የጸጥታ ስጋት ያጠላበት የበዓል አከባበር በኦሮሚያ ክልል
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11 2017
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚሰጠው ልዩ ትርጉምና እሴት ትልቁን ስፍራ የሚይዘው የትንሳኤ በዓል እጅጉን የሚጠበቅ የራሱ የሆነ ድባብ አለው፡፡ በዚህ በዓል የሩቅ ቤተዘመድ ከቅርቡ፣ ልጅ ከቤተሰቡ እና ወዳጅ ከዘመዱ ብዙ ርቀት ተጉዘውም ቢሆን መገናኝት፤ ለበዓሉም ቤት ያፈራውን አብሮ መቋደስ ወግ ባህል የሆነ ነውና በበርካቶች ይናፈቃል፡፡ ይሁንና በሀገሪቱ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ግጭት አለመረጋጋቱ በተስተዋለባቸው አከባቢዎች ይህን ማድረግ ቀርቶ ሰው እንደ ልብ በነጻነት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሱ ፈተና የሆነባቸው ቦታዎች ቀላል አይደለም፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ተወላጅ ወትሮም እንደ ትንሳኤ ያሉ ትላልቅ በዓላትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማሳለፍ ያስደስታቸው እንደነበርና ሁሌም እንደ ግዴታም የምመለከቱት መሆኑን በመግለጽ አሁን ግን ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ከተማ ወደ አከባቢው በመሄድ የለመዱትን ተግባር መከወን የማይበረታታ ነው ይላሉ፡፡ “በዚህ ዞን በርካታ ወረዳዎች በግጭት ምክንያት ልጅ ከወላጅ ጋር ከሩቅ መገናኘቱ ቀርቶ በአንድ አከባቢ የሚኖሩ ዘመዳሞች እንኳ እንደ ጥንት እንደልባቸው አብሮ በዓል ማክበር በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህም ምንድነው ከፀጥታው ይዞታ ተነሳ ነው ማለት ነው፡፡ የታጠቀው የትኛውም አካል በሚፈጥረው ችግር እና እነሱንም በመምሰል ቀንም ሆነ ማታ ህዝቡን ስለሚያሰቃዩ ማህበረሰቡ እንደልቡ በዓል ማክበር እና ለበኣል የሚውሉ ግብዓቶችን ማግኘት ከባድ ሆኖበታል፡፡ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው እንግዲህ ሰው እንደልብ ተንቀሳቅሶ ከቡተሰቡ ጋር በዓል እንዳያከብር እንቅፋት የሆነው” ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ የጸጥታ ፈተና ባለባቸው አከባቢዎች የበዓል ይዞታ
የኑሮ ውድነት ጫናን የወለደው የፀጥታ ችግር
በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ያለፉትን ሶስት-አራት ዓመታት በግጭት ውስጥ ያሳለፉ ሰለሞን የተባሉ ነዋሪ ከግጭት ማግስት ነገሮች ወደ ነባር ይዞታቸው እንዲመለሱ ጥረቶች ብታዩም አሁንም ጊዜ ሳይፈልግ አይቀርም ይላሉ፡፡ አቶ ሰለሞን የበዓሉን አከባበር ዝግጅት ተጽእኖ ከተወደደው የግብዓቶች አቅርቦት ይጀምራሉ፡፡
“የበዓል መዳረሻ ድባቡ ምንም አይልም ደህና ነው፡፡ ግን እኮ ፍየልና በግ የመሳሰሉ የበዓሉ ማድመቂያዎች እዚህ ውድ ነው በጣም፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ በግጭቱ ምክኒያት ሰው በሙሉ ወደ ከተማ ሸሽቶ ምርቱ የለምና አቅርቦቱ እጅጉን አናሳ ነው” ብለዋል፡፡
የተስፋ ጭላንጭል የታየበት የሰላሌ ሰላም ዳግም መደፍረስ
ሰለሞን አስተያየታቸውን ቀጠሉ እንደ ተለመደው በዓልን በጥሩ መንፈስ ማክበር አሁን ላይ ባይታሰብም፤ አከባቢያቸው በግጭት ከተናደባቸው ካለፉት አስከፊ ትዝታቸው በተሸለ አሁን ላይ ተስፋዎች መታየታቸውን አስረዱ፡፡ “እሱ እንኳን አይታሰብም፡፡ በዚህ ከኪረሙ የሚያልፍ የለም፡፡ በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ እኔ ከምገኝበት ሀሮ ቀበሌ ወደ አጎራባች ከተማ አገምሳ እንኳ መዝለቅ አስጊ ነው፡፡ እርጉዝ እንኳ ታማብህ ይዘህ ወጥተህ ሌላ ደህና ከተማ ማሳከም ብታስብ ትፈተናለህ፡፡ እንኳን በዓል እንደጥንቱ አብሮ ማክበር የቅርብ ዘመድ ሞቶብህ 60 ኪ.ሜ ገደማ ተንቀሳቅሰህ መቅበር ፈተና ነው” ይላሉ፡፡ ነገር ግን ብለዋል አስተያየት ሰጪው፡ በቅርቡ በተፈጠረው አንጻራዊ መረጋጋት ወደ ከተማ የሸሸው የገጠሩ ማህበረሰብ ተስፋ ኖሮት ወደ ገጠር ቀየው ተመልሶ እርሻውን ወደ ማረስ መመለሱ ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ የትንሳኤ በዓል በጉልህ እንደምክበርም በማንሳት ለዚሁም ማህበረሰቡ ባለው ሽር ጉድ እያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በፍጹም ነጻነትና ደስታ የሚያከብረው በዓል ግን ለማክበር በዚህ አከባቢ ጊዜው ገና ይመስላል፡፡ አቶ ሰለሞንም ይህን አረጋግጠውልናል፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ በፊት በህብረተሰብ መካከል የተፈጠረው ጥርጣሬና የብሔር ግጭት በሁሉም ማህበረሰብ የአብሮነት ፍላጎትና ስህተቶችን መረዳት ተስፋው አብቧል ባይ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ የመስቀል አከባበር ስነ ስርዓት እና የዘንድሮ የበዓል ስሜት
አንዳንድ ቦታዎች ላይ የተሻሻለ የመሰለው ፀጥታው ስጋት
ከዚሁ በግጭት ውስጥ ከቆየው ዞን ሌላኛው ወረዳ ጊዳ አያና አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም ሀሳባቸውን አከሉ፡፡ እንደ ወትሮውም በዓሉ ጊዜውን ጠብቆ መምጣቱን ብገነዘቡትም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በዓሉን ለማሳለፍ የተዘጋጁትን በርካቶች ያውቁአቸዋል፡፡ “ይህ አከባቢያችን እጅግ ጥሩ አከባቢ ነበር፡፡ በጉ፣ ፍየሉ፣ ከብቱ ዶሮው ሁሉም ይመረት ነበር እኛ ጋ፡፡ ተፈጥሮ በጸጋ የባረከችው አከባቢ ነበር፡፡ ፈጣሪ ምንም አልነሳንም፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ የለም፡፡ የነበረው ግጭት በማህበረሰቡ እጅ የነበረውን አውድሟል፡፡ ህዝቡ በእጅ ላይ የለው የሚገዛበት ነገር ይቸግረዋል፡፡ እና ሳይቀምስ እንኳ በዓሉን የሚያሳልፍ ይኖራል፡፡ ህብረተሰቡ አሁን ቀን የሚገፋው በእርዳታ ነው፡፡ እናም በዓል አይመስልም እኛጋ፡፡ በጣም ነው የሚከፋን፡፡ አያት ቅድመአያታችን አይተው የማያውቁ ዶፍ እኮ ነው የወረደብን፡፡ ከችግር ጋር ተገናኝተን አናውቅም ነበር፡፡ ድርቅ አናውቅ ርሃብ የለም ነበር፡፡ አሁን ግን ማህበረሰባችን አይቶ በማያውቅ ችግር ይሰቃያል፡፡ ከእጁ ያለው ጠፍቶበታል፡፡ ውሎ አዳር የለው፡፡ ታውቃለህ ስታስታውሰው አገር ጥለህ ጥፋ ያስብላል በጣም ነው የሚያሳዝነው” ሲሉ ሃሳባቸውን አብራርተዋል፡፡
ወትሮም እንደ ትንሳኤ ያለው አውዳመት በኢትዮጵያ ቤተሰብን በእጅጉ የሚያገናኝ ነውና ልጅ ከከተማ ወደ ገጠር እየሄደ ቤተሰብ መጠየቅም ወግ ነበር፡፡ አሁን ለዚህ እንዳልታደሉ የሚገልጹና የቤተሰቦቻቸውን ደጅ ከረገጡ ዓመታት ያስቆጠሩ ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ላለፉት ጢቂቀት ዓመታት አስከፊ የተባለው ግጭት የህዝቡን ማህበራዊ መስተጋብር ከናደባቸው አንዱና ዋነኛው በሆነው የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን (ሰላሌ) ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት የተሸለ ተስፋ ተስተውሏል የሚሉት በዞኑ የደብረጽጌ ከተማ ነዋሪ በትንሳኤ ጸሎታቸው በሙሉ ሰላሙ እንዲጸና ነው፡፡ “ሰላም ነው እግዚአብሔር ይመስገን የተሻለ ነገር አለ፡፡ ፈተናው ትንሽ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ነው እንጂ ሰላሙ መልካም ነው የበለጠ ሰላሙ እንዲጸናልን ደግሞ እግዚአብሔርን እንማጸናለን” ሲሉ ተስፋቸውን አጋርተውናል፡፡
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ