የጥቅምት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥቅምት 18 2017ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ክብረወሰን ሰብረው አሸንፈዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል እና ሊቨርፑል ብርቱ ፉክክር ዐሳይተዋል ። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ በባርሴሎና ጉድ ሁኗል ። ትናንት ስርዓተ ቀብራቸው ስለተፈጸመው አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ።
በስፔን ላሊጋ፦ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ገኖ በወጣበት ግጥሚያ ባርሴሎና ሪያል ማድሪድ በሜዳው የግብ ጎተራ አድርጎ አሸንፎታል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር የመሪነቱን ሥፍራ ከሊቨርፑል ተረክቧል ። ኤሚሬተስ ስታዲየም ውስጥ አርሰናል ሊቨርፑልን ለማሸነፍ ያደረገው ብርቱ ጥረት መክኖበታል ። ሊቨርፑል ወሳኝ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባዬርን ሙይንሽን እና ኤርቤ ላይፕትሲሽ በነጥብ ተስተካክለው በግብ ክፍያ ብቻ ተበላልጠዋል ። ባዬርን ተጋጣሚውን 5 ለ0 ድባቅ ሲመታ፤ ኤርቤ ላይፕትሲሽ 3 ለ1 ድል አድርጓል ። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ሥርዓተ ቀብር ትናንት ተፈጽሟል ።
አትሌቲክስ
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የሩጫ ፉክክሮች፦ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሐዊ ፈይሳ ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸናፊ ሆኑ ። ጥቅምት 17 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ጀርመን ውስጥ በተከናወነው የፍራንክፉርት ማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሀዊ ፈይሳ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸናፊ ሆናለች ። አትሌት ሀዊ በውድድሩ ያሸነፈችው 2:17.25 ሮጣ በመግባት ነው ።
ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻም በስፔን ቫሌንሺያ፤ የግማሽ ማራቶን ውድድር ለድል በቅቷል ። ዮሚፍ ውድድሩን 57:30 ሮጦ ያጠናቀቀበት ጊዜ ቀደም ሲል በጄኮብ ኪፕሊሞ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በ1 ሰከንድ ያሻሻለበት ነው ። ዩጋንዳዊው አትሌት ጄኮብ ኪፕሊሞ ቀደም ሲል ሰብሮት የነበረውን የ57:31 የዓለም ክብረወሰን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2024 የሚደፍረው ጠፍቶ ነበር ። ኢትዮጵያዊው አትሌት አሳክቶታል ። የ23 ዓመቱ ሯጭ ጄኮብ በ2016 ሀገሩን በብራዚል የሪዮ ኦሎምፒክ በ15 ዓመቱ በመወከልም የሚታወቅ አትሌት ነው ።
ከስታዲየም ውጪ የ2024 ምርጥ አትሌቶች እጩዎች ውስጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴትም በወንድም ተካተቱ ። የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፦ በሴቶች ዘርፍ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶችሱቱሜ አሠፋ እና ትእግስት ከተማ ከምስቱ እጩዎች ውስጥ ተካተዋል ። ሌሎቹ ሦስቱ፦ ኬንያውያቱ ሩት ቼፕንጌቲች እና አግነስ ጄቤት እንዲሁም ትውልደ ኢትዮጵያ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሠን ናቸው ።
በወንዶች ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ታምራት ቶላ በእጩነት ተካተዋል ። የዩጋንዳው ጃኮብ ኪፕሊሞ፤ የኬንያው ቤንሶን ኪፕሩቶ እና የኤኳዶሩ ብሪያን ዳንኤል በእጩነት ከቀረቡት አምስት አትሌቶች ውስጥ ይገኛሉ ። በማኅበራዊ መገናኛ አውታር የሚሰጠው የድምፅ አሰጣጥ የፊታችን እሁድ ይጠናቀቃል ።
እግር ኳስ
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ሥርዓተ ቀብር እሁድ የጥቅምት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጸመ ። አሰልጣኝ አሥራት ከረዥም ጊዜ ሕመም በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለፈው ሳምንት አርብ ነበር ። የጥቅምት 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ታላቅ ስፍራ የሚሰጠው አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ የሽኝት መርሐ ግብር ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም መካሄዱም ተዘግቧል ። «ጎራዴው» በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ በይበልጥ በምን ይታወሳሉ? የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ።
የአፍሪቃ ሻምፒዮንሺፕ ማጣሪያ
ለአፍሪቃ ሻምፒዮንስሺፕ ማጣሪያ መሳተፍ የነበረባቸው የምሥራቅ አፍሪቃ ሁለት ሃገራት ከውድድሩ መውጣታቸው ተገለጠ ። በማጣሪያው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥ ለመጋጠም ቀጠሮ ተይዞላት ነበር ። ሆኖም ኤርትራ ባልታወቀ ምክንያት በመውጣቷ ውድድሩ መሰረዙን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። ታንዛኒያ ዳርኤሳላም ውስጥ ልትጫወት የነበረችው ጎረቤት ሶማሊያም በገንዘብ እጦት የተነሳ ከውድድሩ መውጣቷ ተገልጧል ።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሴራሊዮን፤ ጅቡቲ፤ ዚምባብዌ እና ሌሶቶም በፊፋ መስፈርት መሠረት ዓለም አቀፍ ጥራቱን ከጠበቀ ስታዲዮም እጦት የተነሳ በደጋፊዎቻቸው ፊት እና በሜዳቸው መጫወት አይችሉም ። ሌላኛዋ የአፍሪቃ ሻምፒዮንስሺፕ ማጣሪያ ተሳታፊ ሀገር ሱዳን ተጨዋቾች በበኩላቸው በእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳ በሀገራቸው መጫወት አይችሉም ።
በዚህም መሠረት፦ ሱዳን ሞውሪታንያ ናዋክቾት ውስጥ ታንዛኒያን ገጥማ 1 ለ0 አሸንፋለች ። እሁድ ዕለት በነበሩ ሌሎች የአፍሪቃ ሻምፒዮንስሺፕ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታዎች፦ ደቡብ ሱዳን ኬንያን 2 ለ0 ድል አድርጋለች ። ላይቤሪያ በሜዳዋ ፓይኔስቪሌ ውስጥ ሴራሊዮንን ገጥማ 2 ለ1 አሸንፋለች ። ርዋንዳ ኪጋሊ ውስጥ በደጋፊዎቿ ፊት በንዑሷ ጅቡቲ የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዳለች ። ቦትስዋና ፍራንሲስታወን ውስጥ ኂምባብዌን የገጠመችው ሌላኛዋ ንዑስ ሀገር ኤስዋቲኒ 3 ለ0 ማሸነፍ ችላለች ። በቅዳሜ ግጥሚያዎች ደግሞ፦ ደቡብ አፍሪቃ ብሎምፎንታይን ውስጥ ሌሶቶ ናሚቢያን 1 ለ0 አሸንፋለች ። ዐርብ ዕለት ሎሜ ውስጥ የተጋጠሙት ቶጎ እና ቤኒን በቶጎ የ2 ለ0 ድል ተጠናቋል ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ አርሰናል እጅግ የሚያስፈልገውን 3 ነጥብ በገዛ ሜዳው ኤሚረተስ ስታዲየም ደጋፊው ፊት በሊቨርፑል ተነፍጓል ። በምሽቱ ግጥሚያ ቡካዮ ሳካ ሊቨርፑልን አስጭንቋል ። ጨዋታው በተጀመረ 9ኛ ደቂቃ ላይም ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል ። ቪርጂልእ ቫንጃይክ ሊቨርፑልን አቻ የምታደርገዋን ግብ 18ኛው ደቂቃ ላይ በጭንቅላት አስቆጥሯል ። ለራሱ በቡድኑ የመጀመሪያ የሆነችውን ለአርሰናል ደግሞ የማሸነፊያ የመሰለችውን ግብ ሚኬል ሞሪኖ በ43ኛ ደቂቃ ላይ እሱም በጭንቅላት ከመረብ አሳርፏል ። የጥቅምት 04 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የፍፁም ቅጣት ምቱን እጅግ ድንቅ በሆነ ሁኔታ በሊቨርፑል ተከላካዮች አናት አሳልፎ ለሚኬል ያደረሰው ዴክላን ራይስ ነው ። ግሩም ቅጣት ምት ነበረች ። ሊቨርፑልን አቻ አድርጎት የነበረው ተከላካዪ ቪርጂል ቫንጃይክ ትንሽ ጭንቅላቱን ከፍ አድርጎ ቢዘል ኳሷ ትጨናገፍ ነበር ። የሆነ ሆኖ አርሰናል እጅግ የቋመጠለትን 3 ነጥብ የማግኘት ሕልም ሞሐመድ ሳላህ 81ኛ ደቂቃ ላይ አምክኖታል ። የአሌክሳንደር አርኖልድ ኳስ መጥኖ ወደፊት መላኩ፥ የዳርዊን ኑኔዝ እኔ ግቡን ካላስቆጠርሁ ብሎ አለመንገብገቡ፥ እንዲሁም የሳላህ አድብቶ ግብ የማስቆጠር ብቃቱ ቅንብር ድንቅ ነበር ።
ቀደም ብሎ በዳርዊን ኑኔዝ ጉሸማ የደረሰበት ጋብሬል ማጋላሄስ ሁለት ጊዜ ሜዳ ላይ ወድቆ መቀየሩ የአርሰናል ተከላካይ መስመር ላይ ብርቱ ክፍተት መፍጠሩ ይታይ ነበር ።
ትናንት በነበረ ሌላ ግጥሚያ፦ ማንቸስተር ዩናይትድ የጨዋታው መደበኛ ዘጠና ደቂቃ ሲጠናቀቅ በተቆጠረበት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በዌስት ሀም ዩናይትድ 2 ለ1 ተሸንፏል ። ዘንድሮ መላ የጠፋው ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት አራተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል ። በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ 14ኛ ላይም በ11 ነጥቡ ተወስኗል ። ቶትንሀም በክሪስታል ፓላስ 1 ለ0 ሲሸነፍ ፥ ቸልሲ ኒውካስል ዩናይትድን 2 ለ1 ረትቷል ።
በዚህም ነጥቡን 17 አድርሶ በደረጃ ሰንጠረዡ 5ኛ ላይ መገኘት ችሏል ። ከአስቶን ቪላም ሆነ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አርሰና በአንድ ነጥብ ነው የሚበለጠው ። ሊቨርፑል በ22 ነጥብ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲንሸራተት ። ቅዳሜ ዕለት በመከራ ሳውዝሐምፕተንን ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል በአንድ ነጥብ በልጦ አንደኛ ደረጃ ላይ መስፈር ችሏል ። ቅዳሜ ዕለት፦ብራይተን ከዎልቭስ ሁለት እኩል፤ እንዲሁም ኤቬርተን ከፉልሀም ብሎም አስቶን ቪላ ከበርመስ ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ዐርብ ዕለት ላይስተር ሲቲ በኖቲንግሐም ፎረስት የ3 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ኢፕስዊች ታውን፤ ዎልቭስ እና ሳውዝሐምፕተን ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል ።
ቡንደስሊጋ
በቡንደስሊጋው ትናንት ቦሑምን በገዛ ሜዳው 5 ለ0 ያደባየው ባዬርን ሙይንሽን የደረጃ ሰንዘረዡን በ20 ነጥብ ይመራል ። ተመሳሳይ 20 ነጥብ ያለው ኤርቤ ላይፕትሱሽ በሁለተነት ይከተላል ። ቅዳሜ ዕለት ፍራይቡርግን 3 ለ1 ማሸነፍ ችሏል ። ባዬርን ሙይንሽን ትናት ሚካኤል ዖሊሴ፤ ጃማል ሙሳይላ፤ ሐሪ ኬን፤ ሌሮይ ሳኔ እና ኪንግስሌይ ኮማን ግቦቹን አስቆጥረዋል ። በ15 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዑኒዮን ቤርሊን እና በ14 ነጥቡ ስድተኛ ላይ የሰፈረው አይንትራኅት ፍራንክፉርት አንድ እኩል ተለያይተዋል ።
በቅዳሜ ጨዋታዎች፦ ከቬርደር ብሬመን ጋር ሁለት እኩል የተለያየው ባዬርን ሌቨርኩሰን 15 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሳንክት ፓውሊ ከቮልፍስቡርግ ጋር ዜሮ ለዜሮ፤ ማይንትስ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል ። ከሁለቱም ቡድኖች ቀይ ካርድ በታየበት ግጥሚያ ሽቱትጋርት ሆልሽታይን ኪይልን 2 ለ1 ሸኝቷል ።
በአውግስቡርግ የ2 ለ1 ሽንፈት የደረሰበት ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ13 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 9ኛ ደቂቃ ላይ የቦሩስያ ዶርትሙንድ የተከላካይ መስመር የግራ ተመላላሹ አልሙጌራ ካባራ ቀይ ካርድ ዐይቷል ። የ18 ዓመቱ ተጨዋች በቡንደስሊጋ የመጀመሪያ ጨዋታው ሁለት ጊዜ ቢጫ ተሰጥቶት ነው በጨዋታ ፍጻሜ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው ። ሳንክት ፓውሊ፤ ሆልሽታይን ኪይል እና ቦሁም በደረጃ ሰንጠረዡ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ ተደርድረዋል ።
ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ፦ ሮቤርት ሌቫንዶብስኪ ሁለት ግቦችን ባስቆጠረበት ግጥሚያ ባርሴሎና ዋነኛ ተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድን 4 ለ0 ጉድ አድርጓል ። ሁለቱ ቀሪ ግቦች የላሚኔ ያማል እና የራፊና ነበሩ ። በቅዳሜው ግጥሚያ ድል ያደረገው ባርሴሎና ላሊጋውን በ30 ነጥብ ይመራል። ሽንፈት የደረሰበት የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድሉ ሪያል ማድሪድ በ24 ይከተላል ። ቪላሪያል በ21 እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ በ20 ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። የመስከረም 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በተያያዘ ዜና የዓለም ምርጥ ተጨዋች በሚመረጥበት የባሎን ዲዖር ምርጭ ከ21 ዓመታት ወዲህ ዘንድሮ ሊዮኔል ሜሲም ሆነ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእጩነት ውጪ ሆኑ ። ዛሬ ማታ በሚከናወነው ምርጫ ሊዮኔል ሜሲን የሚተካ የዓለማችን ምርጡ ተጨዋች ይፋ ይሆናል ። እድሉ አላቸው ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ተጨዋቾች መካከል የሪያል ማድሪዶቹ፦ ቪንሺየስ ጁኒየር እና ጁድ ቤሊንግሀም ይገኙበታል ። በስፔን ቡድን ለዘንድሮ የአውሮጳ ዋንጫ ድል የበቃው የማንቸስተር ሲቲው ሮድሪም ዛሬ ማታ የዓለማችን ምርጥ ተብለው ከሚሰየሙ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር