1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታ ስጋት ሆኖ የቀጠለው የጉጂ እና ምሥራቅ ቦረና ዞን መዋቅር

ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 2015

በኦሮሚያ ክልል ከወራት በፊት ምሥራቅ ቦረና የሚል አዲስ የዞን መዋቅር መፈጠሩን ተከትሎ የተነሳው ውዝግብ አሁንም መቋጫ አለማግኘቱ እየተነገረ ነው። የዞን መዋቅሩ አሁን ወደ ተግባር መግባት መጀመሩ በጉጂ ዞን ስር የነበረው ጎሮ ዶላ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ሳምንት የተነሳው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው ነዋሪዎች የሚገልጹት።

Äthiopien Unruhen in der Zone Guji im Regionalstaat Oromia in der Stadt Guji
ምስል Private

በጉጂ ዞን የቀጠለው አለመረጋጋት

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ከወራት በፊት ምሥራቅ ቦረና የሚል አዲስ የዞን መዋቅር መፈጠሩን ተከትሎ የተነሳው ውዝግብ አሁንም መቋጫ አለማግኘቱ እየተነገረ ነው። የዞን መዋቅሩ አሁን ወደ ተግባር መግባት መጀመሩ በጉጂ ዞን ስር የነበረው ጎሮ ዶላ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ሳምንት የተነሳው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው ነዋሪዎች የሚገልጹት። ከጉጂ ዞን ወደ ምሥራቅ ቦረና ከተጠቃለሉ ወረዳዎች አንደኛው በሆነው በዚህ በጎሮ ዶላ ወረዳ የቀድሞ የወረዳው አመራሮች እየታደኑ ለእስር መዳረጋቸው ትልቁ የቅሬታው ምንጭ ነውም ይላሉ ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው። 

ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ይቆይ ብለው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የጎሮ ዶላ ነዋሪ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ውጥረት ውስጥ የገባው የአካባቢው ፀጥታ አሁንም መቀጠሉን አውስተዋል። እንደ አስተያየት ሰጪው የውጥረቱ ዓቢይ ምክኒያት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የተጠናከረው የወረዳው የቀድሞ አመራሮች እስራት ነው። «የምሥራቅ ቦረና ዞን መዋቅር መዘርጋትን ተከትሎ ጉጂ ማኩረፉ መቼስ ሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡ ይህንን እኛ በኃይል የሚጫንብን ግፊት ነው የሚል እምነት ኒኖረንም በግድ ይፈጸማል ብለው እየገፉት ነው። ድብደባ እና እስራት አለ። አሁንም ሕዝብ የሚወዳቸው አንድም ቀን ሕዝብ ላይ ችግር ያላደረሱ አመራሮች እየታሰሩ ነው። ከዚህ በፊት የወረዳው አስተዳዳሪ እና ምክትላቸው ታስረው ነበር። ዛሬ ደግሞ የወረዳው ጸጥታ አስተዳደር የነበሩት አብዲ ቦሩን ጨምሮ ሌሎችም ታስረዋል። አሁን የምናስተውለው ሕዝብ የማያውቃቸው አመራሮች በእነዚያ በታሰሩት መሪዎቻችን እየተተኩ፤ ማስፈራሪያም እየቀጠለ ነው» ብለዋል።

የጉጂ ዞን ወቅታዊ የጸጥታ ይዞታምስል Private

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ውሳኔ ከአራት ወራት በፊት መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ላይ በተለያዩ አካባቢዎች አዲስ መዋቅር ሲዘረጋ ከቦረና፣ ጉጂ እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳውች ተቀናጅተው  ምሥራቅ ቦረና ዞን በሚል አዲስ ዞን መመስረቱን ተከትሎ የሰው ሕይወት የነጠቀ ተቃውሞ ጭምር በተለይም በጉጂ ዞን በተለያዩ ከተሞች መደረጉ አይዘነጋም። ከጉጂ ዞን በዚህ ላይ ቅሬታቸውን የሚያሰሙ ነዋሪዎች ውሳኔው ሕዝብን አስቀድሞ ያላማከረ ነው ሲሉም ተቃውሟቸውን ያሰማሉ። ዛሬ ከጎሮ ዶላ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላኛዋ የሀርቀሎ ከተማ ነዋሪ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች እስራቱ ቀጥሏል በማለትም ያማርራሉ። «ሰው አድኖ ማሰር ቀጥሏል። መንገዶች ሁሉ እንቅስቃሴ አልባ እንደሆኑ ለቀናት ቀጥለዋልም። መንግሥት ሕዝቡን ቢሰማ መልካም ነው።» … እንደ እኝህ አስተያየት ሰጪ አሁን በጉጂ ዞን ያለመረጋጋቱ ችግሩ ከቦሬ ጀምሮ እስከ ነጌሌ ከተሞች ጎልቶ ይስተዋላል። «በጎሮ ዶላ ወረዳ አሁን ላይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ዝግ ናቸው» ብለዋል። በጎሮ ዶላዋ ከተማ ሃርቀሎ ዛሬ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይስተዋልም ነው  ነዋሪዎቹ ያመለከቱት።

በገሮ ዶላ የሀገር ሽማግሌ መሆናቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ነዋሪም፤ አሁን በሀርቀሎ ከተማ በነገሰው ውጥረት ከተማውን ለቀው መውጣታቸውን በመግለጽ፤ በአካባቢው ነግሷል ስላሉት ውጥረት አስረድተዋል። «አዲሱን የዞን መዋቅር ሕዝቡ ተቃውሟል። ይህን የሕዝብ ተቃውሞ ያቀናጁት የመንግሥት ሠራተኞች እና የወረዳው ካቢኔ ናቸው እየተባለም በርካቶች እየታደኑ ታስረዋል። የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎችም አሉ። አሁን አድማ ተደርጎ እንቅስቃሴ ሁሉ ተገቷል። ከአዶላ ወዲህም ተሽከርካሪዎች እያለፉ አይደለም።» አሁን ከደቂቃዎች በፊት የጎሮዶላ ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊን ጨምሮ የተቀሩትን ከሀርቀሎ ከተማ ይዘው ወደ ነጌሌ ፖሊስ መምሪያ ወስደዋቸዋል። ከዚህ በፊትም ክፉኛ ሕዝቡን ያስቆጣው የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ ለሕዝብ ይቆረቆራሉ ተብለው የሚታመኑ የወረዳው አመራሮች መታሰራቸው ነበር። እነሱ አሁንም በእስር ሁለተኛ ሳምንት እያስቆጠሩ ነው።፡ ከዚህ በፊት ከመንገድ ላይ ታፍሰው የታሰሩ 45 ሰዎች ግን ከትናንት በስቲያ ነው የተለቀቁት። አዲሱ ዞን ምሥራቅ ቦረና አሁን ህዝቡ ያላመነባቸው አመራሮች ነው እየሾሙ ያሉትና መቃቃሩ እንደቀጠለ ነው።»

የጉጂ ዞን ወቅታዊ የጸጥታ ይዞታምስል Private

ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው በዚህ በጎሮ ዶላ ወረዳ በቀጠለው ውጥረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ከመሆናቸውም ባሻገር በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በጸጥታ ኃይሎች ይፈጸማል ያሉትን ወከባ ሽሽት ከከተማ እሸሹ ነው። «በተለይም የመንግሥት ሠራተኛ እና ካቢኔዎች እስር ሽሽት ከከተማ እየወጡ ነው። አንዳንዱም ወደ ጫካ እንዳይሸሽ በዚያም ሸነ የሚባሉ ታጣቂዎች ስላሉ ያንንም ፍራቻ ቤቱ ውስጥ በሩን ዘግቶ የተቀመጠ አለ። እኔ ራሴ በአካባቢው የታወቅኩ የሀገር ሽማግሌ ብሆንም የዞን መዋቅሩን በመቃወሜ ብቻ ስለምፈለግ ከተማውን ለቅቄ ወጥቻለሁ። እንደ ወረዳ የሕዝቡ ጥያቄ አንድ ነው። ጎሮ ዶላ ከምሥራቅ ቦረና ይልቅ ጉጂ ስር ትተዳደር የሚል። ለዚህ ደግሞ አንዱ መፍትሄ የቀድሞ አመራሮቻችንን ወደ ሥልጣናቸው መመለስ ነው።»

በዚህ አካባቢ ስለተነሳው ውዝግብ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ለአዲሱ ዞን ምሥራቅ ቦረና ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጁራ ኦዳ እና ለጎራ ዶላ አዲስ የወረዳ አስተዳዳሪ ጌቱ ጩሉቄ ጋር ደጋግመን ብንደውል፤ በእጅ ስልካቸው ላይም የጽሑፍ መልእክት ብንልክም ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም።  አካባቢውን እያወዛገበ ያለው አዲስ የዞን መዋቅር ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤም አንዱ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ነበር። አንድ የጨፌ አባል በዚያ አከባቢ ሕዝብ እያወዛገበ ያለው ጉዳይ በድጋሚ ቢታይ ብለው አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ በጨፌ ኦሮሚያ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ፍቃዱ ተሰማ እና የክልሉ ፕሬዝዳት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የአዲስ ዞን አወቃቀሩ ያስፈለገው ለሕዝብ አንድነትና ምቹ የጸጥታ ሁኔታን ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን በመግለጽ፤ የሚቀለበስ ውሳኔ እንደሌለም ማስረዳታቸው ይታወሳል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በዚህ ዓመት መጋቢት ወር አጋማሽ ከቦረና፣ ባሌ እና ጉጂ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን አቀናጅቶ ምሥራቅ ቦረና የሚል ዞን መመስረቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ግን በተለይም ከጉጂ ዞን የተነሳው ተቃውሞ አሁንም ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። ይህ አዲስ የዞን መዋቅር ከቦረና ዞን ሞያሌ፣ ጉጂ እና ዋጪሌ ወረዳዎችን እንዲሁም ሞያሌ ከተማን፤ ከጉጂ ዞን ሊባን፣ ጉሚ ኤልደሎ፣ ጎሮዶላ ወረዳዎች እና ነጌሌ ከተማን፤ እንዲሁም ከባሌ ዞን መዳወላቡ፣ ኦቦርሶ እና ሃራና ቡሉቅ ወረዳዎችን ያካተተ መሆኑም ተገልጾ ነበር፡፡ አስቀድሞ የጉጂ ዞን መቀመጫ ሆኖ ለዓመታት ያገለገለውና ሙግት ሲነሳበት የነበረው ነጌሌ ከተማ በአዲሱ መዋቅር የምሥራቅ ቦረና ርዕሰ ከተማ ሆኗል፡፡ በአዲሱ መዋቅር መሠረት የጉጂ ዞን ርእሰ ከተማ ደግሞ ወደ አዶና ሬዴ ከተማ ተዘዋውሯል፡፡

የጉጂ ዞን ወቅታዊ የጸጥታ ይዞታምስል Private

 

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW