1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 21 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 2015

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች በተከናወኑ የማራቶን ሩጫዎች ድል ተቀዳጅተዋል። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች ለሴካፋ ውድድር ወደ ሱዳን አቅንተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል የመሪነት ፉክክራቸውን በቅርብ ርቀት ተያይዘውታል።

UEFA Champions League | RB Leipzig vs. Celtic Glasgow
ምስል Lisi Niesner/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች በተከናወኑ የማራቶን ሩጫዎች ድል ተቀዳጅተዋል። ኬንያውያን አትሌቶችም ብርቱ ፉክክር ዐሳይተው ለድል በቅተዋል። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች ለሴካፋ ውድድር ወደ ሱዳን አቅንተዋል። ከነገ በስትያ ታንዛኒያን ይገጥማል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል የመሪነት ፉክክራቸውን በቅርብ ርቀት ተያይዘውታል። ትናንት አርሰናል የበላይነቱን ባሳየበት ጨዋታ ተጋጣሚው ኖቲንግሀም ፎረስትን አንኮታኩቷል። ሊቨርፑልን ባለፈው ግጥሚያ በአንፊልድ ሜዳው ጉድ ያደረገው ኖቲንግሀም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል። ሊቨርፑል በዚህ ሳምንት ግጥሚያም በሜዳው ሽንፈት አስተናግዶ የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞታል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየርን ሙይንሽን ተጋጣሚውን የግብ ጎተራ ቢያደርግም ዑኒዮን ቤርሊን የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ እንደተቆናጠጠ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽንፈት ገጥሞታል። 

አትሌቲክስ

ትናንት 25,000 ሰዎች በተሳተፉበት የደብሊን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ንግሥት ሙሉነህ በአንደኛነት በማሸነፍ ለድል በቅታለች። በወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያዊው አሸናፊ ቦጃን በ2 ደቂቃ ከ29 ሰከንዶች የበለጠው የሞሮኮው ሯጭ ቶፊቅ አላም ድል ቀንቶታል። ቶፊቅ አየርላንድ ደብሊን ውስጥ በተከናወነው የ42 ኪሎ ሜትር የማራቶን ሩጫ ለአሸናፊነት የበቃው 2 ሰአት ከ11 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሯጭ ብርሃኑ ተሾመ 2:14.2 በመሮጥ የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

የሚሮጥ እግር ከበቅርበት ሶሉ ዕየታየምስል Colourbox

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ንግሥት ሙሉነህ አንደኛ የወጣችው ውድድሯን 2:28.32 ሮጣ በማጠናቀቅ ነው። ብርቱ ፉክክር በታየበት የሴቶች ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሐዊ ዓለሙ ለጥቂት በአንድ ደቂቃ ከ4 ሰከንድ ተበልጣ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። የሦስተኛ ደረጃው በ23 ዓመቷ አየርላናዳዊት ሯጭ ማክ ጉዌር ነው የተያዘው። የደብሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ከኮሮና ወረርሺኝ በኋላ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ተቋርጦ ነበር።

ፍራንክፉርት ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሦስተኛ እና የአራተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በፍራንክፉርቱ የማራቶን ፉክክር በወንድም በሴትም ኬንያውያን ድል ተቀዳጅተዋል። ኬንያዊው ሯጭ ብሪሚን ኪፕኮሪር 2 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመሮጥ የአንደኛ ደረጃ አግኝቷል። የሀገሩ ልጅ ሳሙኤል ንያማይ 1 ደቂቃ ከ8 ሰከንድ ዘግይቶ በመከተል የ2ኛ ደረጃውን ይዟል። ኢትዮጵያዊው ሯጭ ደረሰ ገለታ ከኬንያዊው ለጥቂት በ11 ሰከንዶች ብቻ ተበልጦ ሦስተኛ ወጥቷል።

በሴቶች የፍራንክፉርት የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኬንያዊቷ ሴሊ ቼፕዬጎ 2:23:11 በመሮጥ ለድል በቅታለች። ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃውንም ኬናያውያቱ ተቆጣጥረውታል። ሔላ ዬላጋት 2:24:40 በመሮጥ የሁለተኛውን ደረጃ ስትይዝ፤ 2:25:14 የሮጠችው ጃክሊን ቼፕንጌኖ በሦስተኛነት አጠናቃለች።  ኢትዮጵያዊቱ መሠረት አበባየሁ የ7ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የፍራንክፉርት ማራቶን ላይ ከ11.000 በላይ ሰዎች ትናንት ተሳትፈዋል።

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤት(CECAFA) ዞን ሃገራት ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ውድድራቸውን ሱዳን ውስጥ እያከናወኑ ነው። የማጣሪያ ውድድሩ በሱዳን አዘጋጅነት ካለፈው ዓርብ የጀመረ ሲሆን፤ እስከሚቀጥለው ዓርብ ሳምንት ድረስ ሊከናወንም መርሐግብር ተይዞለታል።

የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤት (CECAFA)ምስል EBRAHIM HAMID/AFP/Getty Images

በዚህም መሰረት የማጣሪያ ፉክክሩ ዓርብ ምሽት በጅቡቲ እና ቡሩንዲ ጨዋታ ተከፍቷል። በዚሁ ውድድር ቡሩንዲ ጅቡቲን 5 ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ድል አድርጋለች። ቡሩንዲ የፊታችን ቅዳሜ በምድብ «ለ» የምትገኘው እና ያለፈውን ዋንጫ የወሰደችው ኡጋንዳን ትገጥማለች። አዘጋጇ ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋር ትናንት ያደረገችው ጨዋታ ያለምንም ግብ ተቀጠናቋል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድሩን ለማከናወን ትናንት ወደ ሱዳን አቅንቷል።  እኩለ ቀን ላይም ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ ልምምዱን ወዲያው ማከናወኑ ታውቋል። የኢትዮጵያ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን ከታንዛንያ ጋር ከነገ በስትያ (ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን፣ 2015 ዓም) ያከናውናል። ቡድናችን መልካም ውጤት እንዲገጥመው ከወዲሁ እንመኛለን።

ፕሬሚየር ሊግ

ትናንት ኖቲንግሀም ፎረስትን 5 ለ0 ድባቅ የመታው አርሰናል የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግን በ31 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን 1 ለ0 በማሸነፉ ነጥቡን 29 አድርሶ አርሰናልን በቅርብ ርቀት ይከተላል። አንድ አንድ ተጨማሪ ጨዋታዎችን ያደረጉት ቶትንሀም እና ኒውካስል ዩናይትድ በ26 እና 24 ነጥብ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ዌስትሀም ዩናይትድ 1 ለ0 በመሸኘት ነጥቡን 23 ማድረስ ችሏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከኒውካስል የሚበለጠው በ1 ነጥብ ብቻ ነው። ቅዳሜ ዕለት በብራይተን የ4 ለ1 ብርቱ ሽንፈት የገጠመው ቸልሲ 21 ነጥብ አለው፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 6ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። አንድ ተጨማሪ ጨዋታ ያደረገው ፉልሀም በ19 ነጥብ ደረጃው 7ኛ ነው። ብራይተን እና ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው 8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በተለይ የሊቨርፑል ዘንድሮ እጅግ ማሽቆልቆል አሰልጣኙ ላይ ብርቱ ትችት አስከትሏል።

ምስል Andreas Gora/dpa/picture alliance

ሆኖም አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ቡድናቸው እያሽቆለቆለ ነው መባሉን «መቶ በመቶ ተገቢ አባባል አይደለም» ሲሉ አጣጥለውታል። በሜዳው ጭምር ተደጋጋሚ ሽንፈት ስለገጠመው ቡድናቸው ሲከራከሩም ለሽንፈታቸው በዋናነት የበርካታ ተጨዋቾቻቸው መጎዳት መሆኑን ጠቁመዋል። ከፍ እና ዝቅ ማለት ያለ እንደሆነ የገለጡት አሰልጣኙ «የውድድሩ ዘመኑ ማብቂቂያ ላይ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲን ማየት ነው» ብለዋል። ውድድሩ ቀጥሎ ወደፊት መሀል ላይ አለያም በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ ሁሉንም ብንመለከት ይሻላል ሲሉ ያልተጠበቁ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

በአንጻሩ በሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ወደ ጥሎ ማለፍ ያለፈው ሊቨርፑል ዘንድሮ የተሻለ አቋም ዕያሳየ ይገኛል። ሆኖም መሪው ናፖሊን ጥሎ ለማለፍ ግን ሊቨርፑል በነገው ምሽት ከአራት ግብ በላይ ማስቆጠር ይጠበቅበታል። ሊቨርፑል ነገ ማታ በሜዳው አንፊልድ በሚያደርገው ጨዋታ ናፖሊን ካሸነፈ በነጥብ እኩል 15 ይሆናል።

«አልፈራም አለያም ስጋት አይውጠኝም» ብለዋል ዬርገን ክሎፕ ስለነገው ወሳኝ ጨዋታ ተጠይቀው ሲመልሱ። «ከባድ ውድድር ነው ግን አደንቃቸዋለሁ» ሲሉም አክለዋል ተጋጣሚዎቻቸው የናፖሊ ተጨዋቾችን። ናፖሊ በሻምፒዮንስ ሊግ ምድብ «ሀ» 16 የግብ ክፍያዎች ይዞ የምድቡ መሪ ነው።  ሊቨርፑል ከ12 ነጥብ ጋር 9 የግብ ክፍያዎች አሉት። በዚያ ላይ ናፖሊ በጣሊያን ሴሪዓ አታላንታን በአምስት ነጥብ ርቆ በ32 ነጥብ እየመራ የሚገኝ ብርቱ ቡድን ነው። ዬርገን ክሎፕ ስለ ነገ ማታው ጨዋታ አክለው ሲናገሩ፦ «አሁን የእኛ ሁኔታ ከናፖሊ ትንሽ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው፤ በማሸነፍ ጎዳና ላይ ከሆንክ በዚያው ለመቀጠል እጅግ ብዙ ማድረግ ይጠበቅብሀል »ብለዋል።

ከሊቨርፑል እና ናፖሊ በተጨማሪ ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት ሌሎች አራት ግጥሚያዎች ይደረጋሉ። ከነገ ወዲያን ጨምሮም አምስት የጀርመን ቡድኖች በጥሎ ማለፉ ውድድር ተሳታፊ ናቸው። በነገው ዕለት አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝቦን ጋር ይጋጠማል። ሁለቱም 7 ነጥብ ሲኖራቸው ምድባቸውን የእንግሊዙ ቶትንሀም በ8 ነጥብ ይመራል። ከዚህ ምድብ ለማለፍ የሚደረገው ፉክክር እጅግ አጓጊ ነው።  በ4 ነጥብ ተወስኖ በምድቡ መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰን በ10 ነጥብ የሚመራው የቤልጂየሙ ክሉብ ብሩዥን ያስተናግዳል።

ማንቸስተር ሲቲ ሰማያዊ ለብሶ ጫ ከለበሰው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ሜዳ ውስጥምስል Sascha Schürmann/AFP/Getty Images

የስፔኑ ባርሴሎና ቪክቶሪያ ፒልስሰን ለመግጠው ወደ ቼክ ሪፐብሊክ አቅንቷል። በምድብ «ሐ» ከኢንተር ሚላን በታች 4 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው። ምድቡን ከኢንተር ሚላን በ5 ነጥብ የሚበልጠው የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን ምድቡን በ15 ነጥብ ይመራል። ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን ያረጋገጠው ባየር ሙይንሽንም የጣሊያኑ ኢንተር ሚላንን የሚገጥመው ነገ ማታ ነው።  

ከነገ ወዲያ ማታ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የዴንማርኩ ኮፐንሀግንን በሜዳው ፓርከን ስታዲየም ውስጥ ይጋጠማል። ማንቸስተር ሲቲ ከሴቪያ፣ ቸልሲ ከዲናሞ ኪዬቭ፣ ጁቬንቱስ ከፓሪ ሳንጃርሞ፣ ኤስ ሚላን ከኤር ቤ ዛልስቡርግ፣ ላይፕትሲሽ ከዶኒዬትስክ፣ የፖርቹጋሉ ቤኔፊካ ከእሥራኤሉ ማካቢ ሐይፋ፤ እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ከሴልቲክ ጋር የሚጋጠሙት ረቡዕ ማታ ነው።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ 26 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው ዑኒዬን ቤርሊን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን ትናንት 2 ለ1 ድል አድርጓል። ቅዳሜ ዕለት ማይንትስን 6 ለ2 የግብ ጎተራ ያደረገው ባየርን ሙይንሽን በ25 ነጥብ ይከተላል። ፍራይቡርግ 24 ነጥብ አለው 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ሻልከን በሜዳው 2 ለ0 አሸንፎታል። ሻልከ 6 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 18ኛ ላይ ይገኛል።

የመኪና ሽቅድምድም

የፎርሙላ አንድ ተሽከርካሪ ምስል ከማኅደርምስል Charlie Neibergall/AP Photo/picture alliance

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን ትናንትም ድል ቀንቶታል። የትናንቱ የሜክሲኮ ሲቲ ሽቅድምድምንም ያሸነፈው ማክስ እስከ አሁን አጠቃላይ ነጥቡ 416 ደርሷል። በ280 ነጥብ የሚከተለው ሌላኛው የሬድ ቡል ባልደረባው ሠርጂዮ ፔሬዝ ትናንትም 2ኛ ደረጃን አግኝቷል። የፌራሪው አሽከርካሪ ሻርል ሌክሌር 275 ነጥብ ይዞ በ3ኛ ደረጃ ይከተላል። ጆርጅ ሩሴል በ231 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በትናንቱ ፉክክር የ2ኛ ደረጃን የያዘው የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በ216 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW