1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጦርነት ስጋት ያዣበበባት የትግራይ ክልል እና የህወሓት አስገዳጁ የገንዘብ ማሰባሰብያ

ሐሙስ፣ መጋቢት 3 2018

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ ነዋሪ የሆነዉ ደሞዝተኛ ሕዝብ የአንድ ወር ደምወዙን እንዲያዋጣ ፤ ደምወዝተና ያልሆነዉ ደግሞ ሌሎች ቁሳቁሶችን እንዲሰጥ መጠየቁን በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠየቁ። በትግራይ ዳግም ግጭት ይቀሰቀሳል የሚለዉ ስጋት አይሏል። የክልሉ ነዋሪዎች አካባቢዉን ጥለዉ እየወጡ ነዉ።

የህወሓት ባንዲራ
የህወሓት ባንዲራምስል፦ Yasuyoshi Chiba/AFP

የጦርነት ስጋት ያዣበበባት የትግራይ ክልል እና የህወሓት አስገዳጁ የገንዘብ ማሰባሰብያ

This browser does not support the audio element.

የጦርነት ስጋት ያዣበበባት የትግራይ ክልል እና የህወሓት አስገዳጁ የገንዘብ ማሰባሰብያ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ ነዋሪ የሆነዉ ደሞዝተኛ ሕዝብ የአንድ ወር ደምወዙን እንዲያዋጣ ፤  ደምወዝተና ያልሆነዉ ደግሞ ሌሎች ቁሳቁሶችን እንዲሰጥ መጠየቁን በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃወሙ። በሌላ በኩሉ በትግራይ ይቀሰቀሳል የተባለዉን ግጭት ፈርተዉ የትግራይ ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ ወጣቱ አካባቢዉን ለቆ እየወጣ እንደሆነ ተሰምቷል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስድስት ቢሊዮን ብርን ለማሰባሰብ ሰራተኛዉ ሕዝብ የአንድ ወር ደመወዙን እንዲሰጥ እያስገደደ መሆኑን አካባቢዉ ላይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጽኑ አዉግዘዋል። በትግራይ ነዋሪ የሆነዉ ደሞዝተኛ ሕዝብ የአንድ ወር ደምወዙን በግድ እንዲያዋጣ የሚያስገድደዉ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሌላ በኩል ደግሞ ፌደራል መንግሥት ለሰራተኛዉ ደምወዝ አላከም ሲል እየከሰሰ ነዉ ሲሉ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አምዶም ገብረሥላሴ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

«ግዚያዊ አስተዳደሩ አንድ ወር ገደማ ሆኖታል። የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም አለን፤ ብሎ ስድስት ቢሊየን ብር እንደሚሰበሰብ በይፋ ተናግሯል። ይህን ገንዘብ የሚያሰባስበዉ ከመንግሥት ሰራተኛዉ ከነጋዲዉ ሁሉ ነዉ ሲል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፏል።  የመንግሥት ሰራተኛዉ አናናዋጣም ብሎ ከፍተኛ ተቃዉሞ ቢያሰማም፤ መመርያ ነዉ ብሎ የግድ መክፈል አለባችሁ ሲል  ትዕዛዙን አስተላልፏል።  »

ህወሓት ይህ መዋጮ መደረግ አለበት ያለዉ ለምንድን ነዉ?

« እንደምክንያት የተጠቀሰዉ ባለፈዉ የትግራይ ጦርነት ላይ፤ ጉዳት የደረሰባቸዉ አካል ጉዳተኞች ህክምና እንዲያገኙ እንክብካቤ እንዲያገኙ ሲል ነዉ የተናገረዉ። ህወሓት ለጦርነቱ ከሻብያ ከፋኖ ጋር የጀመረዉ ጽምዶ የተባለዉ ወታደራዊ ጥምረት ጋር ወታደራዊ ዝግጅቶችን እያካሄደ ነዉ። ገንዘቡን የሚያሰባስበዉ በዋናነት ለዝያ ጦርነት ነዉ። በትግራይ ላይ የምንቀሳቀስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን የህወሓትን እርምጃ በዋናነት ተቃዉመናል።  »   

በትግራይ የሚታየዉን ቀዉስ ተከትሎ በባንኮች የገንዘብ እጥረት ተከስቷልምስል፦ Marco Simoncelli

ገንዘቡን ለጦርነት ማስፈፀምያ ለማዋል ነዉ 

በትግራይ የሚንቀሳቀሰዉ የዉድብ ናፅነት ትግራይ ምክትል ሊቀመንበር አለምሰገድ አረጋይ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ህወሓት በትግራይ ክልል እየፈፀመ ያለዉ ትግራይ ክልል ላይ ጠንካራ አስተዳደር ባለመኖሩ ምክንያት ባይ ናቸዉ።  

« በተደጋጋሚ በመግለጫ ላይ ስንገልጽ እንደነበረዉ፤ በትግራይ ቀዉስ እንዳለ የምናዉቀዉ ነገር ነዉ። ምክንያቱም በክልሉ ጠንካራ አስተዳደር ካለመኖሩ ጋር የተገናኘ ነዉ። አሁን ላይ ስልጣን ላይ ያለዉ ህወሓት ነኝ እያለ ያለ ቡድን እንጂ ህወሓት የለም። በትግራይ ክልልም ቅቡልነት የሌለዉ ፓርቲ ነዉ። በኢትዮጵያ ህግም የምርጫ ቦርድ ፓርቲነቱን ሰርዞታል፤ ግን ህወሓት ነን ብሎ አንድ የሚጠራ ቡድን አለ፤ የመንግሥት ሰራተኞችን ደሞዝ ሰራተኞቹ  ሳይፈልጉ እና ሳይስማሙ እያስገደደ ደሞዛቸዉን እንዲቆረጥ  እያደረገ ነዉ። ይህ በብር ነዉ ፤ ከደሞጥ የሚቆረጥ ነዉ። ተራ ነዋሪቤት እየገባ ደግሞጤፍ ስንዴ ፤  ዘይት በርበሬ ሽሮ ሁሉ እየሰበሰበ ነዉ።

አቶ አለምሰገድ ህወሓት ይህን ገንዘብ ለምንድን ነዉ የሚሰበስበዉ ይላሉ?

«ይህ መልሱ የታወቀ ነዉ፤ ህወሓት ወደ ጦርነት ለመግባት እያደረገዉ ያለዉ ዝግጅት ነዉ። ህወሓት ያለ ጦርነት መግባት ስለማይችል፤ ለጦርነት ይጠቅመኛል ብሎ  ያሰበዉን በአጠቃላይ ዝግጅት እያደረገ ነዉ።»  

ፌደራል መንግሥት ደምወዝ አልሰጠንም በሚል በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ስም በመጥቀስ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)በስማችን መግለጫ አዉጥቶ ነበር ያሉት የብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ  ባይቶና ምክትል ሊቀመንበር ዮሴፍ በረኸ ይህንኑ መግለጫ በማዉጣት ግልፅ አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል።  

« በኛ ስም  ትግራይ ዉስጥ ሆነዉ ሰራተኞች ደምወዝ አልተሰጣቸዉም በሚል፤ የፓርቲዎችን ስም ሰብስቦ ፤ የተሳሳተ ማህተብ በማድረግ፤ መግለጫ አዉጥቶ ነበር። ይህ ስህተት በስህተት በስማችን የተደረገ ነገር ነዉ ስንል መግለጫ አዉጥተን ጉዳዩን አስተባብለናል።  

ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ እየሸሹ ነዉ

አቶ ዮሴፍ እንደሚሉት ህወሓት ገንዘብ አሰባስባለሁ ብሎ ስራ ከጀመረ ቆይቷል ሲሉም አክለዋል። በትግራይ ነዋሪዉ ከነገ ዛሬ ጦርነት ተቀሰቀሰ በሚል ስጋት ዉስጥ ነዉ ሲሉ የገለፁት  የብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ፤  ባይቶና ምክትል ሊቀመንበር ዮሴፍ በረኸ፤ ይህንኑ ሽሽት በርካታየትግራይ ነዋሪዎች በተለይ ወጣቱ አካባቢዉን ጥሎ እየለቀቀ ነዉ ብለዋል።

የትግራይ ክልል ባንዲራ ምስል፦ Marco Simoncelli

« አጠቃላይ ሁኔታዉን ስናይ፤ ትግራይ የሦስት አካላት ሆናለች፤ አንደኛዉ የህወሓት ቡድን ነዉ ፤ ሁለተኛዉ የፋኖ ቡድን ነዉ ሦስተናዉ፤ የሻብያ ቡድን ነዉ። ከነዚህ ሦስት አካላት ዉጭ አሁን ትግራይ ክልል ላይ መኖር አይቻልም። ከነዚህ ዉች ያለዉ ሁሉም ትግራይን ለቆ ወቷል። ጋዘጠኞች ፖለቲከኞች አክቲቪስቶች እና ሌሎች አካላት ትግራይን ለቀዉ ወጥተዋል። ትግራይ ዉስጥ የሚገኙት መዉጫ መንገድ እና መፍትሄ ያላገኙ ብቻ ናቸዉ። በርካታ የትግራይ ክልል ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ ሸሽተዋል።»  

ስምረት ፓርቲ በቅርቡ ባወጣው መግለጫም ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)  በመንግስት ይዞታ ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ለዚሁ የገቢ ማሰባሰብያ በማሰብ ለሽያጭ  እየተዘጋጀ ነው ሲል በመውቀስ በዚህ ግዢ የሚሳተፉ ባለሐብቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቡ የሚታወስ ነዉ።

አዜብ ታደሰ

ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW