1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታ እጦት ችግር እሮሮ በኦሮሚያ

ሰኞ፣ ሰኔ 19 2015

በኦሮሚያ ክልል እየተወሳሰበ መጥቷል የተባለው የፀጥታ ችግር ህብረተሰቡን ከእለት ተእለት ኑሮው ማፈናቀል መቀጠሉን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በተለይም ከኪረሙ ወረዳ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች ከፍቷል ያሉት የፀጥታ ይዞታ ህይወታቸውን መምራት አዳጋች እንዳረገባቸው ተናግረዋል፡፡

 Kamashi town in Benishangul Gumuz region Ethiopia
ምስል Negassa Dessalegn/DW

"ጽንፈኞች እየተባልን ይሄው መረጋጋት እንዳጣን ሶስት ዓመታት አስቆጥረናል"

This browser does not support the audio element.

 


«አሁን እንደ ኪረሙ ነዋሪ ነገሮች ሁሉ ተባብሰው አከባቢውን ለቀን እግር ወዳመራን መጓዝ ነው የቀረን፡፡ ከብቶች ይወሰዳሉ ወጥቶ ማረስ አይቻልም፡፡ በዚህ ሳምንት ብቻ ከብቶች ሁለቴ ከእረኞችም ጭምር በገፍ ተነድተው ተወስደዋል፡፡» ይህን ያሉን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ በመንግሥት ሥራ ተሰማርተው የሚገኙና ለደህንነታቸው ሲባል ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ነዋሪ ናቸው፡፡ እንደ ነዋሪው አስተያየት በዚህ አከባቢ ለጸጥታው መክፋት አስጊ የሆኑት «ፋኖ» ያሏቸው ከአጎራባች ክልል ጭምር ታትቀው የሚገቡና በዚሁ አከባቢ ሲኖሩ የነበሩ ታጥቀው በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የመንግሥት የፀጥታ አካላትስ በአከባቢው የሉም ወይ የተባሉት እኚህ ነዋሪ፡ «የመንግሥት የፀጥታ አካላት በአካባቢው ቢኖሩም ከከተማ ግን እምብዛም ወጥተው አይንቀሳቀሱም» የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
በዚሁ ኪረሙ ወረዳ ከዋፍቲ ቀበሌ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ነዋሪም በአካባቢው ስላለው የከፋ ያሉት የፀጥታ ችግር ልዩነት ባይኖራቸውም ድርጊቱን ይፈፅማል ባሉት አካል ግን ከዚህ የሚቃረን አስተያየት ነው የሚሰጡት፡፡ «በወፍቲ እና ወፍጪ ከብት የተወሰደው የአማራ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ወሳጁም «ሸነ» ነው፡፡ ሰኔ 8 እንኳ ስድስት ሰው ገድለው ነው 103 ከብቶች ነድተው የሄዱት፡፡ ሰው በየጊዜው ይሞታል፡፡ ገለልተኛ አካላት መጥተው እውነታውን አጣርተውት ቢሄዱ እኛ ደስተኞች ነን፡፡ ጽንፈኞች እየተባልን ይሄው መረጋጋት እንዳጣን ሦስት ዓመታት አስቆጥረናል፡፡»
ከዚሁ ወረዳ አስተያየታቸውን ያጋሩን አቶ አያለው ደምሰው የተባሉ ለ50 ዓመት የአካባበው ነዋሪ በበኩላቸው በአካባቢው የመከራ ሌትና ቀናትን እየገፋ ባለው አርሶ አደር ላይ የሚደርሰው ችግር ከሦስት አቅጣጫዎች የሚመነጭ ነው ይላሉ፡፡ «የኦሮሞ እና የአማራ ታጣቂዎች እንደየፊናቸው በዚሁ ማኅበረሰብ ላይ ነው መከራ ያመጡት፡፡ መንግሥትም እገሌን ደበቃችሁ እያለ በጸጥታው ይህንኑ ማኅበረሰብ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ይህ ነገር እያደር በማኅበረሰብም መካከል ጥላሸት እንዳያሳርፍም በሁሉም ወገን ያሉ ምሁራን ተቀራርበው ለህዝቡ የሚበጀውን መፍትሄ ነው ማምጣት ያለባቸው፡፡ አሁን እኮ ወለጋ ወደ ኦናነት እየተቀየረች ህዝብ የሚሰቃይባት ምድር ሆናለች፡፡»
እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት በዚህ ወረዳ በኪረሙ ወረዳ ከተማ ብቻ አስተማማኝ ፀጥታ በመኖሩ አርሶ አደሩ በሙሉ ተፈናቅለው ወደ ከተማዋ እንዲጠለሉ አስገድዷል፡፡ ይህ ደግሞ ለተከታታይ ሦስተኛ የምርት ዘመን አርሶ ህይወቱን የሚመራውን ህዝብ ከለም አፈሩ ጋር አለያይተውታል፡፡ ይህ የፀጥታ ችግር እንደ አሙሩ፣ አቤ ዶንጎሮ፣ ጃርዴጋ ጃርቴ እና ሌሎችም አዋሳኝ ወረዳዎች የተስፋፋ መሆኑን ነው እነዚህ ነዋሪዎቹን በአስተያየታቸው ያጋሩን፡፡ 
ዶቼ ቬለ ስለ አርሶ አደሮቹ እሮሮ ማረጋገጫ እና እልባት ለመጠየቅ ለአከባቢው ( ማለትም ለወረዳ እና ዞን አመራሮች) ቢደውልም ስልካቸው አይሠራም፡፡ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና ጸጥታ አስተዳደር አመራሮች ደውለን አስተያየታቸውን ለማካተት ብንጥርም ስልካቸው ባለመነሳቱ አልሰመረም፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አዋሳኝ ዞኖች ለዓመታት እየዘለቀ ላለው አለመረጋጋት ኅብረተሰቡ የተለያዩ ስያሜ ያላቸውን ታጣቂዎች ተወቃሽ ያደርጋል፡፡ መንግሥትም «ሸነ» እና «የአማራ ጽንፈኛ ታጣቂዎች» ያላቸውን የታጠቁ ቡድኖችን ለአካባቢው የፀጥታ ይዞታ መወሳሰብ በምክኒያትነት ሲያነሳ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW