የጥቅምት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥቅምት 3 2018
በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ የመጨረሻ ማጣርያ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ አንዱን አሸንፋ በሌላኛው ተሸንፋ ከምድቡ አምስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። የሸገር ደርቢን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ያስተናገደው የአዲስ አበባ ስታዲየም በምን አይነት ይዞታ ላይ ይገኛል? ጨዋታዎቹን ስታዲየም ገብቶ ከተከታተለ እና የስታዲየሙን ይዞታ ከቃኘ የስፖርት ጋዜጠኛ ጋር ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ፉክክሮች ድል ቀንቷቸዋል ። የጀርመን ቡድን ዛሬ ከሰሜን አየርላንድ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ይኖረዋል ። በነገው ዕለት የእንግሊዝ ቡድን በዳውጋቫ ስታዲየም ከላቲቪያ ጋር ይጋጠማል ።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሁነዋል
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሃዊ ፈይሳ እሁድ ዕለት በነበረው የቺካጎ ማራቶን አሸነፈች ። አትሌቷ ያሸነፈችበት 2:14.56 ሰዓት በሴቶች የማራቶን ሩጫ ታሪክ አምስተኛው ፈጣን ተብሎ ተመዝግቧል ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መገርቱ ዓለሙ 2ኛ ደረጃ አግኝታለች፥ የገባችበት ሰአትም 2:17:18 ነው ። የታንዛኒያዋ አትሌት ማግዳሌና ሻውሪ ሦስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች ።
በወንዶች ፉክክክር ኡጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ በ2:02:23 አሸንፏል ። ኬንያውያኑ አሞስ ኪፕሩቶ እና አሌክስ ማሳይ ሁለተኛና ሦስተኛ ወጥተዋል ። አሜሪካዊው ኮነር ማንትዝን ተከትለው የገቡት ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች አትሌት ሁሰዲን መሀመድ እና አትሌት ሰይፉ ቱራ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃን አግኝተዋል ።
ዐርብ ዕለት ዩናይትድ ስቴትስ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ በተካሄደው የአትሎስ የአንድ ማይል የቤት ውስጥ እና የጎዳና ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኬፕዬጎን በ4:17.78 በሆነ ጊዜ አሸንፋለች ። የኦሎምፒክ የሦስት ጊዜያት አሸናፊዋ እና በዓለም ፉክክር የአምስት ጊዜያት ባለድሏ ኬኒያዊት አትሌት በኬንያ ሽልንግ ሲመነዘር 7.7 ሚሊዮን አግኝታለች ። $60,000 ዶላር ማለት ነው ። ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ያገኙ ሯጮች እያንዳንዳቸው 25,000 ዶላር ተሸልመዋል ።
በዚህ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ (4:19.75 ) ሁለተኛ ወጥታለች ። ሌላኛዋ የአገሯ ልጅ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በበኩሏ 4:33.20 በመግባት 4ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች ። አሜሪካዊቷ ኒኪ ሒልትዝ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። አራተኛ፣ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ያገኙ ሯጮችም የገንዘብ ሽልማቱ ተቋዳሾች መሆናቸው ተዘግቧል ። ለአራተኛ ደረጃ 8,000 ለአምስተኛ 5,000 እንዲሁም ለስድስተኛ 2,500 ዶላር የገንዘብ ሽልማት መሰጠቱም ታውቋል ። ተፎካካሪዎች በውድድሩ ወቅት የኣትሎስ (Athlos) ማለትም በግሪክኛ «ፉክክር» የሚል ስም ያለበት መለያ ይለብሳሉ ።
የዓለም ዋንጫ ማጣርያ የእግር ኳስ ጨዋታዎች
ለዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ጨዋታ ማለፋቸውን ካረጋገጡ የአፍሪቃ አገራት መካከል ጋና አምስተኛ ሁናለች ። ከ15 ዓመታት በፊት የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ላይ መድረስ የተሳካላት ጋና፦ በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ አልጀሪያ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዝያን ተቀላቅላለች ። የሚቀጥለው የዓለም ዋንጫ የሚካሄው በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ የጋራ አዘጋጅነት ነው ። ጋና በምድቡ ከኮሞሮስ ጋር በነበራት የመጨረሻ ግጥሚያ ለማለፍ የሚጠበቅባት አንድ ነጥብ ማግኘት ብቻ ነበር ። አክራ ስፖርት ስታዲየም ውስጥ በነበረው ግጥሚያ ግን አንድ ለዜሮ ድል አድርጋ ማለፍ ችላለች ። ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረችው ማዳጋስካር በማሊ 4 ለ1 በመሸነፏ ደግሞ ጭራሽ ጋና ለማለፍ ምንም አይጠበቅባትም ነበር ።
በዘጠኝ ምድብ ስድስት ስድስት ተጋጣሚዎችን በማካተት ከተደለደሉት አምሳ አራት አገራት መካከል ከየምድባቸው በነጥብ አንደኛ የሆኑት በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ተፎካካሪነት ያልፋሉ ። ከአጠቃላዩ ምድብ ጥሩ ነጥብ የሰበሰቡ አራት ሌሎች ቡድኖችም ግማሽ ፍጻሜ እና የፍጻሜ ውድድር አድርገው አሸናፊው ይለያል ። ከዚያም አፍሪቃን የሚወክል ዐሥረኛ ቡድን ለመሆን ከእሥያ፣ ከደቡብ አሜሪካ፣ ከኦሺያና እንዲሁም ከመካከለኛው አሜሪካ እና የካሪቢያን እግር ኳስ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን (CONCACAF)በደርሶ መልስ ይጋጠማል ማለት ነው ።
ኤርትራ ከውድድሩ ከወጣች በኋላ ካፍ ባወጣው መግለጫ መሠረት ዘንድሮ ከየምድባቸው መጨረሻ ከወጡ ቡድኖች ጋር የተደረጉ ነጥቦች እንደሚቀነሱ ጠቅሷል ። በዚህም መሠረት ከየምድቡ የመጨረሻ ደረጃ የሚገኙ ቡድኖችን ያሸነፉ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖች ላይ ተጽእኖው ከበድ ይላል ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎቹን ከጊኒ ቢሳው እና ቡርኪና ፋሶ አድርጓል ። ብሔራዊ ቡድኑ በቡርኪናፋሶ ትናንት የ3 ለ1 ሽንፈት ደርሶበታል ። ባለፈው ረቡዕ በነበረው ግጥሚያ ጊኒ ቢሳውን በራምኬል ጀምስ (27') ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል ። ከምድቡ አንድ ነጥብ ብቻ ያላት ጅቡቲን ብቻ ቀድሞ በ9 ነጥብ በአምስተኛነት አጠናቅቋል ። ቡርኪናፋሱ ከግብጽ በአምስት ነጥብ ተበልጣ በ21 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ።
የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፍጻሜ ጨዋታ
19ኛው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ሕዳሴ ዋንጫ አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ትናንት በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል ። በፍፃሜ ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል ጋር ተጋጥሞ 2 ለ1 አሸንፏል ። ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሳንጃው) ከቡድኖች ሁሉ የበላይ በመሆንም የዘንድሮውን ዋንጫ ወስዷል ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፀባይ ዋንጫ ተሸልሟል ።
ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አላሟላም በሚል ውድድሮችን እንዳያካሂድ በፊፋ የታገደው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከረዥም ጊዜ በኋላ ነበር የአገር ውስጥ ውድድሮችን እንኳን ያስተናገደው ። ስታዲየሙ ለረዥም ጊዜ የተለያዩ እድሳቶች ሲደረጉበት ነበር ። ለመሆኑ የመጫወቻ ሜዳው እና የታዳሚያን መቀመጫዎች በአሁኑ ወቅት ምን ማሻሻያ ተደረገላቸው ። የኢትዮኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ የትናንቱን ግጥሚያ አዲስ አበባ ስታዲየም ታድሞ ተከታትሏል ።
በካታንጋ በኩል መቀመጫዎቹ ከፊት ካሉት ጋር የተቀራረቡ በመሆናቸው ጉልበት ለመዘርጋት ያስቸግራሉ የሚሉ ቅሬታዎች ተደምጠው ነበር ። አንተ ስታዲየሙን ስትመለከት ምን ታዘብህ አንተ ባልነበርክበት አቅጣጫስ ከነበሩ ሰዎች የተሰሙ ቅሬታዎችን ለማጣራት ሞክረሀል?
ባለፈው ዐርብ ሉክዘምበርግን 4 ለ0 ድል ያደረገው የጀርመን ቡድን ዛሬ ማታ ከሰሜን አየርላንድ ጋር ይጋጠማል ። በመጀመሪያ ግጥሚያው ሰሜን አየርላንድን 3 ለ1 ነው ያሸነፈው ። የፊታችን ዐርብ ደግሞ ከሉግዘምበርግ ጋር የመልስስ ጨዋታ ይጠብቀዋል ። በመቀጠል ከአንድ ወር በኋላ ከስሎቫኪያ ጋር የመልስ ግጥሚያ ያደርጋል ። ቡድኑ በስሎቫኪያ 2 ለ0 መሸነፉ የሚታወቅ ነው ።
ዛሬ ማታ፦ ስሎቫኪያ ከሉግዘምበርግ፣ ስሎቬኒያ ከስዊትዘርላንድ፣ ስዊድን ከኮሶቮ፤ አይስላንድ ከፈረንሳይ፣ ዩክሬን ከአዘርባጃን እንዲሁም ዌልስ ከቤልጂየም ጋር ይጋጠማሉ ። ትናንት ግሪክን 3 ለ1 የያሸነፈችው ዴንማርክ እስካሁን የሚያሸንፋት ጠፍቶ ከምድቧ በ10 ነጥብ የበላይ ሁናለች ። ትናንት ቤላሩስን 2 ለ1 ድል ያደረገችው ስኮትላንድ ትከተላለች ።
በነገው ዕለት ደግሞ፦ የእንግሊዝ ቡድን በዳውጋቫ ስታዲየም ከላቲቪያ ጋር ይጋጠማል ። የእንግሊዝ ቡድን በሐሙስ ግጥሚያ ዌልስን 3 ለ0 ማሸነፉ ይታወቃል ። ቱርክ ከጆርጂያ፣ ስፔን ከቡልጋሪያ፣ የአየርላንድ ሪፐብሊክ ከአርሜኒያ፣ ፖርቹጋል ከሐንጋሪ፣ ጣሊያን ከእሥራኤል እንዲሁም አንዶራ ከሠርቢያ የሚጋጠሙት ነገ ነው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ