1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፅንፈኞች ስጋት በአፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 2010

አፍሪቃ የሙስሊም ፅንፈኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ ስጋት እየተጠናከረባት መሄዱ እየተነገረ ነው። በተለይ በሳህልንና በማግሬብ አካባቢ ሃገራት የሚታየው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት፤ በሶማሊያና በናይጀሪማ ደግሞ ከዓለም አቀፉ ፅንፈኛ ቡድን አልቃይዳ ጋር ትስስር ያላቸው ቡድኖች እንቅስቃሴ ጥቂት የማይባሉ ደጋፊዎች እንዳሉት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ይገልጻሉ።

Al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab

የፅንፈኛ ተዋጊዎች መበራከቱን የሚናገሩ አሉ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሳምንት ነው የሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቦውሪታ አፍሪቃ ውስጥ 10 ሺህ ፅንፈኛ ሙስሊም ተዋጊዎች አሉ የሚል ማሳሰቢያ ያሰሙት። እነዚህ ደግሞ የአልቃይዳ የሽብር ሰንሰለት አባላት እና እስላማዊ ግዛት ከሚባሉት ከሶርያ እና ኢራቅ የተመለሱ ናቸው። ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅም ስለብዛታቸው ግነት እንደሌለበት እና እንደውም ሶማሊያ ከሚገኘው አሸባን ወይም ናይጀሪያ ከሚንቀሳቀሰው ቦኮ ሀራም ጎን ተሰልፈው የሚዋጉትን አለመካከቱትን ነው ያመለከቱት።

«ዛሬ የአልቃይዳ ከ6,600 የሚበልጡ ተዋጊዎች አፍሪቃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ግልፅ ነው። የዳይሽ ማለትም ራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለው ቡድን ከ3,500 በላይ ተፋላሚዎችም አፍሪቃ ውስጥ ይገኛሉ። አብዛኞቹም ሶርያ እና ኢራቅ ውስጥ ለIS ይዋጉ የነበሩ ናቸው። ለዚህ ነው 10 ሺህ ገደማ በመላው አፍሪቃ ይገኛሉ ያልኩት። ከአሸባብ እና ቦኮ ሀራም ጋር የተሰለፉት እንደውም አልተቆጠሩም።»

ለዚህም አፍሪቃ ውስጥ እስላማዊ ፅንፈኛ ሽብርተኝነትን የሚከላከል ስልት በአፋጣን ያስፈልጋል ሲሉም አፅንኦት ይሰጣሉ። የማግሬብ ሃገራት የሚባሉትም ዓለም አቀፍ ትብብራቸውን በተለይ ደግሞ ከቡድን አምስት የሳህል ሃገራት ጋር አጠናክረው በፅንፈኞች ላይ የሚካሄደውን  ዘመቻ ማጠናከር እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል።  ቡድን አምስት በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ሞሪታንያ፣ ማሊ፣ ኒዠር፣ ቡርኪናፋሶ እና ቻድ በአካባቢው የሽብር ስጋት ሲባባስ በጋራ የ የመሠረቱት ስብስብ ነው። ባለፈው ሳምንት ግን ሳህል አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች እና ሲቪሎች ላይ የፅንፈኞች ጥቃት ተፈጽሟል።

ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab

አፍሪቃ ውስጥ 10 ሺህ ጀሃዲስት እየተንቀሳቀሰ ይሆን? የፅንፈኛ አሸባሪዎች የስም ዝርዝር እንዳልተመዘገበ የሚናገረው አፍሪቃዊው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ማርክ ኤንግሀርት ቁጥሩ ሊቀንስ ይችላል ባይ ነው። ከዋናዎቹ ፅንፈኛ ተዋጊዎች የደጋፊዎቻቸው ቁጥር እንደሚልቅም ይጠቁማል።

«በአሸባሪነት የተሰማሩትን የሚያሳይ ዝርዝር የለም። በእኔ ምርምር መሠረት ቀንደኛ ተዋጊዎቹ በጥቂት መቶዎች ቢቆጠሩ ነው። ይህ ጥቂት የቆረጡ ሰዎች ስብስብ እንደ ማሊ ያለች ትልቅ ሀገርን አግተው መያዛቸው ያስፈራል። እናም ከ10 ሺህ እንደሚያንሱ መናገር እችላለሁ፤ ነገር ግን የደጋፊዎቻቸው ነገር ሰፋ ብሎ ከታየ ከፍ ሊል ይችላል።»

ግጭት የሚታይባቸው የሳህል፣ ማግሬብ አካባቢም ሆነ ሶማሊያ እና ናይጀሪያ ብቻ አይደሉም ኢንግልሄርድን ያሳሰቡት፤ እስከ ቅርብ ጊዜ እስልምና እንግዳ ቃል የነበረባቸው እንደ ኮትዴቩዋር ወይም ሞዛምቢክ ያሉ ሃገራት ሳይቀሩ የእስላማዊ ፅንፈኝነት ጥቃት ኢላማ እየሆኑ መጥተዋል። ቅዱስ ጦርነት የተቀደሰ ትርፍ፤ አፍሪቃ የጅሀዲስቶች ዓለም አቀፍ ጥቃት የፍልሚያ ሜዳ፤ የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ኢንግድልሄርድ ሰዎች የፅንፈኛ ቡድኖች አባላት እየሆኑ ጥቃት የሚያደርሱት ምክንያት ያለውን ሲናገር፤

«በተከታዮቹ ዘንድ ርዕዮተአለሙ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብዬ አስባለሁ። አመለካከቱ ግን ያለው ሚና አናሳ ነው። ኢስላም በተጠቀሱት አካባቢዎች የኖረ ሃይማኖት ቢሆንም አሁን እየተጠቀሙበት ነው»

ጋዜጠኛ እና ጸሐፊው እንደሚለውም ሃይማኖቱን ለስልጣን እና ትርፍ ለማግኛ የሚጠቀሙበት ተበራክተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ድሀ እና የተረሱ ወገኖች የፅንፈኙን አክብሮት ስለሚያገኙ ዋጋ ይሰጡታል። ይህም ሰዎች አጥፍቶ ጠፊ ሆነው ሕይወታቸውን እስከማጥፋት ድረስ አሳልፈው ለቡድኖቹ ያቀርባሉ።

ሌላው ቀርቶ የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤውን ናውክሾት ሞሪታንያ ላይ እያካሄደ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ሳይቀር የፅንፈኞቹ ጥቃት በሳህል አካባቢ ቀጥሏል። ለድርጊቱ ኃላፊነቱን የወሰደው ማሊ የሚገኘው የአልቃይዳ ክንፍ ባለፈው ዓርብ የቡድን አምስት ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያን፤ ቅዳሜ ደግሞ የማሊ ወታደሮች ላይ ያነጣጠረ የተቀበረ ፈንጂ ጥቃት እንዲሁም እሁድ ዕለት ደግሞ የፈረንሳይ ወታደሮችን ያለመ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፍንዳታ ደርሷል። በዚሁ አጋጣሚ ማሊ ውስጥ አራት ሲቪሎች ሲገደሉ 20 ተጎድተዋል። በደቡባዊ ምሥራቅ ኒዠር ደግሞ አስር ወታደሮች ተገድለዋል። የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሃገራት መሪዎችም እስከ መጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2020 ድረስ ባህጉሪቱ የሚካሄድ የትኛውንም የጦር መሣሪያ የታከለበት ግጭት ለማስቆም መወሰናቸውን ተናግረዋል። ቃሉ አስደሳች ቢሆንም ተግባራዊነቱን ግን የሚጠራጠሩ ብዙዎች ናቸው። ሌላው ቀርቶ የድርጅቱ ባልደረባ የሆኑት በአፍሪቃ ኅብረት የማሊ እና ሳህል አካባቢ ተጠሪ ፒየር ቡዮያ ይህን በተግባር ለማየት እንቅፋቱ ቀላል እንዳይደለ ይናገራሉ።

«ሰላምን የመፈለጉ ተግባር እጅግ ግዙፍ የቤት ሥራ ነው። በአንድ ቀን ወይም በዓመት አለያም በአስርት ዓመታት ይከናወናል የሚባል አይደለም። አፍሪቃ ገና ለመረጋጋት እየታገሉ የሚገኙ አዳዲስ ሃገራት የሚገኙባት ወጣት አህጉር መሆኗን ታውቃላችሁ።»

2020 ላይ ለመድረስ 18 ወራት ቀርተዋል። ከጊዜው ማጠር ሌላ ፅንፈኞች ተፅዕኗቸውን በመላው አፍሪቃ ለማዳረስ ሳይሞክሩ እንደማይቀሩ አፍሪቃዊዉ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ኢንግልሀርት ያስጠነቅቃል።

ሸዋዬ ለገሠ/አንቶኒዮ ካሽካሽ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW