1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤና ውሳኔዎቹ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ የካቲት 3 2017

በአዳማ ‘ገልማ አባገዳ’ የተቀመጠው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡ በ 6 ኛው የስራ ዘመን 4 ኛ ዓመት 8 ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደዉ ምክር ቤቱ የተለያዩ ሹመቶችንም አጽድቋልም፡፡ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤው የጸጥታ እና መሰረታዊ የተባሉ የምጣነ ሃብት ጉዳዮች ትኩረትን በመሳብ ተነስቷል፡፡

Äthiopien | Oromia wählt Shimeles Abdisa als Regionalpräsidenten wieder
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤና ውሳኔዎቹ

This browser does not support the audio element.

የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤና ውሳኔዎቹ

በአዳማ ‘ገልማ አባገዳ’ የተቀመጠው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡ በስድስተኛው የስራ ዘመን አራተኛ ዓመት ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤውን ትናንት የተቀመጠው ምክር ቤቱ የተለያዩ ሹመቶችንም አጽድቋልም፡፡ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤው የጸጥታ እና መሰረታዊ የተባሉ የምጣነ ሃብት ጉዳዮች ትኩረትን በመሳብ ተነስቷል፡፡ ለአብነትም አንድ የምክር ቤቱ አባል ህጋዊ ካልሆነ የግብር አሰባሰብ ጋር አያይዞ በጨፌው ጉባኤ ላይበአጽእኖት ጥያቄ አንስተዋል፡፡ “በግብር ስም አርሶ አደሩ የሚከፍለው ክፍያ ከልክ በላይ ነው፡፡ ይህ በተለያዩ አቅጣጫዎች ስነሱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ጨፌ የግብር ክፍያ ብሎ ከወሰነው ተመን ውጪ በመላው ኦሮሚያ ከግብር በተጨማሪ ተብለው በተለያዩ መዋጮዎች በግዴታም ጭምር በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች እየተፈጸመ መሆኑን ህብረተሰቡ ያነሳል፡፡ ቡሳ ጎኖፋ እና ሌሎችንም ካልከፈልክ ግብር አንቀበልም እየተባለ አርሶአደሩ እየተገደደም ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከደረሰኝ ውጪ ከአርሶ አደሩ ግብር የመሰብሰብ ድርጊትም አልፎ አልፎ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ላይ ምላሽ ብሰጥበት የሚለውን ለማንሳት ነው” ሲሉም ጥያቄያቸውን አንስተዋል፡፡

የቀረበው ሰላም ጥሪ

በክልሉ ተደጋግሞ ጥያቄ የሚነሳበት የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ እንደወትሮው በምክር ቤቱ በስፋት የተመከረበት ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ መንግስት በጸጥታው ጉዳይ አበክሮ እንዲሰራ በምክር ቤቱ አባላት ጥያቄም ምክረሃሳብም ተነስቷል፡፡ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን አበክሮ ስሰራ መቆየቱን ያሳወቀው የክልሉ አስፈጻሚ አካል በጨፌው በኩል ለታጠቁ አካልት ዳግም ጥሪውን አቅርቧልም፡፡ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሰዓዳ አብዱራሃማን በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክትም፤ “ህዝባችን በልማቱ ላይ ተሰማርቶ ተዓምር ሰርቶ በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናውን ለማረጋገጥ እያሳየ ያለው ለውጥ በሰላም መደገፍ አለበት፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስትም የክልሉን ህዝብ ሰላም ለብልጽግናው ግብ ወሳኝ ነው በሚል አቋም የሰላም ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም በአንድ ጥላ ስር ተደረገ የሰላም ስምምነት አለ፡፡ እናም የሰላም መንገድን መርጣችሁ የገባችሁ ከህዝባችን እና መንግስት ክብር አላችሁ፡፡ የተቀሩትም የግጭትና መደማማት ምዕራፍ ዘግተው ወደ ሰላም መንገድ ብመለሱ በራችን ክፍት መሆኑን አውቀው ዳግም ጥሪ እናቀርብላቸዋለን” ሲሉ በክልሉ ምክር ቤት ስም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ህገወጥነትን መግታት

ከምክር ቤቱአባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ህብረተሰቡን አማረዋል ተብለው የተነሱትን ድርጊቶች በማስመልከት ከአሁን ወዲህ በየቦታው ኬላ በመዘርጋት ከጉምሩክ እና የጸጥታ ፍተሻዎች ውጪ በየቦታው ገመድ በመዘርጋት የሚደረግ ድርጊት እንዲገታ ብሎም ያለደረሰኝ ግብር መሰብሰብ እንዲቆም አዘዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የህብረተሰቡን ደህንነት የሚያውኩ የአከባቢዎች ሚሊሻን ጨምሮ በመንግስት ጸጥታ ሃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች ከባድ ያሉት ቅጣት እንደሚያስከትልም አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

አዳማ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የስርዓት ለውጥ ፈተና

ይሁንና ክልሉ አሁን ላይ በፀጽጥታው ችግር መፈተኑን ያልሸሸጉት ሽመልስ፤የኦሮሞ ህዝብ የተጨቆነበትን ስርዓት ለመጣል ከከፈለው መስዋእትነት በላይ በእጁ የገባውን እድል ለመጠበቅ ሲል ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈለ ይገኛልም ብለዋል፡፡ “ህዝባችን ትግል ላይ ነበር፡፡ አሁን ላይ ትግላችን የደረሰበት እድል ደግሞ የጨቆነንን ስርዓት ጥለን ስሩን ለመንቀል የመጀመሪያው ስራ ስርዓት መገንባት ነው፡፡ ሌላው በምንገነባው ስርዓት በየደረጃው የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ህዝባችንን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ፤ ህዝባችንን በኢኮኖሚው፣ በትምህርት ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በዚህ የትግል ምዕራፍ ውስጥ ደግሞ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሂደቱን ለማክሸፍ የሚደረገውን ትግል መቀልበስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት ማመጽ ብቻ የነበረውን ትግል አሁን ስርዓቱን በመቀልበሳችን የሚመጣው ሸክም ከብዷል ማለት ነው፡፡ ስርኣትን በማሸነፍ መቀልበስ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ስርዓቱ የዘረጋው ባህልና ያቋቋማቸው ተቋማት አሉት፡፡ ይህን በየመዋቅሮቹ በማስረጽ ለዓመታት ስለኖረ ያንን እያንዳንዱን በማየት ህዝብን ማዕከል ያደረገ ስራ ይፈልጋል፡፡ ያንን ተከትሎ ነው በትክክለኛ ፖሊሲ መተካት የሚያስፈልገው፡፡ ህዝባችን ወደ ሁለገብ ብልጽግና ተሸጋግሮ በየደረጃው ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገት ድህነትና ኋላቀርነትን ከስር መንቀል ይሻል፡፡ ጠንካራ ስርዓት በየደረጃው መገንባት ግን ለትተቀን ተግቶ መስራትን ይጠይቃል” ነው ያሉት፡፡ ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት በክልሉ መንግስት የተሰጡ የተለያዩ አዳዲስ ሹመቶችንም አጽድቋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW