1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ ከኒዠር መውጣት አንድምታ

ቅዳሜ፣ መስከረም 19 2016

የፈረንሳይ መንግሥት በኒዠር የነበሩት የሀገሪቱን አምባሳደር በዚህ ሳምንት አስወጥቷል። ለጸረ ሽብር ዘመቻው ኒዠር ውስጥ ተሰማርተው የቆዩ ከአንድ ሺህ በላይ ወታደሮቹንም በመጪው ታኅሣስ ወር ማለቂያ ለማስወጣት መወሰኑን ይፋ አድርጓል።

 ፎቶ፤ የፈረንሳይ ወታደሮች በኒዠር
ፈረንሳይ ኒዠር ውስጥ በጸረ ሽብር ዘመቻው ያሰማራቸውን 1,500 ወታደሮቿን እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2023 መጨረሻ ድረስ ለማስወጣት መወሰኗን አስታውቃለች። ፎቶ፤ የፈረንሳይ ወታደሮች በኒዠር ምስል Dominique Faget/AFP

የፈረንሳይ ከኒዠር የመውጣት ውሳኔ እና የጸጥታ ስጋት

This browser does not support the audio element.

ፈረንሳይ በቅርቡ በመፈንቅለ መንግሥት ኒዠር ውስጥ ሥልጣን በያዘው ወታደራዊ ኹንታ አምባሳደሯንም ሆነ እዚያ የሚገኙ ወታደሮቿን እንድታስወጣ በተነገራት መሠረት እርምጃዋን ጀምራለች። ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ባሳለፍነው እሑድ ዕለት ነው የሀገራቸው አምባሳደርም ሆኑ ወታደሮቻቸው ከኒዠር እንደሚያስወጡ ይፋ ያደረጉት። በዚሁም መሠረት በኒዠር የፈረንሳይ አምባሳደር የነበሩት  ሲልቫን ኢት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ረቡዕ ዕለት ፓሪስ መግባታቸው ተነግሯል። 1,500 መሆናቸው የተገለጸው ኒዠር የሚገኙ የፈረንሳይ ወታደሮችም እስከያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 መጨረሻ ማለትም እስከመጪው ታኅሣስ ወር ማለቂያ ቀናት ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱም ታውቋል። ከመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች በመጀመሪያ ይውጡ የሚለው ትዕዛዝ ሲተላለፍ ፈረንሳይ «ሕጋዊ መንግሥት ባለመሆኑ አንወጣም» በሚል ስታንገራግር ቆይታ ነበር። ሆኖም ኒዢር ውስጥ በተጠናከረው ፀረ ፈረንሳይ መንፈስ እና ተጽዕኖ ምክንያት የፈረንሳይ አምባሳደር ከኤምባሲው መውጣት እንኳ እንዳይችሉ ማድረጉ ውሎ አድሮ የፓሪስን አቋም እንዳስቀየረ ነው የሚታሰበው። ፈረንሳይ በጀሃዲስቶች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የተጋለጡ የቀድሞ የቅኝ ግዛቶቿን ለመከላከል ወታደሮቿን ካሰማራች ቆይታለች። በጽንፈኛ ሙስሊሞች ጥቃት ከሚናወጡ የሳህል አካባቢ የአፍሪቃ ሃገራት አንዷ ኒዠር ስትሆን፤ የፈረንሳይ ወታደሮች ከግዛቷ እንዲወጡ የጠየቀች ብቸኛ ሀገር ግን አይደለም። ተመሳሳይ የሆነ የጸረ ፈረንሳይ እንቅስቃሴዎች በተጠቀሱት ሃገራት መኖራቸው ይነገራል።

የፈረንሳይ ውሳኔ እና የኒዠራውያን ደስታ

የፈረንሳይ ውሳኔ ወታደራዊውን ኹንታ አስፈንድቋል። በዚህ የተደሰተው ኹንታው ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጋ መሆኑን ነው በኒዠር ለፋይናንስ ግልጽ አሠራር የሚሟገተው ሲቪክ ማኅበረሰብ አስተባባሪ አሊ ኢድሪስ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት። እሳቸው እንደሚሉት ጸረ ፈረንሳይ እንቅስቃሴው ሥር የሰደደ ነው።

የኒዠር ዜጎች የፈረንሳይ ወታደሮች ሀገራቸውን ለቅቀው እንዲወጡ በተቃውሞ ሰልፍ ለመጠየቅ በሀገሪቱ ከተሞች ጎዳና ወጥተዋል። ፎቶ፤ የፈረንሳይ ወታደሮችን መውጣት የጠየቀ ተቃውሞ በኒዠርምስል Balima Boureima/AA/picture alliance

«ኢማኑዌል ማክሮን የፈረንሳይ አምባሳደርንም ሆነ የፀጥታ ኃይላቸውን ለማስወጣት መፈለጋቸውን እናውቃለን። ይኽ ደግሞ ለዚህ ሲታገል ለቆየው የኒዠር ሕዝብ አንድ ድል ነው። መሪዎች አይደለንም ይኽን እንቅስቃሴ ያነሳሳነው። የኒዠር ዜጎች የአጸፋ ምላሽ ነው፤ በቀጣይ የሚሆነውንም የሚወስኑት እነሱ ናቸው። ሆኖም እኛ ግን የመውጣቱ ዕቅድ በፍትኃዊነት እንዴት በግልጽ ተግባራዊ እንደሚሆን በጥንቃቄ እና በንቃት እናስተውላለን።»

ፕሬዝደንት ማክሮን ቀደም ብለው ፈረንሳይ አብሳደሯንም ሆነ ወታደሮቿን ለማስወጣት በሕጋዊ መንገድ የተመረጡት የኒዠር ፕሬዝደንት መሐመድ ባዙምን ውሳኔ እንጂ የመፈንቅለ መንግሥት አድርጊውን ወታደራዊ ቡድን ትዕዛዝ አትቀበልም ብለው ነበር። ሌላኛው የመብት አቀንቃኝ ማይኮል ዞዲም በበኩሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ውለው አድረውም ቢሆን ለኒዠር ሕዝብ ጥያቄ የተፈለገውን ምላሽ መስጠታቸው ግልጽ የሆነ ድል ነው ባይ ናቸው።

«ለእኛ ይኽ ግልጽ ድል ነው። ምክንያቱም፤ ከሳምንታት በፊት ማክሮን የፈረንሳይ ወታደሮች እንዲወጡ ማዘዝ የሚችሉት ከሥልጣን የተወገዱት መሀመድ ባዙም ብቻ ናቸው ነበር ያሉት። አሁን ግን ኒዠራውያን ኒዠር የእነሱ እንደሆነች አሳዩ። ፈረንሳዮች ይኽ የሚሆነው በታኅሣስ መጨረሻ ነው ብለዋል። የመጨረሻው ወታደር እስኪወጣ የእኛም እንስቃሴ ይቀጥላል። ዛሬ ኒዠር ሉአላዊነቷን መልሳ ማግኘት እንደምትችል በጽኑ እናምናለን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሚባለውም ሆነ ለኤኮዋስ የምናስተላልፈው መልእክት ኒዠር እና ሕዝቧ እራሳቸውን ችለው መኖር እንደሚፈልጉ ነው።  የሀገራችን የተፈጥሮ ሀብቶች ተጠቃሚ መሆን እንፈልጋለን። ብዙ የተፈጥሮ ሀብት እያለን የዓለም ድሀ ሀገር ልንሆን አንችልም። የመጨረሻው ወታደር እስኪወጣ ተቃውሟችን ይቀጥላል።»

የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮን ኒዠር የሚገኝ ሀይኃላቸው እና አምሳደራቸውን ለማስወጣት መወሰናቸው ኒዠር ውስጥ ደስታን ፈጥሯል። ታዛቢዎች ግን የጀሃዲስቶች ጥቃት በጠናበት የሳህል አካባቢ የኒዠር የጸጥታ ይዞታ አስጊ ነው እያሉ ነው። ፎቶ፤ ኒዠር ኒያሚ የሚገኘው የፈረንሳይ የአየር ኃይል ወታደራዊ ጣቢያምስል Jerome Delay/AP/picture alliance

ጥንቃቄ

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በበርካታዎቹ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት መፈንቅለ መንግሥት ቢካሄድም በኒዠር ያለው ሁኔታ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ እየተገለጸ ነው። ምክንያቱም ተጽእኖው በራሷ በኒዠር ላይ ብቻ ሳይሆን በድንበር በምትጎራበታቸው የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት እና በተሳሰረው መልክአ ምድራዊ ፖለቲካ ለሳህል አካባቢ ሃገራት ሁሉ እንደሚተርፍ ይታሰባል። በምዕራብ አፍሪቃ የጽንፈኝነት ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ጋናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ሙታሩ ሙማኒ ሙክታር ኒዠር ውስጥ አሁን የሚታየው ደስታ ዕድሜ የለውም ባይ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉትም ድሀይቱ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ኒዠር ራሷን ወደማበልጸግ ለመግባት የሚያበቃ አቅም ላይ አይደለችም፤ ያለባትን ስጋት ለመቋቋም ጠንካራና አስተማማኝ የመከላከል ብቃት አላዳበረችም። በእርግጥም ኒዠር ከወዲሁ ጥቃቶች መድረሳቸው የተነገረ ነው። በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ትናንት በደረሰ ጥቃት ሰባት ወታደሮች ሲገደሉ፤ ለጥቃቱ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ከተሰማሩ አምስቱ ወታደሮች ደግሞ በመኪና አደጋ መሞታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ጥቃቱ በጀሃዲስቶች ሳይፈጸም እንዳልቀረ ተገምቷል። የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ሳሊፎ ሞዲ በሰጡት መግለጫ በወታደሮቹ ላይ ጥቃት ያደረሱት በበርካታ መቶዎች የተገመቱ አሸባሪዎች ናቸው። ኒዠር በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው በተወገዱት መሀመድ ባዙም የፕሬዝደንትነት ዘመን በጸረ ሽብር ውጊያው ቁልፍ ሚና ነበራት። የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት አሁን የሀገሪቱን መንበረ ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ ሽብርተኝነትን መዋጋት አይፈልም ባይ ናቸው። ወታደሮቻቸውን ለማውጣት የወሰኑትም በዚህ ምክንያት መሆኑን ነው የተናገሩት። ጉዳዩን በቅርበት የሚመረምሩት የፖለቲካ ተንታኝ ሙታሩ ሙማኒ ሙክታር የፈረንሳይ ወታደሮች ከኒዠር መውጣታቸው የጸረ ሽብር ዘመቻውን ችላ ያለ ነው ይላሉ። እንደእሳቸው ሁሉ ውሳኔው በኒዠርም ሆነ በሳህል አካባቢ የጸጥታውን ይዞታ አስጊ ሊያደርገው እንደሚችል እያሳሰቡ ነው።

የኒዠሮች የራሳቸውን ዕድል የሞከር ፍላጎት

መፈንቅለ መንግሥት በሚደጋገምባት ኒዠር ውስጥ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋቱ ዋነኛ ችግር ነው። ምንም እንኳን ሀገሪቱ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች መሆኗ ቢነገርም የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽል ሥራ አለመሠራቱ ዜጎችን እያስቆጨ ነው። ፎቶ፤ በመፈንቅለ መንግሥት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ምስል Gerlind Vollmer & Mounkaila Aboubacar/DW

ምንም እንኳን በርካታ የኒዠር ዜጎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ተግዳሮት መኖሩን ቢያውቁም እራሳቸው ሊጋፈጡት ፈቃደኛ መሆናቸው ይናገራሉ። ከኒያሚ ነዋሪዎች አንዱ የፈረንሳይ ወታደሮች በሀገሪቱ መገኘት ያስገኘው ፋይዳ የለም ባይ ናቸው። አክለውም ምንም እንኳን የፈረንሳይ ወታደሮች ለዓመታት ኒዠር ውስጥ በጸረ ሽብር ዘመቻው ቢሰማሩም ሽብርተኝነት ማስወገድ አልቻሉም በማለትም ይወቅሳሉ። እንደውም እነሱን ቀስ በቀስ የማጥፋት ሌላ ተልእኮ እንዳላቸው እንደሚገምቱ ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት። የሃይማኖት መሪ የሆኑት ኢማም አብዱላዚዝ አብዶላይ አማዱ በበኩላቸው ፈረንሳይ አላዋቂ አድርጋ ቆጥራናለች ነው የሚሉት።

«ለምንድነው ኢማኑዌል ማክሮን የሀገራችንን ባለሥልጣናት እውቅና የነፈጉት፤ በሌሎች ለምሳሌ ጋቦን እና ቻድን በመሳሰሉት ሃገራት ላሉ ኹንታዎች እውቅና ሰጥተዋል። ይኽ አስቆጥቶናል፤ እኛ እንደምናስበው ፈረንሳይ አላዋቂ አድርጋናለች።»

እንዲያም ሆኖ ግን ኒዠር ከጸጥታው ስጋት በተጨማሪ የወጣቶች ሥራ አጥነት እና አሳሳቢ የኤኮኖሚ ይዞታዋም ሌላው ፈተናዋ እንደሚሆን ይታሰባል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW