1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 6 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 6 2016

አይቮሪኮስት ባሰናዳችው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ ያልተጠበቁ ቡድኖች ጠንካራ ቡድኖችን ጉድ አድርገዋል ። ግብፅ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለጥቂት ከሽንፈት ስትተርፍ፤ ጋና ያልተጠበቀ ሽንፈት ተከናንባለች። ለዓለም ዋንጫ ለመድረስ አንድ ጨዋታ ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ዛሬ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል።

አይቮሪኮስት አቢጃን፤ አላሳን ዋታራ ስታዲየም
አይቮሪኮስት የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫን በደማቅ ሁኔታ ከፍታለች ምስል Fareed Kotb/AA/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

አይቮሪኮስት በምታሰናዳው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ ያልተጠበቁ ቡድኖች ጠንካራ ቡድኖችን ጉድ አድርገዋል ። ግብፅ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለጥቂት ከሽንፈት ስትተርፍ፤ ጋና ያልተጠበቀ ሽንፈት ተከናንባለች ። ቀዳሚ ግጥሚያዋን ያሸነፈችው አስተናጋጇ አይቮሪኮስት ድንቅ የመክፈቺያ ስነስርዓትም አከናውናለች ። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የኢትዮጵያብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለኮሎምቢያው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ አንድ ጨዋታ ብቻ ይቀረዋል ። ዛሬ ከሞሮኮ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ-ገብርኤልን በስልክ አነጋግረናል ። 

አትሌቲክስ

41ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር ትናንት (እሁድ፤ ጥር 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም)አዲስ አበባ ውስጥ ተከናውኗል ። በወንድም በሴትም በአራት አይነት የውድድር ዘርፎች አሸናፊ ለሆኑም ሽልማት መሰጠቱንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል ። ውድድሮቹ የተከናወኑት፦ በድብልቅ ሪሌ፤ በ6ኪሜ ወጣት ሴቶች፣  በ8ኪሜ ወጣት ሴቶች እና ወንዶች፣ በ10ኪሜ አዋቂ ሴቶች እና ወንዶች ነበር ። በድብልቅ ሪሌ ፉክክር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ኛ በመውጣት አሸናፊ ሆኗል ። ሸገር ሲቲ እና ኦሮሚያ ክልል የ2ኛ እና የ3ኛ ደረጃ አግኝተዋል ።

እግር ኳስ

ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ አለማለፉ ሊወሰን አንድ ጨዋታ ብቻ ይቀረዋል ። በዓለም ዋንጫ ማጣርያ  የመጨረሺያ ዙር የመጀመርያ ጨዋታውን ቅዳሜ ዕለት ከሜዳው ውጪ በኤል አብዲ ስታዲየም አከናውኖ ጥሩ ቢጫወትም በሞሮኮ 2-0 ተሸንፏል ። የመልሱ ጨዋታ እሁድ ጥር 12 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል። በቅዳሜው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለይ በመሳይ ተመስገን እና ንግሥት በቀለ ያገኛቸውን ግብ የሚሆኑ አጋጣሚዎች አለመጠቀሙ እጅግ የሚያስቆጭ ነበር ። ለሞሮኮ ያስሚን ዞሀር እና ባሰር በ10ኛው እና 51ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል ።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ-ገብርኤል «ሞሮኮ በልጦን አይደለም 2 ለ0 ያሸነፈን» ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ መጨረሻው ዙርየ  የማጣሪያ ግጥሚያ ያለፈው የማሊ ቡድንን በሦስተኛው ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በድምሩ 6 ለ0 አሸንፎ ነበር ። ቅዳሜ በነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ጋና ከሜዳዋ ውጪ ሴኔጋልን 2 ለ0 አሸንፋለች ።  ካሜሩን በበኩሏ ዐርብ ዕለት ግብጽን 4 ለ2 ድል አድርጋለች ።

ከአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ-ገብርኤል ጋ የተደረገውን ሙሉ ቃለ መጠይቅ እዚህ ያገኛሉ

This browser does not support the audio element.

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ በዩናይትድ ስቴትስ የእግር ኳስ ታሪክ ከ39 ዓመት ወዲህ በተከላካይነት የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ሆና በመመረጥ የመጀመሪያ ሰው ሆነች ። ሳንሆዜ ካሊፎርኒያ ተወልዳ ያደገችው የ23 ዓመቷ የእግር ኳስ ተጨዋች በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የመሀል ተከላካይ ናት ። ከዛው ከዩናይትድ ስቴትስ ሳንወጣ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሎዛ አበራ በብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ሊግ ቡድኖች (NWSL) ጋ ሙከራ ለማድረግ ፍሎሪዳ እንደምትገኝ ተዘግቧል ። ሎዛ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በርካታግቦችን በማስቆጠር ድንቅ ተጨዋችነቷን ያስመሰከረች ናት ።

የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ

በአፍሪቃ ዋንጫ የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅን ከፊት መስመር ያሰለፈችው ግብጽ ባልተጠበቀ መልኩ በሞዛምቢክ ሽንፈት ከመከናነብ ለጥቂት ተርፋለች ። በቡድንም ሆነ በግል እጅግ ውብ አጨዋወት ያሳየው የሞዛምቢክ ቡድን በተከላካይ ጥፋት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለሽንፈት መዳረጉ ደጋፊዎቹን እጅግ የሚያስቆጭ ነበር ። ሞሐመድ ሣላኅ በጭንቀት ተውጦ የነበረው የግብጽ ብሔራዊ ቡድኑን ከጉድ የታደገው መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 7ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው የፍጹም ቅጣት ምት ነው ። አቻ የምታደርገው ግብ የተቆጠረችውም ኳሷን ከግቡ የቀኝ ቋሚ ጋር አላትሞ ከመረብ በመቀላቀል ነው ።

የግብጽ ቡድን ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ላይ ነበር በሞስጣፋ ሞሐመድ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ። የሞዛምቢኩ ዊቲ ከረፍት መልስ በ55ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል ። አፍታም ሳይቆይ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ሴሲዮ ባውኩዌ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ በማሳረፍ የግብጽ ተጨዋቾችንም ሆነ ደጋፊዎችን እጅግ አስደንግጧል ። ጨዋታው ተጠናቆ የባከነ ሰአት ተጨምሮም በአጠቃላይ 97ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ቅጣት ምቱ ባይቆጠር ኖሮ ከፍተና ግምት የተሰጠው የግብጽ ቡድን በቀላሉ ያሸንፈዋል በተባለው የሞዛምቢክ ቡድን የሽንፈትን ጽዋ ይጎነጭ ነበር ።

እንደ ግብጽ ቡድን ሁሉ ትናንት ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ሁለት ቡድኖች ባልተጠበቁ ቡድኖች ብርቱ በትር ቀምሰዋል ። ናይጄሪያ ከፊቱ ተጋርጦበት የነበረውን ሽንፈት በ2 ደቂቃ ልዩነት በቪክቶር ዖሲምሄን ባይቀለብሰው ኖሮ ኢኳቶሪያል ጊኒ ጉድ አድርጎት ነበር ። ኤኳቶሪያል ጊኒ 36ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ግብ በኢባን ሳልቫዶር በማስቆጠር ናይጄሪያን አስደንግጧል ። የኤኳቶሪያል ጊኒ ተጨዋቾችና ስታዲየም የታደሙ ጥቂት ደጋፊዎቻቸው ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን ደስታቸውን አጣጥመዋል ።

አይቮሪኮስት አቢጃን፤ አላሳን ዋታራ ስታዲየም ውስጥ የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ በደማቅ ሁኔታ ሲከፈት ከፊል ገጽታምስል Weam Mostafa/BackpagePix/picture alliance

የታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ የጋና በኬፕ ቬርዴ 2 ለ1 መሸነፏ ግን ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነበር ። ኬፕ ቬርዴ ጨዋታው በተመጀመረ በ17ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ በጃሚሮ ሞንታይሮ አስቆጥራለች ። ጋና በሁለተኛው አጋማሽ 56ኛ ደቂቃ ላይ በአሌክሳንደር ጂኩ አቻ የምታደርገውን ግብ ብታገኝም፤ 90 ደቂቃ መደበኛ ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪው 2ኛ ደቂቃ ላይ ጋሪ ሮድሪጌዝ የማሸነፊያዋን ግብ ከመረብ አሳርፎ ደጋፊዎችን አስቦርቋል ። ሮጧል ። ግብ ካስቆጠረ በኋላ መለያውን አውልቆ ወደ ደጋፊዎች በመሮጡም ቢጫ ካርድ ዐይቷል ።  ቅዳሜ በደማቅ መክፈቻው፥ አይቮሪኮስት ጊኒ ቢሳዎን 2 ለ 0 ድል አድርጋለች ። እንደተጠበቀውም ፎፋና ተከላካዮችን አስጨንቋል፥ አንድ ግብም አስቆጥሯል ። የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ዛሬ እና ነገ ሦስት ሦስት ከነገ  በስትያ ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነው ሁለተኛው ዙር ግጥሚያ ሐሙስ ይቀጥላል ። ሴኔጋል ዛሬ ጋምቢያን 3 ለ0 አሸንፋለች ። 

ፍራንስ ቤከን ባወር

በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ ስመ ጥር ዝና ካተረፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የ78 ዓመቱ ፍራንስ ቤከን ባወርባለፈው ሳምንት ማረፉ በርካታ የስፖርት አፍቃሪዎችን አሳዝኗል ። በጀርመን የስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ «ንጉሠ-ነገሥት» በሚል ቅጽል ስም ከሚታወቀው ቤከን ባወር ጋ በአንድ ወቅት በብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የነበሩት ቮልፍጋንግ ዖፈራዝ ጓደኛቸውን እንዲህ ይዘክራሉ ። «ከእሱ ጋ ሦስት የዓለም ዋንጫዎችን ተጫውቻለሁ ።  በጋራ ታላላቅ ስኬቶችን አከናውነናል ። ምንጊዜም ጥሩ ሰው ነበር ። በዚያ ላይ ታላቅ ተጨዋችም ነበር ። ወደፊት እንደዚያ ያለ ተጨዋች ይኖራል ብሎ መገመት ይከብደኛል ።  ድንቅ ነበር ። የእሱ ደረጃ ላይ የመድረስ ዕድል ያገኘ ማንም የለም ። »

በጀርመናውያን ዘንድ «ንጉሠ-ነገሥት» በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው ቤከን ባወር በወጣትነቱምስል SvenSimon/picture alliance

ቤንከንባወር በጀርመን የእግር ኳስ ታሪክ በተጨዋችነትም ሆነ በአሰልጣኝነት ዘመን የዓለም ዋንጫ ካነሱ ሦስት ጀርመናውያን መካከል አንዱምበመሆን ይታወሳል ። 

የታኅሣሥ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ቦሁም ከቬርደር ብሬመን እንዲሁም ማይንትስ ከቮልፍስቡርግ አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ዶርትሙንድ ዳርምሽታድትን 3 ለ0 ሲረታ፤ ሽቱትጋርት ትናንት በቦሩስያ ሞምይንሽንግላድባኅ የ3 ለ1 ሽንፈት ደርሶበታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ከቶትንሀም ጋ ተጫውቶ ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ጥሏል ። ኤቨርተን ከአስቶን ቪላ ጋ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። በርንሌይ ከሉቶን ታውን አንድ እኩል ሲወጣ፤ ጸልሲ ፉልሀምን 1 ለ0 አሸንፏል ። ማንቸስተር ሲቲ በኒውካስል ሜዳ 3 ለ2 ድል አድርጓል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW