ፍፁም ስህተት እና ነውር ነው። ቤተ ክርስትያናችን የማንም የፖለቲካ ማራመጃ መሠረት አይደለችም"
በአዲስ አበባ ከመንበረ ክብራቸው ወደየ ጥምቀተ ባህር ወጥተው የነበሩ 80 ታቦታት ወደ ማደሪያቸው ተመልሰዋል፣ ነገም የሚመለሱ ይኖራሉ። በዓሉ በሰላም ተከብሮ ተጠናቋል።

የጥምቀት በዓል አከባበር በአዲስ አበባ-ጃን ሜዳምስል Solomon Muchie/DW
የጥምቀት በዓል አከባበር በአዲስ አበባ-ጃን ሜዳምስል Solomon Muchie/DW

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW