1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጳጉሜ 4 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2016

ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋ እንደተጫወተችው ከኮንጎ ዴሞክራ እግር ኳስ ቡድን ጋም ከሜዳዋ ውጭ ለመጫወት ተገዳለች ። ከመቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ባለው ሀገር አንድ ስታዲየም መገንባት ባይቻል እንኳን እንዴት በተገቢው መልኩ ማደስ ተሳነን? ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በአውሮጳ ኔሽን ሊግ ተጋጣሚውን 5 ለ0 አሸንፏል ።

የፓራሊምፒክስ አትሌቶች በፓሪስ ከተማ ውድድር ላይ
የፓራሊምፒክስ አትሌቶች በፓሪስ ከተማ ውድድር ላይምስል Alex Slitz/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በዛሬው የስፖርት መሰናዶዋችን በዋናነት ትኩረታችን በምሽቱ ስለሚኖረው  የኢትዮጵያ እና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እግር ኳስ ቡድኖች ግጥሚያ ይሆናል ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በአውሮጳ ኔሽን ሊግ ተጋጣሚውን 5 ለ0 አሸንፏል ። ሌሎች ግጥሚያዎችም ተከናውነዋል ። ዛሬ ምሽትም ነገም ጨዋታዎች ይኖራሉ ። ተጨማሪ ስፖርታዊ መረጃዎችን አካተናል ።

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በ2025 የሞሮኮ የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ማታ ከኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ጋ ያደርጋል ። ጨዋታው ከምሽቱ 4:00 ሰአት ላይ ታንዛንያ ዳሬ ሰላም ከተማ ቤንጃሚን ምካፓ ብሔራዊ ስታዲየም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጧል ። 

ቀደም ሲል  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የመጀመሪያ የማጣሪያ ግጥሚያውን ያከናወነው ከሜዳው ውጪ እዛው ታንዛኒያ ውስጥ ነበር ። ከታንዛንያ ቡድን ጋርም ባደረገው ግጥሚያ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይቷል ። ብሔራዊ ቡድናችን በተገቢ መልኩ በተገነባ ስታዲየም እጦት የተነሳ በሀገር ቤት በደጋፊው ፊት የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ለማድረግ አልቻለም ። የሔትሪክ ጋዜጣ መሥራች እና ዋና ሥራ አዘጋጅ ይሥሐቅ በላይ ለስታዲየም ግንባታ ትኩረት አለመሰጠቱ አሳዛኝ ነው ብሏል ።

ለተለያዩ ጉዳዮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ሲፈስሱ ይስተዋላል የሀገርን ስም ሊያስጠራ የሚችል ብሔራዊ ቡድን በደጋፊው ፊት የሚጫወትበት ስታዲየምን ለመገንባት ምንድን ነው ችግሩ? የድሬዳዋ ስታዲየም ማስተካከያ ተደርጎለታል ተብሎ አልነበር ምን ሆነ? ከመቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ባለው ሀገር ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ አንድ ስታዲየም መገንባት እንኳን ቢያቅት ማደስ ለምን አልተቻለም? ይህ የበርካቶች ተደጋጋሚ ጥያቄ ነው ። ይስሐቅ በስፖርቱ ዘርፍ በሚንስትር ደረጃ ሦስት ሚንስትሮች ሲቀያየሩ አንድም ስታዲየም  ፊፋ በሚያዘው መስፈርት ማደስ እንኳ አለመቻሉ አጠያያቂ ነው ሲል ጠቅሷል ።  የአስተዳደር ችግር መሆኑንም ገልጧል ። 

አሰልጣኝ ገብረ መድኅን ኃይሌ የብሔራዊ ቡድኑን የሚያሰለጥኑት የሀገር ውስጥ ቡድንን ከማሰልጠናቸው ደርበው ነው ይህ በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ላይ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል ለሚለው ጥያቄ ይስሐቅ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብሏል ። አሰልጣኙ በኃላፊነት የሚያሰለጥኑት የመድን ቡድንም ሆነ ሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኑ የሙሉ ጊዜ አሰልጣኝ ስላልተመደበለት በተለይ ብሔራዊ ቡድኑ ተጎጂ መሆኑንም ጠቅሷል ። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን መቼ ይሆን በሜዳው ዳግም የሚጫወተው?ምስል Omna Tadele/ DW

ከታንዛኒያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ያለምንም ግብ ከተጠናቀቀው ግጥሚያ ምን ትምህርት መውሰድ ይቻላል? ለአብነት ያህል፦ ብሔራዊ ቡድናችን ኳስን ባላጋራ ግብ ማድረስ ሲቸገር ዐይታይም ይልቁንም ኳሷን ወደ ግብ ሊቀይር የሚችል 9 ቁጥር ተጨዋች መጥፋቱን ከጨዋታው በኋላ በተደረገው ቃለ መጠይቅ ጋዜጠኞች ጠቁመው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌም አስተያየቱን አምነው ተቀብለዋል «በአጠቃላይ አጨራረስ ላይ ችግር አለብን ማለቴ ኳሷን ወደ ባላጋራ ግብ ክልል በማድረሱ ረገድ ምንም ችግር የለብንም በአጨራረስ ላይ ነው ችግራችን ቁጥር 9 ጥሩ አጥቂ የለንም ያው ግን እንደ ቡድን ለመጫወት እየሞከርን ነው » ብለዋል ከታንዛኒያው ግጥሚያ በኋላ በእንግሊዘኛ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ። 

የአውሮጳ ኔሽን ሊግ

በአውሮጳ የኔሽን ሊግ ግጥሚያዎች  የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የሐንጋሪ አቻውን 5 ለ0 በሆነ ውጤት ጉድ አድርጓል ። በቅዳሜው ግጥሚያ ለጀርመን አንድ ግብ ያስቆጠረው ጃማል ሙሳይላ ሦስት ግብ የሆኑ ኳሶችንም በማመቻቸት ብቃቱን ዐሳይቷል ። ጀርመን ዱይስልዶርፍ ከተማ በሚገኘው የሜርኩር ሽፒል አሬና ስታዲየም በነበረው ግጥሚያ ከጃማል ባሻገር፦ ኒክላስ ፉይልክሩግ ቀዳሚዋን ግብ አስቆጥሯል ። ፍሎሪያን ቪርትስ፤ አሌክሳንደር ፓብሎቪች እና ማሳረጊያዋን ደግሞ ካይ ሐቫርትስ በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ አሳርፈዋል ።

በአውሮጳ የኔሽን ሊግ ግጥሚያዎች የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የሐንጋሪ አቻውን 5 ለ0 በሆነ ውጤት ጉድ አድርጓል ምስል Gerhard Schultheiß/Jan Huebner/IMAGO

አንድ ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ ኔዘርላንድ ቦስኒያ ሔርዜጎቪናን 5 ለ2 አሸንፋለች ። ቀደም ባሉት ቀናት ከነበሩ እጅግ በርካታ ግጥሚያዎች የተወሰኑትን ለመጥቀስ፦ ስፔን ከሠርቢያ ጋ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። ዴንማር አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ የተሰናበተበት ስዊትዘርላንድን 2 ለ0 አሸንፏል ። ኖርዌይ ከካዛክስታን ጋ ያለምንም ግብ መለያየቷ ብዙዎችን አስደምሟል ። ፖርቹጋል ክሮሺያን 2 ለ0 ረትታለች ። ስኮትላንድ በፖላንድ የ3 ለ2 ሽንፈት አስተናግዳለች ። ቤልጂየም እሥራኤልን 3 ለ1 ስታሸንፍ፤ የፈረንሳይ በሜዳዋ በጣልያን 3 ለ1 መሸነፍ ደጋፊዋቿን አበሳጭቷል ። እንግሊዝ ወደ ደብሊን ተጉዛ በዴክላን ራይስ እና ጃክ ግሪሊሽ ግቦች አየርላንድን 2 ለ0 አሸንፋለች ።

የኔሽን ሊግ ግጥሚያዎች ዛሬም ቀጥለው፦ ፈረንሳይ ቤልጂየምን ታስተናግዳለች ። ጣሊያን እሥራኤልን ትገጥማለች ። ኖርዌይ ከኦስትሪያ ትፋለማለች ። በነገው ዕለት ከሚኖሩ ዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ ኔዘርላንድ ጀርመንን የምታስተናግድበት በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቅ ነው ።

የፓሪስ ፓራሎምፒክ ውድድር ትናንት በተደረገው ደማቅ የመዝጊያ ስነስርዓት ተጠናቋል ። ዋናተኛዪቱ ዓሊ ትሩዊት ለፓሪስ ፓራሎምፒክ ልምምድ ስታደርግምስል Julia Nikhinson/AP Photo/picture alliance

አትሌቲክስ

የፓሪስ ፓራሎምፒክ ውድድር ትናንት በተደረገው ደማቅ የመዝጊያ ስነስርዓት ተጠናቋል ። በመዝጊያ ስንስርዓቱ ብርቱው ዝናብ ሳያግዳቸው 4,400 አትሌቶች እና 168 የፓራሎምፒክስ ልዑካን የሙዚቃ ድግሱን ተካፍለዋል ።  ከፓራሎምፒክስ ቀደም ብሎ በነበረው የፓሪስ ኦሎምፒክስ ውድድር የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በብዙ ውዝግቦች እና አሳፋሪ ክስተቶች ከከዚህ ቀደሙ የደከመ ውጤት ይዞ መመለሱ ይታወቃል ። በአንጻሩ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው እና ድጋፍ ያላገኘው አካል የኢትዮጵያ የፓራሎምፒክስ ቡድን በዐዕነ ሥውራን እና በጭላንጭ በሚያዩ በጣት የሚቆጠሩ አትሌቶች እጅግ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ። ይህ እንደምን ሊሆን ቻለ? ጉዳዩ ሰፊ ክትትል እና ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ነው ።

ዑጋንዳዊቷ አትሌት ርብቃ ቼፕቴጌ በደረሰባት ጥቃት ባለፈው ሳምንት ሕይወቷ ማለፉ ብዙዎችን አሳዝኗል ። በፓሪስ ኦሎምፒክ ተካፋይ የነበረችው የማራቶን ሯጭ ሕይወቷ ያለፈው ፍቅረኛዋ ቤንዚን አርከፍክፎ ባደረሰባት ብርቱ ቃጠሎ አብዛኛው የሰውነቷ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላ መሆኑ ተዘግቧል ።

ማንተጋፍቶትስ ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW