1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 28 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 28 2015

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከኒውዮርክ እስከ ደቡብ አፍሪቃ ስዌቶ በተለያዩ መድረኮች አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መድፈኞቹ ወደ ስታምፎርድ ብሩጅ አቅንተው ቸልሲን ጉድ አድርገዋል። ባለፈው ናፖሊ ላይ ድል የተቀዳጀው ሊቨርፑል ቶትንሀም ሆትስፐርን በሜዳው ጉድ አድርጎ የማሸነፍ ስሜቱን አነቃቅቷል።

WM 2022 in Katar I Al Thumama Stadium
ምስል Hussein Sayed/AP/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከኒውዮርክ እስከ ደቡብ አፍሪቃ ስዌቶ በተለያዩ መድረኮች አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መድፈኞቹ ወደ ስታምፎርድ ብሩጅ አቅንተው ቸልሲን ጉድ አድርገዋል። ባለፈው ናፖሊ ላይ ድል የተቀዳጀው ሊቨርፑል ቶትንሀም ሆትስፐርን በሜዳው ጉድ አድርጎ የማሸነፍ ስሜቱን አነቃቅቷል። የዓለም ዋንጫ ኳታር ውስጥ ሊከናወን 12 ቀናት ይቀሩታል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞው ተጨዋች ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ፈረንሳይን የሚስተካከል የለም ብሏል፤ ግን ደግሞ አንድ ወሳኝ ተጨዋቿን ካሰለፈች ብቻ መሆኑንንም አስረግጧል።

አትሌቲክስ

በሳምንቱ መገባደጂያ ላይ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተደረጉ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥንካሬያቸውን በማሳየት ለድል በቅተዋል። በቱርክ ኢንስታንቡል የማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ተከታትለው በመግባት አስደምመዋል።  በዚሁ ፉክክር ሲጫሌ ደለሳ 2:25:54 በመሮጥ የ1ኛ ደረጃን አግኝታለች። 2:29:01 የሮጠችው አትሌት መሠለች ጸጋዬ የ2ኛ ደረጃን እንዲሁም እታለማሁ ስንታየሁ 2:31:38 በመሮጥ የ3ኛ ደረጃን አግኝተዋል። በወንዶች የኢስታንቡል ፉክክር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ማግኘት አልቻሉም።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተደረገው የኒውዮርክ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ግን በወንዶች ሹራ ቂጣታ 2:08:54 በመሮጥ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር 2:23:39 የሮጠችው ጎቲቶም ገ/ስላሴ የ3ኛ ደረጃን ይዛለች። በፖርቹጋል-ፖርቶ ማራቶን 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ በአብራራው ምስጋናው እና ሃይማኖት አለው ተይዟል።  

የቤርሊን ማራቶን ሩቻ ፉክክር በ2021 ፎቶ ከማኅደርምስል Annegret Hilse/REUTERS

በደቡብ አፍሪቃ ስዌቶ ማራቶንም ድሉ የኢትዮጵያውያን ኾኗል። በወንዶች ፉክክር ዳባ ኢፋ 2:18:58 በመሮጥ 1ኛ፤ ጋዲሳ በቀለ 2:19:27 ሮጦ በመግባት የ2ኛ ደረጃ አግኝቷል። በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በኢትዮጵያውያቱ ተይዟል። በዚህም መሰረት ጫልቱ በዶ 2:40:56 በመሮጥ 1ኛ፤ ዓመለወርቅ ፍቃዱ በ2:43:14 የሁለተና ደረጃ እንዲሁም ትነበብ ነብዩ 2:44:32 በመሮጥ የ3ኛ ደረጃን አግኝተዋል።

በጣሊያን ፖርዴኖ የቦርጊ ማራቶን በሴቶች ፉክክር የ1ኛ ደረጃውን ኢትዮጵያዊቷ አስመራወርቅ በቀለ ስትይዝ የገባችበትም 1:14:21 በመሮጥ ነው። በስዊትዘርላንድ የጄኔቭ 20 ኪሎ ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክር ሄለን በቀለ 1:06:3 በመሮጥ የ1ኛ ደረጃን ይዛለች። በስፔን ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ፉክክር በወንድም በሴትም ድሉ የኢትዮጵያውያን ኾኗል። በወንዶች አዲሱ ይሁኔ 1ኛ ወጥቷል። በሴቶች መሰሉ በርሄ የ2ኛ እንዲሁም ዘርፌ ወንድማገኝ የ3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በሜክሲኮ-ጓዳላጃራ ማራቶን በሴቶች ፉክክር በ ጀሚላ ሹሬ የ2ኛ ደረጃን አግኝተናል። ጀሚላ ሮጣ የገባችው 2:32:48 ነው።

የዓለም ዋንጫ መዳረሻ

ኳታር ውስጥ የሚደረገው የዓለም ዋንጫ ሊጀምር ከ13 ቀናት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። የትኞቹ ቡድኖች የዓለም ዋንጫን የማንሳት እድሉ አላቸው ተብሎ የተጠየቀው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞው አማካይ ተጨዋች ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ፈረንሳይን የሚስተካከል ቡድን የለም ብሏል። ዘንድሮ ፈረንሳይ ዋንጫውን የመውሰድ የተሻለ ዕድሏ የሚሰፋው ፖል ፖግባን ካሰለፈች ብቻ ነው ብሏል ባስቲያን።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣን ሐንሲ ዲተር ፍሊክ ዋንጫዎችን ሲመለከቱምስል Sven Simon/imago images

«ፖል ፖግባ የሚሰለፍ ከኾነ የፈረንሳይን ቡድን የሚያህለው የለም ነው የምለው። ፈረንሳዮች አብሮ በመጫወት ልምድ ያካበቱ ምርጥ ተጨዋቾች አሏቸው። ኬሊያን እምባፔን ብታይ እንኳን አስደናቂ ተጨዋች ነው። አሰልጣኝ ዲዲዬር ዴሻምፕስም ተጨዋቾቹ ሜዳ ላይ ማድረግ የሚችሉትን ለመጠየቅ በሚገባ የተካኑ ናቸው። ሁሉም በአስተማማኝ አቋም ላይ ካሉ ለእኔ ፈረንሳይ ዋንጫውን ያነሳል ብዬ ከፍተኛ ግምት የምሰጠው ቡድን ነው።»

እግር ኳስ መጫወት በይፋ ካቆመ በኋላ ጀርመን ውስጥ በሚገኘው ዋናው የቴሌቪዥንን ጣቢያ ARD የስፖርት ተንታኝ የሆነው ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ስለ ሀገሩ ብሔራዊ ቡድንም ተናግሯል። ብሔራዊ ቡድናችን ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉትም ብሏል። ስለ ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ግን የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል።

«በሐንስ ፍሊክ እተማመናለሁ። የሚያደርጉትን በሚገባ የሚያውቁም ናቸው። ይልቁንስ ጉዳዩ ስለተጨዋቾቹ ነው። እንደ ጃማል ሙሳይላ ያሉ ጥሩ ተጨዋቾች አሉን። ጃማል በጣም ምርጥ ተጨዋች ነው። በእኔ ዕይታ ከዚህ በፊት ያልነበሩንን ምርጥ ምርጥ ነገሮች ዐሳይቶናል። ከእሱ እጅግ የምወድለት በመከላከሉም በኩል ጥሩ መሆኑን ነው።»

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሁሉንም አኅጉራት የወከሉ በርካታ ቡድኖች ጥንካሬ ውድድሩን ከወዲሁ አጓጊ እንዲሆን አድርጎታል።  

የሻምፒዮንስ ሊግ እና የአውሮጳ ሊግ 16 ቡድኖች ድልድል ዛሬ ኒዮን ስዊትዘርላንድ ውስጥ ወጥቷል። በሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ 8 ብርቱ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ይኖራሉ። ሳዲዮ ማኔን ከፊት መስመር የሚያስቀድመው የጀርመኑ ኃያል ቡድን ባዬርን ሙይንሽን ሊዮኔል ሜሴ፣ ኔይማር፣ ኪሊያን እምባፔ እና ሌሎች የፓሪ ሳንጃርሞ እንቁዎችን ሊገጥም ወደ ፓሪስ ያቀናል።  

የሻምፒዮንስ ሊግ እጣ ድልድል ሲወጣምስል Martial Trezzini/KEYSTONE/dpa/picture alliance

በፕሬሚየር ሊጉ ትናንት ቶትንሀም ሆትስፐርን በሜዳው 2 ለ1 ድል ያደረገው ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ ጋር ይገናኛል። የባለፈው የሻምፒዮንስ ሊግ ቂሙን መወጣት ይችል እንደሆነ ግን አጠያያቂ ነው። ከሊቨርፑል ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ሪያል ማድሪድ ጠንካራ ነው። በፕሬሚየር ሊጉ ፉልሀምን 2 ለ1 አሸንፎ አርሰናልን በ2 ነጥብ የሚከተለው ማንቸስተር ሲቲ ወደ ጀርመን አቅንቶ ላይፕትሲሽን ይገጥማል።

አርሰናል በትናንቱ የለንደን ከተማ ደርቢ ግጥሚያ 62ኛ ደቂቃ ላይ የተገኘውን የማእዘን ምት ኳስ ጋብሬል ከመረብ በማሳረፍ ነው ቸልሲን በሜዳው ኩም ያደረገው። ቤኔፊካ ከክለብ ብሩጅ፤ ኤስ ሚላን ከቶትንሀም ሆትስፐርአይንትራኅት ፍራንክፉርት ከናፖሊ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቸልሲ፤ እንዲሁም ኢንተር ሚላን ከፖርቶ ጋር ይጋጠማሉ።

በአውሮጳ ሊግም 16 ቡድኖች በጥሎ ማለፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች መርኃ ግብር ወጥቷል። በዚህ መሰረትም፦ ባርሴሎና ከማንቸስተር ዩናይትድ፤ ጁቬንቱስ ከናንቴ፤ ስፖርቲንግ ከሚድትዪላንድ፤  ሻካታር ከሬኔ፤ አያክስ ከዑኒዮን ቤርሊን፤  ባዬር ሌቨርኩሰን ከሞናኮ፤ ሴቪያ ከፒኤስቪ እንዲሁም ዛልስቡርግ ከሮማ ጋር ይጋጠማሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW