1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ የሁዲዎች ሥጋት

ማክሰኞ፣ ጥር 5 2007

የፈረንሳይ ካቢኔ በወሰነዉ መሠረት በመላ ሐገሪቱ የሚገኙ 717 ምኩራቦችና የአይሁድ ትምሕርት ቤቶች ጥበቃ እንደሚደረግላቸዉ ሚንስትሩ አስታዉቀዋል።4700 ወታደሮችና ፖሊሶች ለጥበቃ መሰማራታቸዉንም ሚንስሩ ገልጠዋል።

ምስል AFP/Getty Images/J. Guez

ፓሪስ ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት በተጣለዉ የአሸባሪዎች ጥቃት አራት አይሁድ ከተገደሉ ወዲሕ የፈረንሳይ አይሁድ ተጨማሪ አደጋ ይጣልብናል የሚለዉ ሥጋታቸዉ አይሏል።አንዳድዶቹም ወደ እስራኤል ለመሰደድ ማሰባቸዉን እያስታወቁ ነዉ።የፈረንሳይ መንግሥት በበኩሉ ለአይሁድ ተቋማት ልዩ ጥበቃ እያደረገ ነዉ።እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2012 ቱሉዝ በሚገኝ በአንድ የአይሁድ ትምሕር ቤት ላይ ጥቃት ከደረሰ ወዲሕ ወደ እስራኤል የሚሰደዱ የፈረንሳይ አይሁድ ቁጥር ጨምሯል።ባለፈዉ ሳምንት በፓሪሱ የሽብር ጥቃት የተገደሉት አይሁዳዉያን ዛሬ እየሩሳሌም ዉስጥ ተቀብረዋል።

አይሁድ በብዛት በሚኖሩባት ማሪይ በተሰኘችዉ የፓሪስ መንደር የሚገኘዉ ምኩራብ ትናንት በሰዎች ተሞልቶ ነበር።የፈረንሳዩ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ቤርናርድ ካዞነቭም ባለፈዉ ሳምንት በደረሰዉ ያሸባሪዎች ጥቃት የተደናገጡ አይሁድን ለማረጋጋት አካባቢዉን ጎብኝተዋል። የፈረንሳይ ካቢኔ በወሰነዉ መሠረት በመላ ሐገሪቱ የሚገኙ 717 ምኩራቦችና የአይሁድ ትምሕርት ቤቶች ጥበቃ እንደሚደረግላቸዉ ሚንስትሩ አስታዉቀዋል።4700 ወታደሮችና ፖሊሶች ለጥበቃ መሰማራታቸዉንም ሚንስሩ ገልጠዋል።

ምስል AFP/Getty Images/J. Guez

ይሁንና የሚንስትር ካዘነቭ መግለጫም ሆነ የመንግሥታቸዉ እርምጃ አይሁድን የሚረጋጋ አልመሰለም።ዳቪድ ቦኩብዛ እንደሚሉት ኮፊያቸዉን እንኳን ማድረግ እየተሳቀቁ ነዉ።«ሐይማኖታዊ ነፃነቴ ተገድቧል» ይላሉ ቦኩብዛ።

የአዉሮጳ አይሁድ ኮንግሬስ እንዳስታወቀዉ ዓመዓቱ ከባተ ወዲሕ በአይሁድ ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት በሰባት እጥፍ አድጓል።እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2012 ደቡባዊ ፈረንሳይ ቱሉዝ ከተማ በሚገኝ አይሁድ ትምሕርት ቤት ዉስጥ አንድ ፅንፈኛ ሙስሊም አራት አይሁድ ከገደለ በኋላ ደግሞ ሥጋቱ ብሷል።«መንግሥት የሚጣልብንን አደጋ ሊከላከልንን አልቻለም፤ እኛ የጥቃት ኢላማ ነን» ይላሉ ቦኮብዛ።የፈረንሳይ አይሁድ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሮዠር ኩኪርማንም ሥጋቱን ይጋራሉ።

«አይሁዳዉያን ፈረንሳይ ዉስጥ መኖር በጣም ከባድ ነዉ፤ ምናልባትም መኖር አይቻልም የሚል ስሜት እያደረባቸዉ ነዉ።ብዙዎች ለመሰደድ እያሰቡ ነዉ።ወደ እስራኤል»

የአሁዱ የሥጋት ምንጭ ሙስሊም ፅንፈኞች ብቻ አይደሉም።ኩኪርማን እንደሚሉት አንዳድ የፈረንሳይ ቀልደኞች ወይም ኮሜዲያን የሁዲን የሚያኪያኪስ ፌዞችና ቀልዶች ማሰራጨታቸዉ ሌላዉ ችግር ነዉ።የመንግሥት ተቋማትም የሁዲን ከማንቋሸሽ የፀዱ አይደሉም-እንደ ኩኪርማን።

«የሁዲ የሚለዉ ቃል በሪፐብሊኪቱ ትምሕርት ቤት ሳይቀር የስድብ ቃል ነዉ።ይሕ በጣም መጥፎ ነዉ።»

ፈረንሳይ ዉስጥ ግማሽ ሚሊዮን ያሕል አይሁድ አለ።ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰባት ሺሕ ያሕሉ ወደ እስራኤል ተሰደዋል።የስደቱ ምንጭ ግን ሥጋት ብቻ አይደለም።የምጣኔ ሐብት ኪሳራ ጭምርም እንጂ።በፓሪሱ ሽብር የሞቱን ለመዘከር ባለፈዉ ዕሁድ ከተደረገዉ የአደባባይ ሠልፍ በሕኋላ እዚያዉ ፓሪስ የሚገኘዉን የአይሁድ ምኩራብ የጎበኙት የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ከፈረንሳይ የሚፈልሱ አዩዳዉያንን እጇን ዘርግታ እንደምትቀበላቸዉ ቃል ገብተዋል።

ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/Remy de la Mauviniere

«ወደ እስራኤል መምጣት የሚሹ አይሁዳዉያንን እጃችንን ዘርግተን፤ልባችንን ከፍተን ነዉ የምንቀበላቸዉ።እንግዳ ሐገር አይደለም የምትመጡት።»

ኔታንያሁ ትናንት አሁዳዉያኑ የተገደሉበትን ሥፍራ ሲጎበኙም ይሕንኑ መልዕክታቸዉን ደግመዉታል።የኔታንያሁ ደጋፊ አድናቂዎች መልዕክቱን በጭብጨባ ቢቀበሉትም በፈረንሳይ የአይሁድ ዋና ራባይ ሐይም ኮሸርን ግን ተቃዉመዉታል።ፈረንሳይ እኛም ጭምር የገነባናት ሐገር ናት-ብለዉ።

«ይሕቺን ሐገር እኛም አብረን ገንብተናታል።ወደፊትም እንገነባታለን።የምናልመዉ በፈረንሳይኛ ነዉ።በፈረንሳይኛ ነዉ የምናስበዉ።ፈረንሳይ ሐገራችን ናት።ምንም ጥርጥር የለዉም።ይሁንና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትርን ቃላት እኔ የምገነዘበዉ ከሐዘንና ሕመም የመነጩ አድርጌ ነዉ።አሁን የሚያስፈልገን ግን የሚያረጋጋ እና ተስፋ ሰጪ ቃላት ነዉ።ለፈረንሳይ አይሁድ የምናገረዉ እዚሕም ደስተኛ ሆኖ መኖር ይቻላል( እያልኩ ነዉ)»

ባለፈዉ ሳምንት አሸባሪዎች በአይሁዳዉያኑ የምግብ ሸቀጣሸቀጥ የገበያ አዳራሽ ዉስጥ የገደሏቸዉ አራቱ ፈረንሳይ-አይሁድ ቤተሰቦቻቸዉ በጠየቁት መሠረት እየሩሳሌም ተቀብረዋል።

ባርባራ ቬዘል / ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW