የጥር 12 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥር 12 2017ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዩናይትድ ስቴትስ ሒውስተን ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር በወንዶችም በሴቶችም አሸንፈዋል ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። በማራቶንም ድል ቀንቷቸዋል ። ፉክክሩ በተጧጧፈበት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው መሪው ሊቨርፑል ተከታዩ አርሰናልን በስድስት ነጥብ ርቆታል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባዬርን ሌቨርኩሰን ባዬርን ሙይንሽንን እግር በእግር እየተከተለ ነው ። በዘንድሮ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ለሰባት ጊዜያት የዓለም ባለድል በሆነበት ሜርሴዲስ ሳይሆን በሌላ ተሽከርካሪ ብቅ ብሎ ደጋፊዎቹን አስደምሟል ።
አትሌቲክስ
ዩናይትድ ስቴትስ ሒውስተን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር በወንድም በሴትም ኢትዮጵያ አሸነፈች ። በወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያው አትሌት አዲሱ ጎበና 59 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ወጥቷል ። አሜሪካዊው አትሌት ኮነር ማንትዝ ከአዲሱ እግር በእግር ተከትሎ በመግባት እንዲሁም ታንዛኒያዊው ሯጭ ጋብሪኤል ጊዬይ በአንድ ሰከንድ ብቻ ልዩነት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። 59 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ሩጦ አራተኛ ደረጃ ያገኘውም ኢትዮጵያዊው አትሌት ጀማል ይመር ነው ። አራቱም ሯጮች ከአንድ ሰአት በታች ባጠናቀቁበት የግማሽ ማራቶን ሩጫ በሰከንዶች ልዩነት ብቻ መበላለጥ የታየበት ፉክክር እጅግ ከፍተኛ ነበር ።
በሴቶች ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሠናይት ጌታቸው (01:06:05) በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ቡዜ ድሪባ አሜሪካዊቷ ዋይኒ ኬላቲን በመከተል የሦስተኛ ደረጃ (01:06:48)አግኝታለች ። በዋይኒ የተቀደመችው በ39 ሰከንዶች ነው ። በሒውስተን የ42 ኪሎ ሜትር ማራቶን ሩጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቁመሺ ሲጫላ (02:20:42)በመሮጥ አንደኛ ደረጃ አግኝታለች ። አሜሪካዊቷ ኤሪካ ኬምፕን በመከተል ኢትዮጵያውያቱ ትእግስት ኃይለሥላሴ (02:25:09)እና ሐና ዲባባ (02:26:49)የሦስተኛ እና የአራተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። የጥር 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በወንዶች የማራቶን ፉክክር፦ ኤርትራዊው አትሌት የማነ ኃይለሥላሴ በእስራኤላዊው ሯጭ አይምሮ ዓለሜ በ8 ሰከንዶች ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ወጥቷል ። የገባበትም ጊዜ 2 ሰአት ከ8 ደቂቃከ25 ሰከንድ ሁኖ ተመዝግቧል ። በዚሁ የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊው አትሌት አሠፋ ተፈራ በስድስተኛ ደረጃ (02:09:52)አጠናቋል ። አምስተኛ የወጣው ሌላኛው የኤርትራ ሯጭ ፊልሞን አንዴ (02:08:59)ነው ።
እግር ኳስ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ማንቸስተር ሲቲ ትናትን ወራጅ ቀጣናው ውስጥ የሚገኘው ኢፕስዊች ታውንን በሜዳው 6 ለ0 ጉድ አድርጎታል ። ለማንቸስተር ሲቲ ፊል ፎደን ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል ። ማቴዎ ኮቫቺች፤ ጄሬሚ ዶኩ፣ ኧርሊንግ ኦላንድ እና ጄምስ ማክአቲ አንድ አንድ ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል ። 38 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ሲቲ በኖቲንግሀም ፎረስት በስድስት ነጥብ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ኖቲንግሀም ፎረስት ትናንት ሳውዝሐምፕተንን 3 ለ2 አሸንፏል ።
በ44 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ከአስቶን ቪላ ጋር ሁለት እኩል ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ከመሪው ሊቨርፑልም በስድስት ነጥብ ይበለጣል ። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ብሬንትፎርድን በገዛ ሜዳው 2 ለ0 አሸንፏል ። የታኅሣሥ 28 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ፕሬሚየር ሊግ
26 ነጥብ ሰብስቦ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት በገዛ ሜዳው ኦልድ ትራፎርድ በብራይተን የ3 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ከባዶ ከመሸነፍ ያተረፈችውን ግብ ያስቆጠረው ብሩኖ ፈርናንዴሽ ነው ። ኤቨርተን ቶትንሀምን 3 ለ2፤ ፉልሀም ላይስተር ሲቲን 2 ለ0 አሸንፈዋል ። እንደ ቸልሲ 38 ነጥብ ሰብስቦ በግብ ክፍያ ልዩነት አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኒውካስል ሴይንት ጄምስ ፓርክ ስታዲየም አቅንቶ በበርመስ የ4 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ክሪስታል ፓላስ ዌስትሐም ዩናይትድን 2 ለ0 ድል አድርጓል ። በ37 ነጥቡ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን ከዎልቭስ ጋር ያደርጋል ። ቸልሲ ካሸነፈ የማንቸስተር ሲቲ አራተኛ ደረጃን ይረከባል ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ቮልፍስቡርግን 3 ለ2 አሸንፎ ነጥቡን 45 አድርሷል ። ቅዳሜ ዕለት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ1 ድል ያደረገው ተከታዩ ባዬርን ሌቨርኩሰን 41 ነጥብ አለው ። በ36 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው አይንትራኅት ፍራንክፉርት ዶርትሙንድን 2 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 36 አድርሷል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ25 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ እና ከበላዩ የሰፈረው ሽቱትጋርት ልዩነታቸው የ1 ነጥብ ብቻ ነው ። ፍራይቡርግን ቅዳሜ ዕለት 4 ለ0 ድባቅ የመታው ሽቱትጋርት 32 ነጥብ አለው ። አትሌቲክስ ስፖርት እና የእግር ኳስ ዘገባዎች
የመኪና ሽቅድምድም
ብሪታኒያዊው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ተፎካካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በዘንድሮ የ2025 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ውድድሩን አሸነፈ ። በማርሴዲስ አሽከርካሪነቱ ለበርካታ ዓመታት በድል የሚታወቀው ሌዊስ ዘንድሮ ፉክክሩን የጀመረው በፌራሪ ተሽከርካሪ ነው ። በመርሴዲስ ለሰባት ጊዜያት የዓለማችን ሻምፒዮና በመሆን ዋንጫዎችን የሰበሰበው ሌዊስ የዘንድሮ የውድድር ዘመኑን በፌራሪ ለመዝለቅ በድል ሀ ብሎ ጀምሯል ። የ40 ዓመቱ ሐሚልተን ከቀይ የፌራሪ F40 አጠገብ ቆሞ የተነሳው ፎቶግራፍ በርካታ አድናቂዎቹን አስደምሟል ። በፎቶግራፉ ላይ እንደ ጥንቱ ከጥቁር ሱፉ ላይ ጥቁር ካባ ደርቦ፤ እጆቹን እምብርቱ አጠገብ አነባብሮ በኩራት ተኮፍሶ ቁሟል ። ከጀርባው ቀያይ መስኮቶች እና መዝጊያዎች ያሉት ሕንፃ ይታያል ። በኢንስታግራም ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወድደውታል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ