1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 29 2015

«በቁጥጥር ሥር ማዋሉ የሚበረታታ ሆኖ ሳለ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ኬላዎች አልፎ ይህ ሁሉ የጦር መሣሪያ ወደ ከተሞች የገባበት ሁኔታ አልገባኝም ? » «ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገደል ሲፈናቀል በተለይ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል በቁሙ ሲያቃጥሉት ዝም ተብሎ አሁን ባለስልጣን ሊገሉ ሲሉ በቁጥጥር ሥር አዋልናቸዉ ሲባል አያስተዛዝብም?»

Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Seyoum Getu/DW

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፤የዶክተር ጫላ ያለመከሰስ መብት መነሳት፤አዲሱ የትግራይ ካቢኔ

This browser does not support the audio element.

«በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት በመፈጸም ሁከት እና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ሲንቀሳቀሱ ነበር »የተባሉ ቡድኖች  በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሳምንት ነበር ያስታወቀው ።የሀገሪቱ የፀጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብር ኃይል በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች “በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በአዳማ እና በድሬዳዋ ከተሞች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች በመፈጸም አገራዊ ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ ነበር” ብሏል። ጥቃቱን ለመፈጸም በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልሎች መቀመጫቸውን ያደረጉ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶችን እና የማኅበረሰብ አንቂዎችን የያዘ ህቡዕ መዋቅር በምስጢር ሲንቀሳቀስ ነበርም ብሏል። በዚህ የግብረ ኃይሉ መግለጫ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ከመካከላቸው ዘለፋ ያካተቱትንና የሰዎችን ክብር ዝቅ የሚያደርጉትን ወደ ጎን ትተን ቀሪዎቹን እንቃኛለን።
ታረቀኝ ታረቀኝ በፌስቡክ «ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገደል ሲፈናቀል በተለይ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል በቁሙ ሲያቃጥሉት ዝም ተብሎ አሁን ባለስልጣን ሊገሉ ሲሉ በቁጥጥር ሥር አዋልናቸዉ ሲባል አያስተዛዝብም? ብለዋል።የአስቻለው ክንዱ  መልዕክትም «ምሁራንን ሰብስቦ አስሮ "ባለስልጣን ለመግደል ብጥብጥ ለማስነሳት " የሚል ታፔላ መለጠፍ መንግስትን ትዝብት ላይ ይጥላል ይላል። «ምሁራንን ማሳደድ ተቀባይነት የለውም» በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት  ወርቁ ወርቁ በፌስቡክ «ምሁራን በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ግፍ ስለሚያጋልጡ የሚደረግ ሴራ ነው» ካሉ በኋላ  ባስቸኳይ ፍቱአቸው በማለት ጥሪ አቅርበዋል። እስራኤል ጎሹ ወንድምነህም «ፍትህ ለንጹሀን እስረኞች! ። በአስቸኳይ ይፈቱ ሲሉ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል።አክሊሉ ተሻገር «ወንጀል የሠራ ሠው ጥላውን አያምነውም እንኳን እነዚህ ሙህራኖችካሉ በኋላ .እውነት በዕሥር አይታፈንም እያደር ፈንቅሎ ይወጣል እንጂ በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። 
ግብረ ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹ በተቀናጀ መልኩ ህቡዕ ወታደራዊ ክንፍ በማደራጀት በጦር መሣሪያ የታገዘ የከተማ ላይ ጥቃት የመፈፀም እቅድ ነበራቸውም ብሏል። በህቡዕ አመራሮች የተዋቀረ ያለው የአዲስ አበባው የአደረጃጀቱ ክንፍ በየክፍለ ከተማው ለዘረጋው መዋቅሩ በርካታ የተለያዩ የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያዎች፣ተቀጣጣይ ፈንጂዎችና ቦምቦችን ወደ ከተማዋ ማስገባቱንም የጋራ ግብረሐይሉ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ዘውዱ ቲጉዲሳ በፌስቡክ  «በቁጥጥር ሥር ማዋሉ የሚበረታታ ሆኖ ሳለ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ኬላዎች አልፎ ይህ ሁሉ የጦር መሣሪያ ወደ ከተሞች የገባበት ሁኔታ አልገባኝም ? ሲሉ ጠይቀዋል።መስፍን ግርሙ የመንግሥትን ርምጃ «በጣም ጥሩ ስራ ነው» ሲሉ አድንቀዋል።« የዛሬውን በጣም ተአማኒ የሚያደርገው ከነሥም ዝርዝራቸው መቅራቡ ነው ይበል ያሰኛል። ካሉ በኋላ አሁንም በሁሉም ቦታ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።የመንግስት ከፍተኛ በለሥልጣኖችም በደንብ ቢፈተሽ ጥሩ ነው።ምክንያቱም ይህ ኃይል ብቻውን አይደለም።ትኩራት ይሰጥ።በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል። 
  የጋራ ግብረ ሐይሉ መግለጫ በህቡዕ አደረጃጀቱ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሂደት በተቀናጀ መንገድ መቀጠሉን አመልክቷል። 
በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ቀልብ ከሳቡ ጉዳዮች ውስጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ሳምንት ማክሰኞ የቀድሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የዶ/ር ጫላ ዋታን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ነው። የምክር ቤት አባል ዶክተር ጫላ ዋታ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት የመንግሥት የግዢ ሕግ ከሚፈቅደው አሰራር ውጪ የ195 ሚሊዮን ብር ግዢ ገንዘብ ሚኒስቴር ሳያውቀው በቀጥታ በመፈጸም፣ለተቋሙ የውስጥ ገቢ ማስገኛ በሚል ሕጋዊነት የጎደለው አማካሪ ድርጅት በማቋቋም ከፍተኛሙስና ፈጽመዋል በሚል በመጠርጠራቸው ያለመከሰስ መብታቸውን ምክር ቤቱ አንስቷል። የዶክተር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብት መነሳት ላይ በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ይቶሬ ይቶሩ አማራ በሚል የፌስቡክ ስም በፌስቡክ የሰፈረ አስተያየት ይገኝበታል።« የመንግሥትን ተቀባይነት ከሚሸረሽረዉ ዉስጥ አንዱ የህግ የበላይነትን አለማሥከበር ነዉ ሥለሆነም የተጀመረዉ የጸረ -ሙሥና ትግል ጥሩ ነዉ በሌላዉም የመንግሥት አስፈጻሚ ላይ ተጠናክሮ መሔድ አለበት።ይላል።ኢትዮ እዮብ «በአራት ዓመት ውስጥ ይህን ያህል ዘረፋ የሚገርም ነው ሲሉ ወሴ አህመድ ደግሞ እሳቸው ስለተደረሰባቸው እንጂ ያልተነቃባቸው ብዙ አሉ በማለት አሳስበዋል፤ ወገኔ ሙሉጌታ ጥሩ ውሳኔ ነው በማለት አድናቆታቸውን ሲገልጹ ሀቢብ ሀሰን ግን  «የመጨረሻዉ ዘመን ሲቃረብ ትልቁ ሌባ በትንሹ ሌባ ላይ ክስ ይመሰርታል! ሲሉ ተሳልቀዋል። አዲና መለስ ደግሞ መከሰስ አለባቸው የማንኛዉም ሰው ባንክ አካዉንት ይፈተሺ» የሚል ማሳሰቢያ  አካፍለዋል 
 የማቴዎስ ደርሶ ሀሮ ሀሳብ ደግሞ የለተየ ነው። ጉዳዩ የፖለቲካ ይዘት ስላለዉ ክሱን እንቃወማለን ብለዋል ።  ሚኪያስ ሰሎሞን ጫላ ብቻ አይደሉም ፤በሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ተመሳሳይ ሙስና አለ ሲሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። አበበ መኩሪያ «በስርዓቱ ውስጥ አስፈፃሚ እና የሕግ አውጭነትን ማደባለቅ ትልቁ ስህተት!  የፓርላማ አባላት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ወይም ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሆነው ይሰራሉ። ይህ ስርዓቱን እንዲበላሽ ያደርገዋል» ሲሉ በርሳቸው አስተያየት የችግሩ ምንጭ ያሉትን ስህተት ለማስረዳት ሞክረዋል። ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የምክር ቤት አባል ዶክተር ጫላ በዚህ ሳምንት ረቡዕ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፍትሕ ሚኒስቴርን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አወል ሱልጣንን ጠቅሶ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በፌስቡክ ገጹ ዘግቧል። 
በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች ውስጥ አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉትን ካቢኔ በዚህ ሳምንት ይፋ ማድረጉበአዲሱ ካቢኔ ሌተና ጄነራል ታደሰ ወረደ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል። ሌተና ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ፣ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነዋል። አዲሱ የተዋቀረው   ከህወሓት፣ ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራን እና ከባይቶና ፓርቲ ከተውጣጡ አባላት ነው ተብሏል። አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ይፋ በሆነበት እለት ላለፉት አምስት ዓመታት የትግራይ ክልልን ያስተዳደሩት ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ስልጣናቸውን አዲስ ለተሰየሙት ለአቶ ጌታቸው ረዳ በይፋ አስረክበዋል። በአዲሱ የትግራይ ክልል ካቢኔ አወቃቀርና በስልጣን ርክክቡ ላይ  ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል የበገና ዳባ አጭር መልዕክት ይገኝበታል። «ሰላም ፍቅር ይቅርታ እና እርቅን የሚመስል ነገር አለ ወይ ?»ይላል ጂግሳ ዋታ ደግሞ ስለ ስልጣን ሽግግሩ በሰጡት አስተያየት ፤« ይህ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ከአንድ ግለሰብ ወደሌላ ግለሰብ የተሸጋገረበት አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው።  ብለዋል። ጌታቸው ማሞ በፌስቡክ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ስጋታቸውም ሁለት ከፍተኛ ጀነራሎች በምክትል ፕሬዝዳንትነት መሾማቸው ነው። «የትግራይ ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር 2 ጄኔራሎችን ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾሟል፣ ጄኔራሎችን ለምን መረጣቸው ?  የሚል ጥያቄ ካስቀደሙ በኋላ አንድ ግዙፍ ዓላማ እንዳለ መለያ ነው፣ በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
«የገረመኝ ቆይ ትግራይ ውስጥ ወጣት የተማረ ዘመናዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው የለም እንዴ? ይህ የዜድ ጃማር ጥያቄ ነው።ባንተጊዜ ጌትነት በሚል የፌስ ቡክ ስም «እኔ እምለው አሁንም እራሳቸውን ነው የሚሾሙት እንዴ? ይላል።

ምስል Million Hailesilassie/DW
ምስል Solomon Muchie/DW

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW