1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጥር 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 19 2017

እንደተለመደው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም የውድድር መድረኮች ድል ቀንቷቸዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፉክክር አርሰናል ወሳኝ የሆነ ድሉን በአንዲት ብቸኛ ግብ አግኝቷል ። ሊቨርፑል በመሪነቱ እንደገሰገሰ ነው ።

Fußball-Bundesliga 2025 | Freiburg gegen Bayern München
ምስል፦ Thomas Kienzle/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

እንደተለመደው  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም የውድድር መድረኮች ድል ቀንቷቸዋል።  ጃፓን ውስጥ ከአንድ ወር በኋላ ለሚደረገው የቶኪዮ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ተሳታፊዎች በተመለከተ ቃላ መጠይቅ አድርገናል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፉክክር አርሰናል ወሳኝ የሆነ ድሉን በአንዲት ብቸኛ ግብ አግኝቷል ። ሊቨርፑል በመሪነቱ እንደገሰገሰ ነው ። በሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ጀርመናዊው ተፎካካሪ በጣሊያናዊው ድል ተነስቷል ።

አትሌቲክስ

የቶኪዮ ማራቶን ውድድር ሊካሄድ አንድ ወር ግድም በቀረበት በአሁኑ ወቅት እዛው ጃፓን ውስጥ በተከናወነ የኦሳካ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወርቅነሽ ኢዴሳ አሸናፊ ሁናለች። አትሌት ወርቅነሽ ትናንት አንደኛ በመውጣት ያሸነፈችው 2:21.00 በመሮጥ ነው ። ጃፓናውያቱ ካና ኮባያሽ እና ዩካ ሱዙኪ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በውድድሩ ሦስት ኬኒያዊት፣ አንዲት የባህሬንና ሌላ የእሥራኤል አትሌት እንዲሁም፤ አራት የሌላ አገራት ተፎካካሪዎች ሲታደሙ የቀሩት በአጠቃላይ ጃፓናውያን አትሌቶች ናቸው ።

በሌላ የግማሽ ማራቶን ፉክክር፦ በስፔን ሚጃ ቴራሳ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ሁነዋል ። በሴቶች ፉክክር፦ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ኪሮስ ሙዓዝ እና ገነት ሣኅሌ አንደኛ እና ሁለተኛ በመውጣት የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ አስገኝተዋል ።  ኪሮስ ውድድሯን ለማጠናቀቅ (1:14:06) ሲፈጅባት፤ ገነት ከ42 ሰከንዶች በኋላ ተከትላት አጠናቃለች ። ስፔናዊቷ ባርባራ ራሞን ሳላማንያ የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። የጥር 12 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በወንዶች ፉክክር የአትሌት ሰለሞን ባረጋ ወንድም ሚኪያስ ባረጋ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር (1:02:18) አሸንፎ ወርቁን አጥልቋል ።  ኬንያውያኑ ጊልበርት ኪቤት (1:02:40) እና ቲሞቲ ኪፕቹምባ (1:03:185)ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ። 

ከ33 ቀናት በኋላ ጃፓን ውስጥ ለሚካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ተሳታፊ አትሌቶች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ሁኗል ። ከኢትዮጵያ በወንድም በሴትም 15 አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል ። በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ስለ አትሌቶቹ ማንነትና ወቅታዊ ብቃት በማብራራት ይጀምራል ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰምስል፦ DW

ፕሬሚየር ሊግ

የማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አንድሬ ዖናና ፉልሀምን 1 ለ0 ማሸነፋቸው ለቡድኑ በጨዋታ ዘመኑ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር አጋጣሚ ነው ብሏል ። ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በ78ኛ ደቂቃ ላይ ትናንት ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ማንቸስተር ዩናይትድን ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ አድርጓታል ። ባለፈው ግጥሚያ በገዛ ሜዳው ኦልድ ትራፎርድ በብራይተን የ3 ለ1 ሽንፈት ላስተናገደው ማንቸስተር ዩናይትድ በእርግጥም የትናንቱ በተቃራኒ ሜዳ ያገኘው ድል ወሳኝ ነበር ። አስቶን ቪላ ከዌስት ሐም ጋር አንድ እኩል ሲለያይ፤ ብሬንትፎርድ እና ላይስተርሲቲ ተጋጣሚዎቻቸው ክሪስታል ፓላስን እና ቶትንሀም ሆትስፐርን በገዛ ሜዳቸው 2 ለ1 ድል አድርገዋል ።

ቅዳሜ ከነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ በተለይ የዋንጫ ተፎካካሪው እና በደረጃ ሰንጠረዡ 3ኛ ላይ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት በቦርመስ የደረሰበት የ5 ለ0 ብርቱ ቅጣት በርካቶችን አስደምሟል ። ኒውካስልን 4 ለ1 ድል አድርጎ የነበረው ቦርመስ ከትናንት በስትያም መሰል ድሉን ኖቲንግሀም ፎረስት ላይ ደግሞታል ። በቅዳሜው ድል የምዕራብ አፍሪቃዊቷ ቡርኪናፋሶ ምርጥ አጥቂ ዳንጎ ዋታራ ለቦርመስ ሦስት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል ። ቅዳሜ ዕለት ኤቨርተን ብራይተንን 1 ለ0 አሸንፏል ።

በሌሎች ግጥሚያዎች፦ አርሰናል ወሳኝ በሆነ አንድ ብቸኛ ግብ በፕሬሚየር ሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪነት እድሉን እጅግ አስፍቷል ። ሁለት ቀይ ካርዶች ለሁለቱም ቡድኖች ተጨዋቾች በተሰጠበት የቅዳሜው ግጥሚያ አርሰናል ዎልቭስን በገዛ ሜዳው 1 ለ0 አሸንፏል ። የማሸነፊያዋne ግብ 74ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሪካርዶ ካላፎሪ ነው ። አርሰናል 47 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው መሪው ሊቨርፑልም በስድስት ነጥብ ይበለጣል ። የጥር 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቡንደስሊጋ፦ የመሪው ባዬርን ሙይንሽ ተጨዋቾች ሔሪ ኬን እና ሌዎን ጎሬትስካምስል፦ Bahho Kara/Kirchner-Media/IMAGO

ቅዳሜ ዕለት በሜዳው ኢትሀድ ስታዲየም እና ደጋፊው ፊት ቸልሲን 3 ለ1 ድል ያደረገው ማንቸስተር ሲቲ በ41 ነጥብ አራተኛ ደረጃውን እንዳስጠበቀ ነው ። ለማንቸስተር ሲቲ ሶስኮ ግቫርዲዮል፤ ፊል ፎደን እና ኧርሊንግ ኦላንድ አንድ አንድ ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል ። ኧርሊንግ ኦላንድ ቅዳሜ ዕለት 68ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ባሳረፋት ግብ አሌክሳንደር ይሳቅን በአንድ የግብ ልዩነት መብለጥ ችሏል ። የኒውካስሉ አጥቂ አሌክሳንደር ቡድኑ ሳውዝሐምፕተንን በሜዳው 3 ለ1 ድል ሲያደርግ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር አጠቃላይ ግቦቹን 17 አድርሷል ። የሊቨርፑል አጥቂ ሙሐመድ ሣላኅ 19 በኮከብ ግብ አግቢነት ይመራል ።

ሊቨርፑል ወራጅ ቀጣናው ግርጌ በ16 ነጥብ የሚዳክረው ኢፕስዊች ታወንን 4 ለ1 ድል ባደረገበት የቅዳሜው ግጥሚያ ሁለተኛዋን ግብ 35ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ሞሐመድ ሣላኅ ነው ። ቀሪዎቹ ግቦች የዶሚኒክ ሶቦዝላይ እና ኮዲ ጋክፖ ናቸው ። 90ኛው ደቂቃ ላይ የኢፕስዊች ታወን ደጋፊዎችን ያስፈነጠዘችውን የማስተዛዘኛ ግብ ጄኮብ ግሬቪስ አስቆጥሯል ።

ቡንደስሊጋ

የሞሐመድ ሳላኅ የአገር ልጅ ግብጻዊው ዖማር ማርሙሽ ከጀርመን ቡንደስሊጋ ኮከብነት ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሸጋገሩ የሰሞኑ መነጋገሪኢ ሁኗል ። ዖማር ማርሙሽ ቁልፍ ተጨዋች ከነበረበት የጀርመኑ ፍራንክፉርት ቡድን የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ዘንድሮ ብርቱ ፈተና ወደ ገጠመው ማንቸስተር ሲቲ ያቀናው በ79 ሚሊዮን ዶላር የዝውውር ክፍያ ነው ። በቡንደስሊጋው የነበረውን ኳስ ተቆጣጥሮ ተከላካዮችን የማርበትበት ብቃት በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለማንቸስተር ሲቲም ይደግማል ተብሏል ። የታኅሣሥ 28 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ በ48 ነጥብ የሚመራው ባዬርን ሙይንሽን ፍራይቡርግን 2 ለ1 አሸንፏል ። በ42 ነጥብ ተከታዩ ተከታዩ ባዬርን ሌቨርኩሰን ከላይፕትሲሽ ጋር ሁለት እኩል ተለያይቷል ። በሆፈንሀይም ሜዳ ትናንት ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ የተጋራው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ37 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሰፈረ ነው ።

ጀርመናዊው አሌክሳንደር  ዜቬሬቭ በአውስትራሊያ ፍጻሜ በጣሊያናዊው ጃኒክ ዚነር የ6 ለ3 ሽንፈት ደርሶበታልምስል፦ Quinn Rooney/Getty Images

ከቬርደር ብሬመን ጋር ቅዳሜ ዕለት ሁለት እኩል የወጣው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 11ኛ ደረጃ ላይ ይዳክራል ። ማይንትስ ሽቱትጋርትን 2 ለ0 እንዲሁም አውግስቡርግ ሐይደንሀይምን 2 ለ1 ማሸነፍ ችለዋል ። ቮልፍስቡርግ እና ሆልሽታይን ኪየል ሁለት እኩል ተለያይተዋል ። ሐይደንሀይም እና ሆልሽታይን ኪየል በ14 እና 12 ነጥብ 16ኛ እና 17ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ። ከስራቸው 10 ነጥብ ብቻ ያለው ቦሁም የመጨረሻ ደረጃው ላይ ሰፍሯል ።

የሜዳ ቴኒስ

በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ፍጻሜ  የጀርመን ተፎካካሪ አሌክሳንደር  ዜቬሬቭ ትናንት በጣሊያናዊው ጃኒክ ዚነር የ6 ለ3 ሽንፈት ደርሶበታል ። ሽንፈቱ በአጠቃላይ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ድል በመንሳት ዋንጫ ለማንሳት ጫፍ ደርሶ ለነበረው አሌክሳንደር እጅግ አስቆጭ ነው ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW