1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 04 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 4 2017

በቺካጎ ማራቶን ኬንያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ድል ሲቀዳጁ በሴቶች ፉክክር በኢትዮጵያ ተይዞ የነበረው የዓለም ክብረወሰን ተሰብሯል ።ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቤርሊን ማራቶን ከሁለት ሳምንት በፊት የውድድሩ ሙሉ ለሙሉ አሸናፊዎች ሁነው በቺካጎው ኬንያውያን ለምን በለጡ?

Fußball Euro 2024 | Niederlande v England
ምስል KENZO TRIBOUILLARD/AFP/Getty Images

የጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በቺካጎ ማራቶን ኬንያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ድል ሲቀዳጁ በሴቶች ፉክክር በኢትዮጵያ ተይዞ የነበረው የዓለም ክብረወሰን ተሰብሯል ። ኢትዮጵያውያንአትሌቶች በቤርሊን ማራቶን ከሁለት ሳምንት በፊት የውድድሩ ሙሉ ለሙሉ አሸናፊዎች ሁነው በቺካጎው ኬንያውያን ለምን በለጡ? ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። ሞሮኮ ለምታዘጋጀው የ2025 የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት በጊኒ በሰፋ የግብ ልዩነት ተሸንፏል ። በኔሽን ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ጀርመን ዛሬ ማታ ኔዘርላንድን ይገጥማል ። ዛሬ እና ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት 18 ጨዋታዎች ይኖራሉ ።  ተጨማሪ ዘገባዎችን አካተናል ።

አትሌቲክስ

በ2024 የቺካጎ ማራቶን ኬንያውያን በወንዶችም በሴቶችም አሸነፉ ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል ። በተለይ በሴቶች ፉክክር ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች በ2023 የቤርሊን ማራቶን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሠፋ ተይዞ የነበረውን (2:11:53) የዓለም ክብረወሰን በ2 ደቂቃ ግድም በማሻሻል ሰብራለች ።  በአሸናፊነት የገባችበት 2:09:56 አዲስ የዓለም ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል ። በሴቶች የማራቶን ሩጫ ታሪክም ከ2 ሰአት ከ10 ደቂቃ በታች በመግባት የመጀመሪያዋ ሆናለች ።

ባለፈው ዓመት የቺካጎ ማራቶን በ2ኛ ደረጃ አጠናቃ የነበረችው ኬኒያዊት አትሌት በ2021 እና 2022 በዚሁ ውድድር አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል ።  በዚሁ የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ አሠፋ 2:17:32 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። 

በወንዶች ተመሳሳይ የሩጫ ፉክክርም ድሉ የኬንያ ሁኗል ። ኬኒያዊው አትሌት ጆን ኮሪ 2:02:44 በመሮጥ አሸናፊ ሁኗል ። ኢትዮጵያዊው አትሌት ሑሴይዲን ሞሐመድ ኢሳ  (2:04:39) በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ።  በወንድም በሴትም ፉክክር የነሐስ ሜዳሊያው የኬኒያውያን ሁኗል ።

በ2024 የቺካጎ ማራቶን ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች በ2023 የቤርሊን ማራቶን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሠፋ ተይዞ የነበረውን (2:11:53) የዓለም ክብረወሰን በ2 ደቂቃ ግድም በማሻሻል ሰበረችምስል Patrick Gorski/USA TODAY Sports/Reuters

የመስከረም 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባከሁለት ሳምንት በፊት (እሁድ መስከረም 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) ጀርመን ውስጥ በተከናወነው የቤርሊን ማራቶን የ50ኛ ዐመት ልዩ የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ በሴቶች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከታትለው በመግባት ዓለምን አስደምመው ነበር ። በወንዶችም ድሉ የኢትዮጵያውያን ነበር ። ይህ በቤርሊን ታይቶ የነበረው አንጸባራቂ ድል በቺካጎ ያልተደገመው ለምን ይሆን? በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የስፖርት ዘገባዎችን የሚያቀርበው ጋዜጠኛ ዘርዓይ ኢያሱ ወጥ የሆነ የሥልጠና ተከታታይነት እጦትን እንደምክንያት ከዘረዘራቸው ነጥቦች ውስጥ ይጠቅሳል ።

የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ

ሞሮኮ ለምታዘጋጀው የ2025 የአፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የማጣርያ 3ኛ የምድብ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት በጊኒ የ4 ለ1 ሽንፈት አስተናገደ ። 4 ለ0 ሲመራ ለነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሦስት ጨዋታዎች የመጀመሪያዋን እና ብቸኛዋን የማስተዛዘኛ ግብ 62ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ከነዓን ማርክነህ ነው ።  ለጊኒ ሲይሆ ጉራሲይ ሦስት ኳሶችን አከታትሎ ከመረብ በማሳረፍ ሔትትቲክ ሠርቷል ። አራተኛው ግብ የሰይዱባ ሲሴ ነው ። ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ከሀገራቸው ውጪ አቢጃን አይቮሪ ኮስት ውስጥ ትናንት ባደረጉት ግጥሚያ የኢትዮጵያ ቡድን ላይ ሦስቱ ግቦች የተቆጠሩት ከእረፍት በፊት ነበር ።

በምድቡ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እስካሁን ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ9 ነጥብ ይመራል ። ሐሙስ ዕለት ታንዛኒያ ሜዳ ኪንሻሳ ድረስ የተጓዘው የኮንጎ ቡድን ለድል የበቃው በ53ኛው ደቂቃ ላይ በምዚዜ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ነው ። በሜዳዋ የተሸነፈችው ታንዛኒያ በ4 ነጥብ ሁለተኛ፤ ኢትዮጵያን ትናንት ያሸነፈችው ጊኒ በ3 ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። የኢትዮጵያ ቡድን በአንድ ነጥብ እና በስድስት የግብ ክፍያ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

ዘንድሮ ሞሮኮ ለምታዘጋጀው የ2025 የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድሩ ተጧጡፏል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Sia Kambou/AFP

ለአፍሪቃ ዋንጫ አዘጋጇ ሞሮኮ ከምትገኝበት ምድብ «ለ» ውጪ ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ቡድኖች በቀጥታ ያልፋሉ ።  ምንም እንኳን ሞሮኮ ማለፏ ቀድሞውኑም የተረጋገጠ ቢሆን የምድቧ መሪ ናት ።  ከሞሮኮ ጋር ከምድቡ ሦስት ቡድኖች ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበው ሌላ አንድ ቡድን አብሮ ያልፋል ። የመስከረም 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

እስካሁን በተደረጉ ሦስት ግጥሚያዎች አራት አራት ቡድኖችን ባካተቱ ሌሎች 12 ምድቦች ውስጥ፦ ግብፅ፤ አልጄሪያ፤ አዘጋጇ ሞሮኮ፤ አንጎላ እና አይቮሪ ኮስት በ9 ነጥብ ይመራሉ ። ናይጄሪያ፤ ማሊ፤ ካሜሩን፤ ኡጋንዳ እና ቡርኪና ፋሶም ከየምድባቸው በ7 ነጥብ መሪዎች ናቸው ። በምድብ «ሀ» ቱኒዝያ ኮሞሮስን በአንድ ነጥብ ብቻ በልጣ በ6 ነጥብ ትመራለች ።

ኔሽንስ ሊግ

በየኔሽንስ ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ማታም ይከናወናሉ ። ዛሬ ማታ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከኔዘርላንድ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ይጠበቃል ። ጨዋታው በባየርን ሙይንሽን ሜዳ ላይ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ ሦስት ሰአት ከ45 ደቂቃ ላይ ይጀመራል ። የጀርመን ቡድን እስካሁን በነበሩ ሦስት ግጥሚያዎች 7 ነጥብ በመሰብሰብ ምድቡን ይመራል ። የምሽቱ ተጋጣሚው ኔዘርላንድ በ5 ነጥብ ይከተላል ። ሁለት ነጥብ ያላት ሐንጋሪ በአንድ ነጥብ ከተወሰነችው ቦስኒያ እና ሔርዜጎቪና ጋር በተመሳሳይ ሰአት ዛሬ ማታ ከሜዳዋ ውጪ ትጫወታለች ።

ዛሬ ማታ ከሚኖሩ ጨዋታዎች መካከል ቤልጂየም ከፈረንሣይ እንዲሁም ዩክሬን ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርጉትም በብዙዎች ዘንድ ይጠበቃሉ ። ስፔን ከሠርቢያ፤ ፖላንድ ከክሮሺያ፤ ስዊትዘርላንድ ከዴንማርክ እንዲሁም ስኮትላንድ ከፖርቹጋል ጋር የሚያደርጓቸው ግጥሚያዎችም በነገው ዕለት ከሚጠበቁት መካከል ናቸው ። በአጠቃላይ ዛሬ እና ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት 18 ጨዋታዎች ይኖራሉ ። 

በየኔሽን ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ማታም ይከናወናሉ ምስል Lars Baron/Getty Images

ትናንት በነበሩ አራተኛ ዙር ግጥሚያዎች፦ እንግሊዝ ፊንላንድን በሜዳዋ ሔልሲንኪ ኦሊምፒክ ስታዲየም ውስጥ 3 ለ1 ጉድ አድርጋታለች ። ጃክ ግሪሊሽ፤ ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ እና ዴክላን ራይስ ለእንግሊዝ አስቆጥረዋል ። ፊንላንድ የማስተዛዘኛዋን ግብ መደበኛው 90 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃ ሲቀረው ያስቆጠረችው በአርቱ ሆስኮነን ነው ።  እንግሊዝ ከምድቡ 12 ነጥብ ያላት ግሪክን ተከትላ በ9 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። ግሪክ ትናንት በሜዳዋ አይርላንድን አስተናግዳ 2 ለ0 አሸንፋለች ።

ኦስትሪያ ኖርዌይን አስተናግዳ 5 ለ1 የሸኘችበት ግጥሚያ ትናንት ከነበሩ ጨዋታዎች በርካታ ግቦች የተመዘገቡበት ግጥሚያ ነው ። እንዲያም ሆኖ ከምድቡ ኖርዌይ ተመሳሳይ ሰባት ነጥብ ያላት ኦስትሪያን በግብ ክፍያ ልዩነት በልጣ አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ።

ዬርገን ክሎፕ የሬድ ቡል ሶከር ዓለም አቀፍ ኃላፊ ሁነው ተሹመዋል

በኔሽን ሊግ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የፊታችን ቅዳሜ ዳግም ይጀምራል። የጀርመን ቡንደስሊጋም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይከናወናል ። በሌላ የስፖርት ዜና፦ የቀድሞ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ በጀርመን ቡንደስሊጋ ተሳታፊ የሆነው ኤርቤ ላይፕትሲሽ ቡድን በሚገኝበት የሬድ ቡል ሶከር ዓለም አቀፍ ኃላፊ ሁነው ተሹመዋል ።  የ57 ዓመቱ ጀርመናዊ አሰልጣኝ በፕሬሚየር ሊግ ቆይታቸው ሊቨርፑልን በ209 የሻምፒዮንስ ሊግ፤ በዓመቱ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫዎችን እንዲያነሳ አስችለዋል ። በሁለቱም ዓመታት በፊፋ የዓለማችን ምርጡ አሰልጣኝ ተብለውም ተሸልመው ነበር ።

የቀድሞ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ በጀርመን ቡንደስሊጋ ተሳታፊ የሆነው ኤርቤ ላይፕትሲሽ ቡድን በሚገኝበት የሬድ ቡል ሶከር ዓለም አቀፍ ኃላፊ ሁነው ተሹመዋልምስል Elmar Kremser/Sven Simon/picture alliance

ከሊቨርፑል በራሳቸው ፍላጎት የለቀቁ ሲሆን በሬድ ቡል ሶከር በጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ሥራቸውን ይጀምራሉ ። ሬድ ቡል ሶከር፦ ከጀርመን ቡንደስሊጋው ሬድ ቡል ላይፕትሲሽ፤  ሬድ ቡል  ዛልስቡርግ በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው ኒው ዮርክ ሬድ ቡልስ፤ የብራዚሉ ብራጋንቲኖ እና የጃፓኑ ዖሚያ አርዲጃ  ቡድኖችን ያካትታል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሚገኘው ሊድስ ዩናይትድ ቡድንም ከፊሉ በሬድ ቡልስ ባለቤትነት የተያዘ ነው ። 

ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ ከሊቨርፑል ቀደም ሲል የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርርሙንድ እና ማይንትስ ቡድኖች አሰልጣኝም ነበሩ ። ቦሩስያ ዶርትሙንድን በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2011 የቡንደስሊጋ በዓመቱ ደግሞ የቡንደስሊጋም የጀርመን ፖካል (DFB) ዋንጫዎችን ማንሳት የቻሉ ጠንካራ አሰልጣኝ ናቸው ። በሬድ ቡል ቆይታቸው ግን የአሰልጣኝነት ሳይሆን የስፖርት ስትራቴጂ በማውጣት በበርካታ ጉዳዮች የማማከር ተግባር ነው የሚኖራቸው ተብሏል ። ሬድ ቡል በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ውስጥም ዋነኛ ተፎካካሪ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW