1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ እና የጸጥታ ትኩረቱ

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016

በኦሮሚያ ክልል በታጠቁ አካላት ተነጣጥሮ ነበር የተባለ አገር የማፍረስ ልዩ ልዩ ሙከራ መንግስት መቀልበሱን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡ ሽመልስ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤተ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ አማጺያን ታህድሶ ስልጣና ወስደው ከህብረተሰቡ ጋር መቀላቀላቸዉን ተናግረዋል።

ፎቶ ማህደር፤ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ
ፎቶ ማህደር፤ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳምስል Seyoum Hailu/DW

የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ፡ የጸጥታ ትኩረቱ

This browser does not support the audio element.

የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ፡ የጸጥታ ትኩረቱ

በኦሮሚያ ክልል በታጠቁ አካላት ተነጣጥሮ ነበር የተባሉትን አገር የማፍረስ ልዩ ልዩ ሙከራዎች መንግስት መቀልበሱን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አዳማ ገልመ አባገዳ በጨፌ አዳራሽ እየተካሄደ ያለው የጨፌ ኦሮሚያ (የክልሉ ምክር ቤተ) መደበኛ ጉባኤ ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ በዚህ ዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ አማጺያን ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጣና ወስደው ከህብረተሰቡ ጋር እየተቀላቀሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ ይህን ማብራሪያ ለምክር ቤቱ የሰጡት አሁንም ድረስ በፀጥታ ችግሩ በክልሉ የተለያዩ እገታና ግድያዎች እንደሚፈጸሙ ተደጋግሞ በሚገለጽበት ወቅት ነው፡፡ ከትናንት እሁድ ጀምሮ ዛሬም ቀጥሎ ስካሄድ በዋለው የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን ሶስተኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ የምክር ቤቱ አባላትና የክልሉ ስራ አስፈጻሚ በጉልህ አንስተው ከመከሩበት ጉዳይ አንደኛው በክልሉ የብዙሃን የትኩረት ጉዳይ የሆነው የጸጥታ ችግር ነው፡፡

ፈታኙ የጸጥታ ጉዳይ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በትናንትናው እለት የመንግስት የበጀት ዓመቱ ስራ አገፈጻጸም ሪፖርትን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ይህንኑን የጸጥታ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተውት በሪፖርታቸው አካተውታል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳነሱትም “የኦሮሚያ እና ኦሮሞ ፀጥታን ማረጋገጥ ከሁሉም የላቀ አጀንዳ መሆኑ ታምኖበት ከውስጥ እና ከውጪ ጠላት የተነጣጠረብንን የትኛውንም ጥቃት እየመከትን እንገኛለን” ሲሉ መንግስታቸው ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ላቅ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ ሽመልስ በዚሁ ማብራሪያቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጸጥታ መዋቅሩ ለዚሁ መስዋእትነት እየከፈለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም ክልሉንና አገሪቱን ለማፍረስ ይሰራሉ ያሉትን የታጠቁ አካላትን ጠቃቅሰዋል፡፡

“ክልላችንና አገራችንን ለማፍረስ ከሚጣጣሩ አንዱ ኦነግ-ሸነ ሲሆን ይህ ኃይል የኦሮሞና ኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡ ፍላጎታቸው በምርጫ ተፎካክረው ህዝባቸውን ማገልገል ሳይሆን ሁሌም የኦሮሞ ጠላቶች ፍላጎት ለማሳካት ከነሱ ጋር በመሰለፍ ህዝባቸው ላይ ክህደት መፈጸም ነው፡፡ ከዓለማቀፉና ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር መራመድ የተሳናቸው ኦሮሞን በቀዬው ያዋረዱ ናቸው፡፡ መንግስት ያቀረበለትን የሰላም ጥሪ እምብኝ ብሎ መዝጋቱም ይታወሳል፡፡ በመሆኑም በክልላችን የህግ የበላይነትና ሰላም ለማስከበር ከፍተኛ እርምጃተወስዷል፡፡ በዚህም ኦፕሬሽን ውስጥ የተማረኩና እጃቸውን የሰጡ በርካቶች በምህረት እንዲገቡና በሶስት ዙር የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከህዝብ ጋር እንዲቀላቀሉ ሆኗል” ነው ያሉት፡፡

አቶ ሽመልስ ኦሮሚያ ውስጥ በስፋት ከምንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን መሃል ምን ያህሉ ትጥቃቸውን ፈተው ከህብረተሰቡ ጋር እንደተቀላቀሉ ግን አልገለጹም፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ምክር ቤት ፊት ቀርበው ከአንድ ዓመት በፊት በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ጥሪን ሲያቀርቡ ስጠቀሙ የነበረው የተላዘቡ ቃላትም ባሁኑ ተቀይሮ ታጣቂዎችን በአገር ማፍረስ እና ህዝብን በማሰቃየት ድርጊት ክፉኛ ወቅሰዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ያነሱት ሌላኛው ታጣቂ

በሌላ በኩልም በፕሬዝዳንቱ በአገር ማፍረስ እና ህዝብ በማሰቃየት የተከሰሱት “ጽንፈኛ” የተባሉ የታጠቁ አካላት ሲሆኑ የነዚህ አካላት ማንነት ላይ እምብዛም ማብራሪያ ሳይሰጥ አደረሱት የተባሉ ጥቃት ግን ተብራርቷል፡፡ “የጽንፈኛው ሃይል በክልላችን ስተገብር የቆየውን አፍራሽ ድርጊት በመቋቋም የተለያዩ አድርምጃዎች ስወሰዱ ቆይቷል፡፡ ይህ ሃይል የአገራችን ብዝሃነት የማይቀበል፣ ብዝሃነትን ለማጥፋት የሚንቀሳቀስና ኦሮሞን በጠላትነት የፈረጀ ነው፡፡ በተለያዩ አከባቢዎች ዝርፊያ በመፈጸም በህዝብ ላይ ግድያ የሚያደርጉ ብሆንም የዚህ ኃይል እቅስቃሴም በተወሰደ እርምጃ ለመቀልበስ ተችሏል” ነው ያሉት፡፡

ፎቶ ማህደር፤ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳምስል S.Getu/DW

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው በርካታ ጥያቄዎች ማብራሪያ ስሰጡም አሁን አገሪቱን በሚመራው መንግስት ‘ሁለንተናዊ’ ያሉት እምርታ መገኘታቸውን መከራከሪያ ሃሳቦችን አንስተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት ከጸጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዘው ስላሉ ፈታኝ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ  “እኛን የደረሰን ተራ የመስራት በላባችን ተራራ ባጭረን መልሶ የማልማት፣ ወገባችን እስኪጎብጥ በመስኖ ጭምር የስንዴ ምርትን የመጨመር በተለያዩ ኢኒሼቲቮች የኦሮሚያን የማምረት አቅም ከፍ የማድረግ ተራ ነው፡፡ ህዝባችን አሁን አርፎ መልማት ስገባው ግን አሁንም በጭለማ እንዲኖር ተማሪም ወደ ፈተና እንዳይሄድ ቆሙ የሚተኩስበት የእርግማን ሃይል ግን ገብቶብናል፡፡ ይህ ሃይል የጽንፈኛ ሃይል ስመጣ ዞር ይላል፡፡ ከህዝባችን መሳሪያ እየፈታ ለጥቃት እንዲጋለጡ አበክሮ ይሰራል፡፡ ይህ አካሄድ አይበጀንም ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ገብተው እስካሁን በሶስት ዙር ስልጠና ወስደው ህዝባቸውን ተቀላቅለዋል፡፡ ለዚህ የክልላችን መንግስት ከፍተኛ አድናቆት አለው፡፡ አሁንም ለዚህ የተዘጋጁ ካሉና በአንድ ሺህ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ቢሆኑ 999 ኪ.ሜ. መንገድ ህደን ልንቀበላቸው ተሰናድተናል፡፡ በተቃራኒው የጥፋት መንገድን እንከተላለን ያሉት ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ ያሰፍናል” ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ በግብርናው ብሎም እንደ ጤና እና ትምህርት ባሉ የማህበራዊ ዘርፎችም በዓመቱ እምርታን ማስመዝገባቸውን ለምክር ቤቱ በዝርዝር ሲያስረዱ፤ ከጸጥታው ችግር ጋር ተያይዞ ስላገረሹት እንደ ወባ ያሉ ወረርሽኞች የህብረተሰቡን ጤና መፈተናቸውን፣ የትምህርት ዘርፉም በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች ስላስተናገደው ብርቱ ፈተና እና የማዳበሪያ እጦት ስለፈተነው የግብርናው ሴክተር ግን ብዙ አላሉም፡፡ በበጀት ዓመቱ 5.9 ቢሊየን ብር ከሙስና ማዳን መቻሉንና 3.1 ቢሊየን የሚገመት ንብረት አሁንም ድረስ በምርመራ ላይ መሆኑን ግን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡    

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW