“የፀጥታ ችግሩን ተከትሎ በአማራ ዝርፊያና እገታ ተባብሷል” አብን
ማክሰኞ፣ መስከረም 27 2018
በአማራ ክልል የሰዎች እገታ፣ የዝርፊያና የግድያ ወንጀሎች መበራከታቸዉን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ።ንቅናቄዉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሚደረገዉን ግጭት «እንደመልካም አጋጣሚ የቆጠሩትና የክልሉን ህዝብ ለማጥፋት ይሰራሉ» ያላቸው ፤ ህወሓትንና ሻዕቢያን” በቀጥታና በተዘዋዋሪ በግጭቱ እየተሳተፉ ነው ሲልም ከስሷል።ሥለ ክሱ ከህወሓት በኩል አስተያየት ለማግኘት ወኪላችን ያደረገዉ ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።አብን ግን መንግሥት፣ የታጠቁ ኃይሎችና ባለድርሻ አካላት አለመግባባቶችን በውይይት እንዲፈቱ ጠይቋል።ዓለምነዉ መኮንን
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ በወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ከሁለት ዓመታት በፊት በአማራ ክልል የተከሰተው የፀጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ ህብረተሰቡን ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎታል፡፡ አብን በመግለጫው፣ “የእገታ፣ የዝርፊያና የግድያ ወንጀሎች ተበራክተዋል” ብሏል፡፡ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ውጪ መሆናቸውን ያመለከተው የአብን መግለጫ፣ ነጋዴዎች ንብረታቸውን በእገታና በዝርፊያ እንደተወሰድባቸው ገልጧል፣ ህክምና የሚፈልጉ በርካታ ታካሚዎችም በህክምና እጦት ህይወታቸው እያለፈ መሆኑ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
“ማህበራዊ ቀውሱ ተባብሷል” የአብን መግለጫ
ክልሉ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡን የአብን የፖልቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ፣ “ ክልሉ የጠላት ማራገቢያ ሆኗል፣ ታሪካዊ ጠላቶች ድል በሚያደርጉበት ሁኔታና የአማራ ህዝብ ደግሞ በሚዋረድበት ሁኔታ እየተከናወነ ያለ የእገታ፣ የዝርፊያና የግድያ ወንጀሎች፣ አለመማር፣ የጤና መታወክና የማህበረሰብ ቀውሶች የተብራከቱበት ክልል እየሆነ መጥቷል፡፡” ብለዋል፡፡
የክልሉን የሰላም መደፍረስ እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠርህወሓትና ሻዕቢያ የአማራን ህዝብ ለማጥፋትና ለማደናቀፍአቅደው እንደሚንቀሳቀሱ አብን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ ይህም ለክልሉን ህዝብ የደህንነት ስጋት፣ የኢኮኖሚ ደቀትና ለህልውና አደጋ እንደአጋለጠው ነው መግለጫው ያመለከተው፡፡
ሰለቀረበበት ክስ ከህወሓት ጽ/ቤት አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ ያደረግሁት ጥረት “የሚመለከተው አካል ይደውልልሀል” የሚል ምላሽ ከጽ/ቤቱ ቢነገረኝም፣ የተባለውን አካል ዛሬ ከቀኑ 9፡00 እስከ ቀኑ 11፡00 ድርስ ብንጥብቅም ሊደውል ባለምቻሉ የህወሓትን አስተያየት ማካተት አልቻልሁም፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው እንደሚሉት የአማራ ክልል የጦርነት ኢኮኖሚ የሚያራምዱ አካላት መናኸሪያ እንዳደረጉት አመልክተዋል፡፡
የአማራን ክልል የጦርነት አውድማ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ አካላት ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የፖልቲካ ጉዳዮች ኃላፊው ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ይገልፃሉ፡፡
“
“ወላዋዮች” የፀጥታ ችግሩን አባብሰውታል ስለመባሉ” ዳምጠው ተሰማ የአብን የፖልቲካ ጉዳዮች ኃላፊ
ከመንግሥት ወይም ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ያልሆኑ ሚናቸው የማይታወቅ ኃይሎች የየፀጥታው ችግር እንዲባባስ እያደረጉ ያሉ አካላት መኖራቸውን ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተናግረዋል፣ እንዴት ስንል ጠይቀናቸዋል፡፡”እየወላወለ ያለ ከተቃዋሚም ከመንግሥትም ያልሆን፣ ጠዋት ጠዋት ከመንግሥት ሌላ ጊዜ ደግሞ ከተቃዋሚ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት የፀጥታውን ችግር እያባባሱት በመሆናቸው ከድርጊታቸው ይቆጠቡ ነው ያሉት፡፡
የግጭትና የጦርነት ፖለቲካ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም ያለው የአብን መግለጫ መንግሥትና የታጠቁ ኃይሎች ለድርድርና ለውይይት በር እንዲከፍቱ ጠይቋል፡፡ የክልሉ ሕዝብም ይህ እውን እንዲሆን የራሱን ድርሻ እንዲወጣ አብን ጠይቋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለተለያዩ አካላት ከማሳወቅ ባሻገር ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ እየሰራ እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐ,ይ ጫኔ