የጥበብ ባለሙያው ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀመ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2017
የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓት ቀብር ዛሬ ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው መንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀመ።የኪነ ጥበብ ባለሙያው በሕይወት ዘመኑ በደራሲነት፣ በተርጓሚነት፣ በአዘጋጅነት፣ በተዋናይነት እና በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ሀገሩን በስፋት ስለማገለገሉ በተነበበው የሕይወት ታሪኩ ላይ ተጠቅሷል።
በተለያዩ ሥርዓቶች ለእሥር የተዳረገ "የሰብዓዊ መብት ተሟጋች" ጭምር እንደነበር የተነገረለት አርቲስት ደበበ እሸቱ እሑድ ነሐሴ 11ቀን 2017 ዓ.ም ነበር በ84 ዓመቱ ያረፈው።
ሁለገብ የሚባለው የኪነ ጥበብ ባለሙያ ደበበ እሸቱ ዛሬ ማክሰኞ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሙያው ወዳጆች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዐተ ቀብሩ ተፈጽሟል። ከዚህ አስቀድሞ ለሁለት ዐሥርት ዐመታት በላይ ባገለገለበት ብሔራዊ ትያትር የኢፌደሪ ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት የአስክሬን ሽኝት ተደርጎለታል።
በ1934 ዓ.ም የተወለደው አርቲስት ደበበ እሸቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኋላም እ.አ.አ በ1965 ሃንጋሪ ውስጥ የቲያትር ጥበብን ስለመማሩ በሕይወት ታሪኩ ተገልጿል።
የሕይወት ታሪኩን ያቀረበው አርቲስት ተፈሪ መኮንን አርቲስት ደበበ እሸቱ በደራሲነት፣ በተርጓሚነት፣ በትያትር አዘጋጅነት፣ በተዋናይነት፣ በመድረክ መሪነትና ሌሎች ዘርፎች ለኢትዮጲያ የኪነ ጥበብ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽዖ አድርጓል ብሏል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ደበበ እሸቱ ከ40 በላይ ተውኔቶች ላይ የተሳተፈ መሆኑና "እናት ዓለም ጠኑ፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ኪንግ ሊር፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ የከርሞ ሰውና ጠልፎ በኪሴ" ይገኙበታል።
ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የተሳተፈ መሆኑና የ1997 ትን ምርጫ ተከትሎም ለእሥር ተዳርጎ እንደነበርም ተገልጿል።
በሥነ ጽሑፍ ዘርፍም ከተዋናይ ሀሁ፣ የባሩድ በርሜል፣ ድብልቅልቅ የመድረክ ተውኔት፣ ያልታመመው በሽተኛ፣ የደም እንባን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉሟል።በኢትዮጵያ እና በውጭ ፊልሞች ላይም ተሳትፎ በማድረግ ለሌሎች ዓርዓያ እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ያሳያል።
አርቲስት ደበበ እሸቱ ከባለቤቱ ከወይዘሮ አልማዝ ደጀኔ አራት ልጆን ያፈራ ሲሆን የስምንት የልጅ ልጆች አያትም እንደነበርም ተገልጿል። ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ለማግኘት የበቃው አርቲስቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2015 የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶቶታል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ