1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 15 2015

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ እጅግ ውብ ፉክክር በታየበት ግጥሚያ አርሰናል ማንቸስተር ዩናይትድን ድል በማድረግ ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሳት የቆረጠ መሆኑን ዐሳይቷል። ኧርሊንግ ኦላንድ በዘንድሮ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለማንቸስተር ሲቲ አራተኛ ሔትትሪኩን ሠርቷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቬርደር ብሬመን በኮሎኝ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል።

Bundesliga, 16. Spieltag, Borussia Dortmund - FC Augsburg
ምስል IDennis Ewert/RHR-FOTO/imago images

የጥር 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ እጅግ ውብ ፉክክር በታየበት የትናንቱ ግጥሚያ አርሰናል ማንቸስተር ዩናይትድን ድል በማድረግ በእርግጥም ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሳት የቆረጠ መሆኑን ዐሳይቷል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲን በአምስት ነጥቦች በልጧል። ኧርሊንግ ኦላንድ በዘንድሮ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለማንቸስተር ሲቲ አራተኛ ሔትትሪኩን ሠርቷል። በርካታ ተጨዋቾቻቸው የተጎዱባቸው ቸልሲ እና ሊቨርፑል ድል ርቋቸው የደረጃ ሰንጠረዡ አማካይ ላይ እየተንገታገቱ ነው። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቬርደር ብሬመን በኮሎኝ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቻን ፉክክር ተሰናብቷል። በዐለም የእጅ ኳስ ፉክክር የጀርመን ቡድን ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ዛሬ ማታ ወሳኝ ግጥሚያውን ያደርጋል።  

ፕሬሚየር ሊግ
አርሰናል ዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ግስጋሴውን ቀጥሏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታው እየቀረው ነጥቡን 50 አድርሷል። ቡካዮ ሳካ፤ ኤድዋርድ ንኬቲያህ እና ጋብሪዬል ማርቲኔሊን ትናንት በአጥቂ መስመር ያሰለፈው አርሰናል በስተመጨረሻም የሚፈልገውን ድል አጣጥሟል። ለመድፈኞቹ እያንዳንዷ ጨዋታ በልዩ ጥንቃቄ የምትከወን ሆናለች።  እጅግ ብርቱ ፉክክር በታየበት ግጥሚያ ወደ አርሰናል ኤሚሬት ስታዲየም ያቀኑት የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾች በኳስ ይዞታ፤ በቡድንም ሆነ በግል ጥበብ ተበልጠው 3 ለ2 ተሸንፈዋል። 

በአርሰናል የ3 ለ2 ሽንፈት የገጠመው የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን ተጨዋች ማርኩስ ራሽፎርድ የመጀመሪያውን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ምስል Martin Rickett/empics/picture alliance

በትናንቱ ግጥሚያ ቀዳሚዋን ግብ በ17ኛው ደቂቃ በማርኩስ ራሽፎርድ ያስቆጠረው ማንቸስተር ዩናይትድ ጥረት ቢያደርግም ከመሸነ ፍግን አልተረፈም። ለአርሰናል በተለይ ሁለት ግቦቹን በ24ኛው እና 90ኛው ደቂቃዎች ላይ ያስቆጠረው ኤድዋርድ ንኬቲያህ እና ቡካዮ ሳካ እጅግ ጎልተው ታይተዋል። ቡካዮ ሳካ 53ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ካስቆጠረበት ቦታ ላይ ተመሳሳይ የግብ ሙከራ አድርጎ ለጥቂት ዒላማውን ሳይስት ቀረ እንጂ በምሽቱ ለእሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ ባስቆጠረ ነበር። የአርሰናሉ ተመላላሽ ተከላካይ ኦሌክሳንደር ሲቼንኮም በአብዛኛው የቡድኑን አጥቂ መስመር በመደገፍ ድንቅ እንቅስቃሴ ዐሳይቷል።  ለማንቸስተር ዩናይትድ ሁለተኛዋን ግብ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ነው። 

45 ነጥብ ይዞ አርሰናልን የሚከተለው ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ ዎልቨርሀምፕተንን ትናንት በኳስ ይዞታም በአጠቃላይ እንቅስቃሴም በልጦ 3 ለ0 አሸንፏል። በኢትሀድ ስታዲየማቸው አስተማማኝ ድል ላገኙት ማንቸስተር ሲቲዎች ኖርዌያዊው አጥቂ አራተኛ ሔትትሪኩን ሠርቷል። ኧርሊንግ ኦላንድ የትናንቱን ጨምሮ በዚህ የጨዋታ ዘመን እስካሁን ለማንቸስተር ሲቲ አራት ጊዜ በእየጨዋታዎቹ ሦስት ግቦችን ማስቆጠር የቻለ የግብ ቀበኛ ነው። ኧርሊንግ ኦላንድ ትናንት 20ኛው እና 54ኛው ደቂቃዎች ላይ በጨዋታ፤ 50ኛው ላይ ደግሞ በፍጹም ቅጣት ምት በአጠቃላይ ሦስት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። የቀድሞ የቦሩስያ ዶርትሙንድ አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድ የመጀመሪያ ሔትሪኩን የሠራው ክሪስታል ፓላስን 4 ለ2 ባሸነፉበት ጨዋታ ነው። ከዚያም ከአራት ቀናት በኋላ ኖቲንግሀም ፎረስ ትላይ በተመሳሳይ ሦስት ግቦችን ኧርሊንግ ኦላንድ አስቆጥሮ ነበር። ጥቅምት መጨረሻ ላይ ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድን 6 ለ3 ጉድ ባደረጉበት ጨዋታ ይኸው የግብ ቀበኛ ሦስት ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል።

ትናንት በነበረ ሌላ ግጥሚያ ሊድስ እና ብሬንትፎርድ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።  ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ክሪስታል ፓላስ እና ኒውካስል ዩናይትድ እንዲሁም ሊቨርፑል እና ቸልሲ ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርተዋል። ቦርመስ ከኖቲንግሀምፎረስት ጋር አንድ እኩል ሲወጣ፤ ላይስተር ሲቲ እና ብራይተንም ሁለት እኩል ተለያይተዋል። አስቶን ቪላ ሳውዝሀምፕተንን 1 ለ0፤ ዌስትሀም ዩናይትድ ኤቨርተንን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ዛሬ ማታ ፉልሀም 33 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀምን ያስተናግዳል። 

ዘንድሮ በአሸናፊነት የሚገሰግሰው አርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በአሰልጣኝነት ዘመናቸውምስል picture-alliance/dpa

ቡንደስሊጋ
በጀርመን ተወዳጁ የቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ጨዋታ ዐርብ እለት በባየርን ሙይንሽን እና ላይፕትሲሽ ግጥሚያ ዳግም ጀምሯል። ኮሎኝ ብሬመንን 7 ለ1 ድል ያደረገበት ውጤት ግን እጅግ አስደንጋጭ ነበር። በኮሎኝ ቡድን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታም አምስቱ ግቦች የተቆጠሩት ከመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ እረፍት በፊት ነበር። የኮሎኝ አሰልጣኝ ሽቴፈን ባውምግራት ቡድናቸው ብሬመንን እንዲያ በሰፊ የግብ ልዩነት ከረመረመ በኋላ አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች ሲሰጡ ኮራ ብለው ነው። 

«ከምንም በፊት፤ ደስ የሚለው ነገር ተጨዋቾቹ ገና ጨዋታው ከመጀመሩ አንስቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ በእልህ መጫወታቸው ነው። የምንፈልገው ያን ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ ግልፅ ነበር። ያው በመሀል የሆኑ ነገሮች ነበሩ። አንዳንዴ በእንደዚያ ያለ ጨዋታ እንዲህ ያለ ነገርም ያስፈልግሀል። ግን ደግሞ ያያችሁት ሆኗል። ጥሩ ነው የተጫወትነው። ብዙ ጥሩ ነገሮችን ዐሳይተናል። እንደ እኔ ዕይታ በእየጊዜው አንዳች ነገር ዕያሳየን ነው። በዚያ ከፍታ ላይ ደግሞ እንደዚያ ያለ ውጤት ማግኘት።  ያንን እንዴት ማጣጣም እንዳለብን አስቀድመን አውቀናል እና ሁሉም ነገር ጥሩ ነው። እንግዲህ ሁሉም ነገር አልፏል። ዛሬ ቢያንስ ለአፍታም ቢሆን እንደሰታለን።»

ወደ ኮሎኝ ራይን ኢነርጂ ስታዲየም አቅንቶ ብርቱ ሽንፈት ብቻ ሳይሆን አደገኛ ውድቀት የደረሰበት የቬርደር ብሬመን ቡድን አሰልጣኝ ዖሌ ቬርነር በበኩላቸው ቅዳሜ ዕለት በኮሎኝ ስለገጠማቸው ክስተት ለማብራራት ቃላት ያጠራቸው ይመስላል።

«በቃላት ለመግለጥ ይከብዳል። ምክንያቱም ከሁሉም አቅጣቻ ሲታይ ዛሬ ያሳየነው አቋማችን መቼም ሊደገም የማይገባው እጅግ ደካማ ነው። ትርምስምሱ የወጣ ነበር ማለት ይቻላል። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች አደረጃጀታችን ቢያንስ ጥሩ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ሦስት ጊዜም ቢሆን ራሳችን ነን ኮለኖችን ወደ ግብ ክልላችን የጋበዝናቸው። ሁለት ጊዜያት እንደውም ወደ ባላጋራ ቡድን በተጠጋንበት ወቅት ሲሆን፤ አንዱ ደግሞ በራሳችን የግብ ክልል የተገኘ የእጅ ውርወራ ነው። ከዚያም ትርምስምሳችን ነው የወጣው። ከባላጋራም ሆነ ከግል ሁኔታ አንጻር መቼም ቢሆን እንዲህ ያለ አቋም ሊኖረን አይገባም።»  

ብሬመንን 7 ለ1 ድል ያደረገው የኮሎኝ ቡድን የመጀመሪያዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ተጨዋቾቹ ደስታቸውን ሲገልጡምስል Harald Bremes/Jan Huebner/IMAGO

ለቬርደር ብሬመን በቅዳሜው ግጥሚያ ለማጽናኛ ያህል የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ኒክላስ ፉይልክሩግ አንድ በጭንቅላት አስቆጥሯል። ቬርደር ብሬመን 21 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከስሩ የሚገኘው ኮሎኝን የሚበልጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ኮሎኝ ነገ ባየር ሙይንሽንን ለመግጠም ወደ ሙይንሽን አሊያንትስ አሬና ያቀናል። 

ቡንደስሊጋውን ባየርን ሙይንሽን አሁንም በ35 ነጥብ ይመራል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት፤ ዑኒዮን ቤርሊን እና ፍራይቡርግ እኩል በ30 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ያለውን የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ ተቆጣጥረዋል። ላይፕትሲሽ 29 ነጥብ ይዞ ለአውሮጳ ሊግ የምድብ ጨዋታ ማሳለፍ የሚያስችለው 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እንዲሁም ትናንት አውስቡርግን 4 ለ3 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ለአውሮጳ ኮንፈረንስ ሊግ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚያበቃውን 6ኛ ደረጃ ይዟል። ሽቱትጋርት፤ ሔርታ ቤርሊን እና ሻልከ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ናቸው። 

ቻን
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለሀገር ውስጥ ቡድኖች ብቻ የሚሰለፉ ተጨዋቾች ከሚሳተፉበት የአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮን (CHAN) ውድድር ተሰናብቷል።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ ዕለት የምድቡ ሦስተኛ ግጥሚያውን ከሊቢያ ጋር አከናውኖም የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። በሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ማክሰኞ ዕለት በስታድ ደ ባራኪ ስታዲየም አድርጎ በአስተናጋጇ አልጄሪያ የ1 ለ0 ሽንፈትን አስተናግዷል። የኢትዮጵያ ቡድን በምድቡ የመጀመሪያ ግጥሚያ ከሞዛምቢክ ጋር ያለምንም ግብ በመለያየት ካገኘው አንድ ነጥብ ውጪ በጋቶች ፓኖም አንድ ብቸኛ ግብ ከውድድሩ ተሰናብቷል።  በቅዳሜው ግጥሚያ ሊቢያዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኳስ ይዞታ ቢበለጡም ለድል ግን በቅተዋል። 

እጅ ኳስ
በዐለም እጅ ኳስ ጨዋታ ውድድር የጀርመን ቡድን ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ዛሬ ማታ ከኖርዌይ ጋር ይጋጠማል። የፈረንሳይ፤ የስፔን፤ የስዊድን እና የሐንጋሪ ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፋቸውን ከወዲሁ አረጋግጠዋል።  በዐለም እጅ ኳስ ጨዋታ ፉክክር በሩብ ፍጻሜ የጀርመን ቡድን ከፈረንሳይ አለያም ከስፔን ጋር ቢገጥም ፍላጎቱ መሆኑን ገልጧል።

ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች አውስትራሊያዊው አሌክስ ደ ሚናውርን አሸንፏልምስል Pavel Mikheyev/REUTERS

የሜዳ ቴኒስ
በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች አውስትራሊያዊው አሌክስ ደ ሚናውርን ዛሬ አሸንፏል። ኖቫክ በዛሬው ግጥሚያ ሁለት ጊዜ 6 ለ2 እንዲሁም አንዴ 6 ለ1 በአጠቃላይ ድምር ውጤት 3 ለ0 በማሸነፍ ነው ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው። የ35 ዓመቱ ሠርቢያዊ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች በአራተኛ ዙር የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ የሩስያው አንድሬ ሩብሌቭ ይጠብቀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW