1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጳጉሜ 01 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 1 2013

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት አማካሪ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ዛሬም ድል ቀንቶታል። የዩጋንዳው ተጋጣሚውን በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሱን አረጋግጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በነገው ዕለት ባሕር ዳር ስታዲየም ውስጥ ጨዋታውን ያከናውናል።

Äthiopien Fußball Nationalmannschaft
ምስል ISSOUF SANOGO/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት አማካሪ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ዛሬም ድል ቀንቶታል። የዩጋንዳው ተጋጣሚውን በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሱን አረጋግጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በነገው ዕለት ባሕር ዳር ስታዲየም ውስጥ ጨዋታውን ያከናውናል። ቡድኑ በምን አይነት ደረጃ ላይ ይገኛል? ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በሚያደርገው ጨዋታ ተጋጣሚው የዚምባብዌ ቡድንን ለማሸነፍስ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? የባለሞያ ሐሳብ አካተናል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዛሬ በዙም የኢንተርኔት ቀጥታ ሥርጭት ከሰጡት መግለጫም አካተናል።  በመላው ዓለም የሚገኙ ሃገራት ዋና ዋና ቡድኖች ለዓለም ዋንጫ የሚያደርጓቸውን የማጣሪያ ጨዋታዎችንም እንዳስሳለን።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት አማካሪ (CECAFA)ግጥሚያ ዛሬ ለፍጻሜ ማለፉን አረጋገጠ። ንግድ ባንክ ሎዛ አበራ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረችው ግብ አንድ እኩል በጭማሪ ሰአትም በተመሳሳይ ውጤት ነበር የተጠናቀቀው። በፍጹም ቅጣት ምቱ መለያ ኢትዮጵያ 5 ለ3 በሆነ ውጤት አሸንፋ ለፍጻሜ ገብታለች።

ሎዛ አበራ በ14 ግቦች ኮከብ ግብ አግቢነቱን በመምራት ላይ ትገኛለች። በግማሽ ፍጻሜው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጋጠመው ከዩጋንዳው ሌዲ ዶቭስ ጋር ነበር። ከሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ ጥቂት ቀደም ሲል በዚያው በኬንያው ንያዮ ስታዲየም ውስጥ የኬንያው ቪኺጋ ክዊንስ ከምድብ ሀ የነጥብ መሪው የታንዛኒያው ሲምባ ክዊንስ ጋር ተጫውቶ 2 ለ1 አሸንፏል። በዚህም መሠረት በግማሽ ፍጻሜው ድል የቀናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኬንያው ቪኺጋ ክዊንስ የፊታችን ሐሙስ ለፍጻሜው ይጋጠማሉ።

የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ የንግድ ባንክ አምበሏ ሎዛ አበራ በግብ ትመራለች። ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በሚከናወነው ውድድር ሎዛ በ12 ከመረብ ያረፉ ግቦች ነው የምትመራው። ቀድሞ ለማልታ እግር ኳስ ቡድን ትጫወት የነበረችው ኢትዮጵያቷ አጥቂ ሎዛ አበራ፦ የኬንያው ቪህጋ ክዊንስ (Vihiga Queens FC)4 ለ1 ባሸነፉበት ጨዋታ ሎዛ አንድ ግብ አስቆጥራለች። በሁለተኛው የምድብ ለ ግጥሚያ የዛንዚባር ኒው ጀኔሬሽን (New Generations FC) የተሰኘውን ቡድን 10 ለ1 ሲያንኮታኩቱ ደግሞ አምስቱ ግቦች የሎዛ ነበሩ።  ሎዛ የባለፈው ቅዳሜ ሳምንት በነበረው ግጥሚያም 10 ለ0 ሲያሸንፉ ሁለት ጊዜ ሔትትሪክ ሠርታለች። ቡድኗ ወደ መጨረሻው ደረጃ እንዲሻገርም አምስት ግብ የሆኑ ኳሶችን ማመቻቸቷን ሴካፋ በድረ ገጹ ላይ ያወጣው ጽሑፍ ይጠቁማል።

ሌላኛዋ የንግድ ባንክ አጥቂ መዲና አወልም በግብ ክፍያ የሁለተኛነት ደረጃ በመያዝ ብቃቷን አስመስክራለች። መዲና እስካሁን ስምንት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ሎዛን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

የካፍ ቀጠናዊ የፍጻሜ ግጥሚያ ፍጻሜ የፊታችን ሐሙስ ይከናወናል። በፍጻሜው ግጥሚያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ከቀናው ከሁለት ወራት በኋላ ግብፅ ውስጥ በሚከናወነው የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ውድድር የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃን በመወከል ተካፋይ ይሆናል።

ለኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ከዚምባብዌ አቻው ጋር በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በደጋፊው ፊት ይጋጠማል። የዚምባብዌ ቡድን በአዲሱ አሰልጣኝ ሁጎ ብሩስ ከተመራው የደቡብ አፍሪቃ ቡድን ጋር ባለፈው ዐርብ ባደረገው ግጥሚያ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በዕለቱ የኢትዮጵያ ቡድን በጋና አቻው 1 ለ0 ተሸንፏል።

ምስል Omna Tadele/DW

ጋና የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ በሜዳዋ ያሸነፈችው 35ኛው ደቂቃ ላይ ሙባረክ ዋካሱ ከግብ ክልሉ 32 ሜትር ርቀት ላይ የላካት ኳስ ከመረብ በማረፏ ነው። ኳሷን ተንበርክኮ በሁለት እጆቹ ለማዳን የሞከረው ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ በእግሮቹ መሀል አልፋ መረብ ከመንካት ግን ሊታደጋት አልቻለም። በዚህም ጋና የመጀመሪያውን ግጥሚያ 1 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ቡድኑ ግብ ጠባቂ ላይ በተከሰተው አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን ግብ ማስቆጠር ባለመቻሉ መሸነፉን ዛሬ ከጥቂት ሰአታት በፊት ከባሕርዳር የዙም የቀጥታ መግለጫ የሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተናግረዋል። «በተክለማሪያም ምክንያት አይደለም የተሸነፍነው። አጠቃላይ የተሸነፍነው በጨዋታው ግብ ማስቆጠር ስላልቻልን ነው፤ ስለዚህ ነጥብ ማስቆጠር የምንችልበትን ዕድሎች መፍጠር ነው የሚጠበቅብን እንጂ ያቺ ስህተት ብቻ ቡድኑን ለሽንፈት ዳርጋዋለች ብዬ አላስብም። በእርግጥ በዛ ግብ ነው የተሸነፍበው፤ ግን ያ ብቻ አይደለም። ያ ከዘጠናው ደቂቃ አንዱ ክስተት ነው» ብለዋል።

በጋናው ግጥሚያ ቡድኑ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ማድረጉንም አሰልጣኙ አክለው ተናግረዋል። 46ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል ተቀይሮ ገብቷል። የአንድሬ አዩ እና ሌሎች ብርቱ ሙከራዎችንም ግብ ከመሆን አጨናግፏል። በዕለቱ ግጥሚያ ቡድኑ ያገኘውን በርካታ የግብ ዕድሎች ለውጤት አለማብቃቱንም እንደ ክፍተት እንደሚመለከቱ አሰልጣኝ ውበቱ ተናግረዋል።

የጋናውን ጨምሮ የብሔራዊ ቡድኑ ያደረጋቸውን ግጥሚያዎች በቅርበት የተከታተለው የሪፖርተር ጋዜጣ የአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ ስፖርት አዘጋጅ ዳዊት ቶሎሳ የነገው ጨዋታ ስኬታማ ይሆናል የሚል እምነት አለው።

በተለይ ደግሞ ቡድኑ ከፍተኛ ድጋፍ በሚሰጠው የባህር ዳር ስታዲየም ውድድሩን ማካኼዱ ለውጤት እንደሚያበቃውም አክሎ ገልጧል። ቡድኑን በመደገፍ የሚታየው ከፍተኛ መነቃቃት ለውጤት አጋዥ ነውም ብሏል።

ምስል DW/O. Tadele

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድቡን ጋና ከኢትዮጵያ ባገኘችው 3 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ ትመራለች። ግብ አልባዎቹ ደቡብ አፍሪቃ እና ዚምባብዌ አንድ ነጥብ አላቸው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለምንም ነጥብ እና 1 የግብ ዕዳ የምድቡ መጨረሻ ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት የነገው ግጥሚያ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እጅግ ወሳኝ የሚባል ነው። ቡድኑ ከጋና ጋር ባደረገው ግጥሚያ የታዩትን ድክመቶች ካሻሻለ ዚምባብዌ ላይ እና በመልሱ የጋና ግጥሚያም ነጥብ የማምጣት ሰፊ ዕድል አለው። ከምንም በላይ ቡድኑ በወኔ እንዲነቃቃ ከአሰልጣኝ፣ እስከ ደጋፊ፤ ከጋዜጠኞች እስከ እግር ኳስ አፍቃሪያን ልዩ ድጋፍ ያሻዋል እንላለን።

በሌሎች ዋና ዋና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የጀርመን ቡድን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ ምድቡን በመምራት ላይ ይገኛል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሐንሲ ዲተር ፍሊክ በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያቸውን ለሦስተኛ ጊዜ በማሸነፍ ሔትሪክ ለመሥራት ተቃርበዋል። ባለፈው ሐሙስ ቡድናቸው ሊሽተንሽታይንን 2 ለ0 አሸንፎ ነበር። ትናንት ደግሞ አርሜኒያን ሽቱትጋርት ከተማ ውስጥ 6 ለ0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ረትቷል።  ከአይስላንድ ጋር ከነጌ ወዲያ ረቡዕ ማታ ይጋጠማል።

ምስል Andre Penner/AP Photo/picture alliance

የብራዚል እና የአርጀንቲና የማጣሪያ ግጥሚያም ተጨዋቾች ወደ ሜዳ ከገቡ በኋላ በኮሮና ምክንያት ተቋርጧል። ከእንግሊዝ የመጡ የአርጀንቲና ተጨዋቾች በኮሮና ሕግ መሠረት ወደ ሜዳ መግባት አይፈቀድላቸውም ነበር ተብሏል። ሆኖም ተጨዋቾቹ በቀጥታ ወደ ስታዲየሙ በማቅናታቸው ሜዳ ውስጥ እንደገቡ በሀገሪቱ የጤና ባለሞያዎች ጨዋታው ተቋርጧል። ኹኔታው በርካቶችን አስደምሟል። አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ፦ «ጨዋታውን ለምን አስጀመሩት፤ ለምንስ ከአምስት ደቂቃ በኋላ አቋረጡት?» ሲል በቴሌቪዥን ለቀረበለት ቃለ መጠይቅ መልሷል። «እዚህ ስታዲየም ውስጥ ለአንድ ሰአት ያህል ነበርን ሊነግሩን ይችሉ ነበር» ሲልም ቅሬታውን ገልጧል።

በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ እንግሊዝ አንዶራን እንዲሁም ስፔን አጆርጂያን በተመሳሳይ 4 ለ0 አሸንፈዋል። ጣሊያን ከስዊትዘርላንድ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።  ቼክ ሪፐብሊክ በቤልጂየም የ3 ለ0 ሽንፈት ገጥሟታል። ከፍተኛ ግብ በተቆጠረበት ግጥሚያ ፖላንድ ሳንማሪኖን 7 ለ1 አሸንፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW