1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫና የሕግ ምሁር አስተያየት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 23 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት ጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በህቡዕ ተደራጅተው የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ተገኝተዋል ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ትናንት አመሻሽ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በመግለጫው ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ ግን በሕግ አፈጻፀሙ ሳይ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

Äthiopien | Straßen in Addis Abeba
ምስል Solomon Muchie/DW

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግሥት ጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በህቡዕ ተደራጅተው የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ተገኝተዋል ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ትናንት አመሻሽ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። ግብረ ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹን ከበርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም ከሳተላይት መገናኛ መሣሪያዎች እና የተለያዩ መረጃዎችን ከያዙ ላፕቶፖች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም ገልጿል። የተጠርጣሪዎቹን ማንነት በስም ጭምር የዘረዘረው የጋራ ግብረ-ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹን የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን የግድያ ዒላማ በማድረግ፤ ክልሉን እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመቆጣጠር ያልማሉ ሲል ከሷልም። በመግለጫው ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ ግን በሕግ አፈጻፀሙ ሳይ ጥያቄዎችን አንስተዋል። 

መንግሥት በዚህ መግለጫው «የአማራን ህዝብ የማይወክሉ» ያሏቸውና በጽንፈኝነት የፈረጃቸው መንግሥት ለተለያዩ ግጭቶች ሰላማዊ አማራጭን እንደ መፍትሄ ማቅረቡን በመግፋት ከሷቸዋል። የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ፤ «የጽንፈኛ ኃይሎች» ያላቸው ኃይሎች የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የኢንተለጀንስ፣ የፋይናንስ እና የሚዲያ ክንፍ በተለያዩ የውጭ ሃገራት ከሚገኙ 16 «ጽንፈኛ» ካሏቸው የዲያስፖራ አባላት ጋር ትስስር በመፍጠር በሚያገኛቸው የሎጀስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፎች በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂዎችን በመመልመል፣ በማሰልጠን እና አስታጥቆ እንደሚያሰማራ በተደረገ ክትትል እና ምርመራ ተደርሶበታል ብሏል።

ግብረኃይሉ ለዚህም ማሳያ አድርጎ ካቀረባቸው ጉዳዮች ሰሞኑን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩ አቶ ግርማ የሺጥላን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር መገደላቸውን ነው። በ130 የአማራ ክልል ወረዳዎች ተመለመሉ ያሏቸው 450 ግለሰቦች በክልሉ መሰማራታቸውም በዚህ መግለጫ ተጠቅሷል። በዚህ መግለጫ ላይ የግል ምልከታቸውን ለዶቼ ቬለ ያጋሩት የዓለም አቀፍ ሕግ አዋቂ አቶ ባይሳ ዋቅዎያ፤ «በመግለጫው ይዘትና ወቅታዊነት ላይ ብዙም አሻሚ ነገር ባላገኝበትም፤ የወጣው መግለጫ ምን ያህል ተፈጻሚ የሚሆን ነው የሚለው ጥያቄ ፈጥሮብኛል። መንግሥት ሰብዓዊ መብትን ባልጣሰ መልኩ ሕግ ማውታትና የጠረጠረውን ሰው መጠየቅ ይችላል። ግን እነዚህ ተጠርጣሪዎችን ለህዝብ ይፋ ስናደርግ በደንም ተጠንቷል ወይ የሚለውን አሁንም በጥያቄ ነው የማነሳው» ብለዋል።

የመንግሥት የትናንቱ መግለጫ «ጽንፈኛ ኃይሎች» ያሏቸውን ግለሰቦቹን የሀሰት ወሬዎችን በመፍጠር እና ከፍተኛ የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ህዝብን በብሔር እና በሃይማኖት ከፋፍሎ በማጋጨት ጥረትም ከሷል። ግለሰቦቹ ላይ በሽብርተኝነትም  ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን በመግለጽ፡ ከሚኖሩባቸው ሃገራት በዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) እንዲሁም  ከሚኖሩባቸው ሃገራት መንግሥት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር ተመሠረቱ በተባሉ የትብብር ማዕቀፎች ወደ ሀገር ቤት ተላልፈው በሕግም እንዲጠየቁ እየተሠራም ነው ተብሏል። የዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያው አቶ ባይሳ ዋቅዎያ ግን በዚህ ሃሳብ ተፈፃሚነት ላይ እምብዛም አይስማሙም። «እኔ እስከማውቀው ድረስ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ላይ በመሳተፍ የተጠረጠሩ ካልሆነ የተለየ የአጋራት ስምምነት እስከሌለ ድረስ በዚህ አይነት መልኩ ተጠርጣሪውን አሳልፎ የመስጠቱ ተግባር እምብዛም በዓለማችን አይስተዋልም። ያ እስከሆነ ደግሞ ተፈፃሚነቱ የሚያጠራትርን ነገር በመግለጫ ማውጣቱ ጥቁሙ ብዙም አይገባኝም።»

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ ግን፤ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ተፈላጊዎች ከውጭ ሀገር በሚያገኙት እና በሀገር ውስጥ ባላቸው ሀብት ወንጀል ስለሚሠሩ፤ በሀገር ውስጥ ያላቸውን ሀብት የመለየት እና በሕግ የመቆጣጠር ሥራ እንደሚሠራ አስታውቋል። ግብረኃይሉ እነዚህን አካላት በስም ካልጠቀሳቸው የኢትዮጵያን አንድነት ከማይፈልጉ የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በቅንጅት በመሥራትም ከሷል። የሕግ ባለሙያው አቶ ባይሳ እንደሚሉት ግን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው፤ አስተማማኝ የሕግ ስርኣት በመዘርጋት እና በእርቅና መግባባት የሚያልቁ ጉዳዮችን በዚያው በመጨረስ ነው። ባለፈው ሳምንት ውስጥ ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መገደላቸውን ተከትሎ፤ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ በሀገር ውስጥና በውጭ ሃገራት በህቡዕ ተደራጅተውና ተቀናጅተው በሚንቀሳቀሱ «ጽንፈኛ» ባላቸው ኃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን በሚያዚያ 20 2015 ዓ.ም መግለጫው ማሳወቁ ይታወሳል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW