የጥቅምት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥቅምት 25 2017የ58 ዓመቱ የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ማይክ ታይሰን የልጅ ልጁ ከሚሆነው ሌላ የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ጋር ሊፋለም የተያዘለት ቀጠሮ እየተቃረበ ነው ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ሽንፈት አስተናግደዋል ። በኮዲ ጋክቦ እና ሞ ሳላኅ ግቦች ለድል የበቃው ሊቨርፑል የደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን ዳግም ተረክቧል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬር ሙይንሽን ድል ሲቀናው፥ ኤርቤ ላይፕትሲሽ በቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽንፈት ገጥሞታል ። ነገ እና ከነገ በስትያ 16 የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።
እግር ኳስ
ቅዳሜ ዕለት ብራይተን አልቪዮንን ከኋላ ተነስቶ በሁለት ደቂቃ ልዩነቶች ሁለት ግቦች በማስቆጠር 2 ለ1 ያሸነፈው ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ዳግም የበላይነቱን ተቀዳጅቷል ። የዋነኛ ተፎካካሪዎቹ የማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል መሸነፍ ለሊቨርፑል መልካም አጋጣሚ ነበር ። በቅዳሜው ግጥሚያ ብራይተኖች ለማሸነፍ ብርቱ ትግል በማሳየት ሊቨርፑልን ፈትነውት ነበር ። በኮዲ ጋክፖ እና ሞሐመድ ሳላኅ በ70 እና 72ኛ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠሩ ግቦች ያሸነፈው ሊቨርፑል ነጥቡን 25 ማድረስ ችሏል ።
ፕሬሚየር ሊግ
በበርመስ ሜዳ የ2 ለ1 ሽንፈት ያስተናገደው ማንቸስተር ሲቲ በ23 ነጥቡ ወደ ሁለተኛነት ዳግም ተንሸራቷል ። ማንቸስተር ሲቲን ከ2 ለ0 ሽንፈት የታደገውን ግብ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ተከላካዩ ጆስኮ ግቫርዲዮል ነው ። ቅዳሜ ለአርሰናል ደጋፊዎችም አስደንጋጭ ቀን ነበር ። ባለፈው ሳምንት ከሊቨርፑል ጋር በገዛ ሜዳው ሁለት እኩል ለመለያየት የተገደደው አርሰናል በኒውካስል የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዶ ተመልሷል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ ማጠናቀቂያ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ዌስትሐም ዩናይትድን 3 ለ0 የረታው ኖቲንግሀም ፎረስት በ19 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃውን ተቆጣጥሯል ። ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ዖልድ ትራፎርድ ሜዳ ሄዶ የተጋጠመው ቸልሲ ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል ። ቸልሲ እንደ አርሰናል 18 ነጥብ ሰብስቦ በግብ ክፍያ በመብለጥ ግን አርሰናልን አስከትሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። የጥቅምት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 19ኛ ላይ የሚገኘው ሳውዝሐምፕተን በዐሥር ግጥሚያዎች የመጀመሪያ ድሉን ኤቨርተንን 1 ለ0 በማሸነፍ ቅዳሜ አጣጥሟል ። 4 ነጥብ አለው ። ከስሩ ዎልቨርሀምፕተን በ3 ነጥብ ብቻ 20ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ከበላዩ ኢፕስዊች ታውን በ5፤ ክሪስታል ፓላስ በ7 እንዲሁም ኤቨርተን በ9 ነጥብ ከ18ኛ እስከ 16ኛ ተኮልኩለዋል ።
የጀርመን ቡንደስሊጋ
ቅዳሜ ዕለት ዑኒዮን ቤርሊንን 3 ለ0 የረታው ባዬርን ሙይንሽን ቡንደስሊጋውን በ23 ነጥብ ይመራል ። በቦሩስያ ዶርትሙንድ የ2 ለ1 ሽንፈት የገጠመው ኤር ቤ ላይፕትሲሽ በ20 ነጥብ ይከተላል ። ቦሁምን 7 ለ2 የግብ ጎተራ አድርጎ የሸኘው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ17 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ባዬር ሌቨርኩሰን፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ፍራይቡርግ በእኩል 16 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ተደርድረዋል ። ቬርደር ብሬመንን ትናንት 4 ለ1 የረታው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ13 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሆፈንሀይም፤ ሆልሽታይን ኪዪል እና በ9 ግጥሚያዎች 1 ነጥብ ብቻ ያለው ቦሁም ወራጅ ቀጣናው ላይ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ተደርድረዋል ።
የስፔን ላሊጋ
የስፔን ላሊጋ ኮከብ ግብ አግቢነትን የባርሴሎናው አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በ14 ግቦች ይመራል ። የቪላሪያሉ አዮዝ ፔሬዝ እና ሌላኛው የባርሴሎና አጥቂ ራፊና በ7 ግቦች ይከተላሉ ። የሪያል ማድሪዱ ኪሊያን ምባፔ እና የዖሳሱናው ቡድሚር 6 ግቦች አላቸው ። የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ቪንሺየስ ጁኒየር ከሌሎች አራት ተጨዋቾች ጋር በ5 ግብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።
በነገራችን ላይ ቪንሺየስ ጁኒየር ባለፈው ሳምንት ሰኞ በተደረገው የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች ምርጫ አለማሸነፉ አወዛግቧል ። ያም ብቻ አይደለም፦ በርካቶች ከአፍሪቃዊ ቆዳ ቀለሙ ጋር አያይዘው በደል እንደተፈጸመበት ተናግረዋል ። አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ለስምንት ጊዜያት ወደ ሀገሩ የወሰደው የባሎን ደ ዖር (Ballon d'Or) ዋንጫ ዘንድሮ ያሸንፋል ተብሎ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ለቪንሺየስ ጁኒዬር ነበር ። ሆኖም የዘንድሮ የባሎን ደ ዖር ዋንጫ የተሰጠው ለሮድሪ ነው ።
የባሎን ደ ዖር (Ballon d'Or) ዋንጫ
ያሸንፋሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል የሪያል ማድሪድ አጥቂዎች ቪንሺየስ ጁኒየር እና ጁድ ቤሊንግሀም በዘንድሮው የሽልማትሥነ ሥርዓት ላይ አልተገኙም ። ምክንያት ደግሞ ዋንጫውን ቪንሺየስ ጁኒየር ሳይሆን ሮድሪ እንደሚያሸንፍ ቀድሞ በመታወቁ ነው ። በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ እጩ የነበሩት የቪንሺየስ ጁኒየር የቡድን አባላት፦ ጁድ ቤሊንግሀም፤ ዳኒ ካርቫሀል፤ ኬሊያን እምባፔ፤ አንቶኒዮ ሩዲገር እንዲሁም ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ አልታደሙም ። የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲም በፓሪሱ የሽልማት ስነስርዓት አልተገኙም ። የሪያል ማድሪድ ፕሬዚደንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ በሽልማቱ ቀን እዛው እቤታቸው ቀርተዋል ። የ2024 ኮፓ ዋንቻ አሸናፊው የ19 ዓመቱ ቱርካዊው አማካይ አርዳ ጉይለርም ከማድሪድ አልወጣም ። በአጠቃላይ ማለት ይቻላል ሪያል ማድሪድ በሽልማቱ አልተደሰተም ። የጥቅምት 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የዘንድሮ የባሎን ደ ኦር ዋንጫ አሸናፊ ሮድሪ ቡድኑ ማንቸስተር ሲቲን በፕሬሚየር ሊግ እንዲሁም ብሔራዊ ቡድኑ ስፔንን ለዩሮ 2024 ዋንጫ አብቅቷል ። ሆኖም ሪያል ማድሪድን በላሊጋው ዋንጫ፤ በሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ፤ እንዲሁም በስፔን ሱፐር ሊግ ዋንጫ ለድል ያበቃው ቪንሺየስ ጁኒየር አሸናፊ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ሳይታለም የተፈታ ነበር ። ከሽልማቱ ቀደም ብሎ በነበረው የጨዋታ ዘመን 39 ጊዜ ወደ ሜዳ ብቅ ብሎ 24 ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል ። 11 ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን አመቻችቷል ። ያም ብቻ አይደለም ። የ24 ዓመቱ አጥቂ በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ በሁለት ፍጻሜዎች ላይ ግቦችን በማስቆጠርም ለረዥም ጊዜ በሊዮኔል ሜሲ ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን መስበር የቻለም ነው ።
እናስ የባሎን ደ ዖር ዋንጫ ለምን አልተሰጠውም? የብዙዎች ጥያቄ ነው ። ራሱ ቪንሺየስ ጁኒዬር በሽልማቱ ወቅት በኤክስ መገናኛ አውታሩ የጻፈው አጭር መልእክት ብዙ ይናገራል ። «ማድረግ የግድ ከሆነ 10 ጊዜ ማድረግ እችላለሁ ። እነሱ ዝግጁ አይደሉም» ሲል ይነበባል ። ቪንሺየስ ጁኒዬር በጨዋታ ወቅት ስታዲየም ውስጥ ከተመልካቾች ብዙ ጊዜ የዘረኝነት ስድብ ይገጥመዋል ። እንደ ጦጣ እየጮሁ አፍሪቃዊ የቆዳ ቀለሙ ላይ በተደጋጋሚ ይሳለቃሉ ። የዘረኝነት ምስሎችን በየአደባባዩ እየሰቀሉ ሊያሸማቅቁትም ይሞክራሉ ። በየጊዜው ግን ሁሉን ችሎ በብቃቱ ከፍ እያለ መምጣቱም እጅግ የሚያንገበግባቸው ጥቂት አይደሉም ። ምክንያቱ ደግሞ ደረቅ ዘረኝነት ።
ሻምፒዮንስ ሊግ
ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊጉ ነገ ኤሲ ሚላንን ይገጥማል ። ቪንሺየስ ጁኒዬር በነገው ግጥሚያ እንደተለመደው ማበቡ የማይቀር ነው ። በነገው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ፦ የጀርመኖቹ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ኤርቤ ላይፕትሲሽ ስቱርም ግራዝ እና ሴልቲክን ይገጥማሉ ። ቦሎኛ ከሞናኮ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከስፖርቲንግ እንዲሁም ሊቨርፑል ከባዬርን ሌቨርኩሰን የሚጋጠሙት በነገው ዕለት ነው ። ረቡዕ ዕለት ከሚኖሩ ግጥሚያዎች መካከል፦ ባዬርን ሙይንሽን ከቤኔፊካ፤ አርሰናል ከኢንተር ሚላን እንዲሁም ፓሪስ ሳንጃርሞ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚያደርጓቸው ይጠቀሳሉ ። በአጠቃላይ ነገ እና ረቡዕ 16 የሻምፒዮን ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።
የብስክሌት ሽቅድምድ
ጃፓን ውስጥ በተከናወነው የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢንያም ግርማይ ቅዳሜ አሸናፊ ሁኗል ። በጃፓን ውድድር ከአፍሪቃ ተፎካካሪ ለድል ሲበቃ ቢንያም የመጀመሪያው ነው ። ቢንያምን ተከትለው የ35 ዓመቱ ስሎቬንያዊ ፕሪሞዝ ሮግሊሽ እና የ39 ዓመቱ ብሪታኒያዊው ብስክሌተኛ ማርክ ካቬንዲሽ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። የጥቅምት 04 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የከባድ ሚዛን ቡጢ
የ58 ዓመቱ ጡረተኛ ቡጢኛ ማይክ ታይሰን ከእድሜው በግማሽ የሚያንሰውን የ27 ዓመቱን ጄክ ፖል ሊገጥም ነው ። የቡጢ ውድድሩ ኔትፍሊክስ በተሰኘው የመዝናኛ ዓለም አቀፍ ድረ ገጽ የፊታችን ዓርብ ሳምንት ማታ በቀጥታ ይተላለፋል ተብሏል ። ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ አርሊንግተን ቴክሳስ ከሚገኘው የAT&T ስታዲየም በቀጥታ በኔትፍሊክስ ብቻ ይተላለፋል ተብሏል ። የቴሌቪዥን ሥርጭት ላይ ውድድሩ እንደማይታይም ተገልጧል ። ውድድሩ ሐምሌ ወር ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ ነበር ። ሆኖም ማይክ ታይሰን የጨጓራ ቁስለት ገጥሞት በመታከሙ ውድድሩ ለወራት ተራዝሞ ቆይቷል ።
ማይክ ታይሰን ከሁለት ዐሥርተ ዓመት በፊት መቧቀሻውን እስከሰቀለበት ጊዜ ድረስ 50 ጊዜ 44ቱን በዝረራ ማሸነፍ የቻለ ቡጢኛ ነው ። በውድድር ዘመኑ ሁሉ የተሸነፈው ለ6 ጊዜ ብቻ ነው ። እናም የማይክ ታይሰን የአፍላ ዘመን ብርቱ ተፋላሚነትን የሚያስታውሱ ደጋፊዎቹ በዐርቡ ግጥሚያ ያሸንፋል ሲሉ ተንብየዋል ። ብዙዎች ግን እስካሁን ባደረጋቸው 10 ውድድሮች ሰባቱን በዝረራ አሸንፎ በአንዱ ብቻ የተሸነፈው የቀድሞው የዩቲዩበር እና ማኅበራዊ መገናና አውታር ዝነኛ ማሸነፉ አይቀርም ብለዋል ። ማይክ ታይሰን ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ከተፋለመ ሃያ ዓመት ሊሞላ ነው ።
እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘወርበት ይህን ልዩ የቡጢ ፍልሚያ ለመታደም ከትንሹ 37 ዶላር እስከ ከፍተኛው የ2 ሚሊዮን ዶላር ቲኬት ተሰናድቷል ። በቡጢ መፋለሚያ መድረኩ የተወጠሩ ገመዶች አቅራቢያ በተዘጋጁ ሁለት ልዩ የግል መመልከቻዎች ተቀምጠው መመልከት የሚሹ ባለጸጎች የሁለት ሚሊዮን ዶላር ቲኬት መግዛት ይኖርባቸዋል ተብሏል ። የውድድር ስፍራው 80,000 ታዳሚዎችን ማስተናገድ ይችላልም ተብሏል።
በብዙዎች ዘንድ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን ግጥሚያ የቡጢ ፍልሚያ አሰናጁ ኤዲ ሔርን፦ «እጅግ አደገኛ፤ ኃላፊነት የጎደለው» እና «ለቡጢ ስፖርት ክብር የነሳ ድርጊት» ሲል በብርቱ ተችቷል ። ምናልባትም ዝግጅቱ በእንባ የሚጠናቀቅ ይሆናል ሲልም አደገኛነቱን ጠቁሟል ። የ58 ዓመቱ ከ27 ዓመቱ ቡጢኛ ጋር ልፋለም ማለቱ ግን ምን ይባል ይሆን?
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ