የፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች ከስድስት አስርተ አመታት በኋላ ምን ላይ ናቸው?
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24 2017
«65 የብስለት ዘመን ነው" በሚል ነበር የኮትዲቯር ፕሬዝዳንት አላሳን ኦውታራ በቅርቡ ሀገራቸውን የነፃነት ቀን እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት። "አሁን ምን ያህል እንደደረስን የጋራ ግንዛቤ የምናገኝበት ወቅት ነው። የተማርነውን እንድናጠናክር እና ወደ ፊት እንድንመለከት የተደረገ ግብዣ ነው።» ብለዋል።
አፍሪካ በዚህ አመት ብዙ 65ኛ የነፃነት በዓሎችን እያከበረች ነው፡ ናይጄሪያ፣ ሶማሊያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ1960 ነፃነታቸውን አግኝተዋል። ከሁሉም በላይ ፈረንሳይ ለ14 የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿን ለቃለች። የወቅቱ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከአፍሪካ የቀድሞ ቅኝ ገዥዎች ጋር የሻከረ ግንኙነት አላቸው ተብሎ ይታሰባል። በመሬት ላይ ያሉ መንግስታት እና ማህበረሰቦች ትልቅ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ነው።የፍራንኮፎን አፍሪካ ከ65 ዓመታት በኋላ የደረሱበት ደረጃ ሲገመገም፤አንዳንድ ሀገራት ከዓለም ድሃ ከሆኑ አገሮች ተርታ ይጠቀሳሉ። የሰብዓዊ ልማት መረጃ ጠቋሚን ስንመለከት ሁኔታው አሁንም በብዙ ቦታዎች ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ያሳያል፡ ከእነዚህ 14 አገሮች ውስጥ ስምንቱ - የሳህል ግዛቶች ማለትም ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር እና ቻድ በዚህ ዝርዝር ግርጌ ላይ ይገኛሉ።
በሐምቡርግ የሚገኘው የጂጋ የአፍሪካ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ማቲያስ ባሴዳው ለእያንዳንዱ ሀገር የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ይላሉ፡። እሳቸው እንደሚሉት በበርካታ ቦታዎች አፈሩ ለም አይደለም፣ የማዕድን ሃብቶች ውስን ናቸው።ከፍተኛ የወሊድ መጠንም የኢኮኖሚ እድገትን ፍላጎት ይጨምራል። ባሴዳው ለDW በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሌሎች ምክንያቶችንም ጠቅሰዋል። «ከዚያም ሌሎች ተግዳሮቶች አሉ። ለምሳሌ የፖለቲካ አለመረጋጋት። ይህ በቀላሉ ወደ ግጭት ወጥመዶች ሊመራ ይችላል፡ ይህ ማለት ግጭቶቹ የእድገት መቀዛቀዝ ያስከትላሉ። እና የእድገት መቀዛቀዝ ደግሞ ወደ ብዙ ግጭቶች ያመራል።»ብለዋል።በማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ሲቪል መንግስታት ይህን አዙሪት መስበር ባለመቻላቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመፈንቅለ መንግስት ወታደራዊ ሀይላት ስልጣን ተቆጣጥረዋል።
ከጠንካራ ተቋማት ይልቅ ጠንካራ ወንዶች
መፈንቅለ መንግስት በፍራንኮፎን አፍሪካ ከፍተኛ ነው። ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ባለፈው አመት በሴኔጋል ከተደረገው ውጭ ብዙ አይታይም።
በሌላኛው ጫፍ በብዙ ቦታዎች እርጅና የተጫናቸው የረዥም ጊዜ ገዥዎች አሉ፡ በኮት ዲቩዋር፣ አላሳን ኦውታራ በ83 ዓመታቸው ለአራተኛ ዙር ለመቀጠል እየፈለጉ ሲሆን፤ በካሜሩን ፖል ቢያ በ92 ዓመታቸው እንኳን ለስምንተኛ ጊዜ መወዳደር ይፈልጋሉ።በቶጎ ደግሞ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ፋዉሬ ናሲንግቤ ላልተወሰነ ጊዜ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ለዉጥ አደርገዋል።
በጎርጎሪያኑ 1990 ዎቹ ውስጥ ያለው «የጠንካራ ተቋማት ዘመን» ተስፋ ጠፍቷል። ሲሉ በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ የሶርቦኔ ኑቬል ታሪክ ምሁር ቱምባ አልፍሬድ ሻንጎ ሎኮሆ ተናግረዋል። ሻንጎ ሎኮሆ ለDW እንደተናገሩት «በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በስልጣን ላይ የሙጥኝ ያሉ ጠንካራ ሰዎች ናቸው።በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ፤ህገ መንግስቶችን ወደ ጎን በመተው በማንኛውም መንገድ እየገለባበጡት ነው ።ይህ በትክክል ከአፍሪካ ታላላቅ ድክመቶች አንዱ ነው። ጠንካራ ተቋማት እንፈልጋለን።» ብለዋል።
የፈረንሳይ የፖለቲካ ተጽእኖ እየቀነሰ ነው
ማቲያስ ባሴዳው እንደሚሉት አብዛኛዎቹ እነዚህ ተቋማት የተፈጠሩት በ 1960 በፈረንሣይ ሞዴል ላይ በመመስረት ነው ፣ : «ሁልጊዜ ይህ ፕሬዚዳንትነት አለ። እሱም ከፈረንሳይ የበለጠ ፕሬዚዳንታዊ እና ፈላጭ ቆራጭ ነው። እና ብዙዎቹ ሕገ-መንግሥቶችም እንዲሁ በፈረንሣይ ሞዴል ተቀርፀዋል።በእርግጥ አንዳንድ ልዩነቶች አሉ።ምናልባት እዚህ ያለው ልዩ ባህሪ ለሀይማኖት የወገነ አለመሆኑ እና የሃይማኖት እና የመንግስት ጥብቅ ትስስር መለያየቱ ነው። ይህም በቀጠናው ሃይማኖታዊ መድልዎ እንዳይኖር አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።» ብለዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ መንግስታት ከፈረንሳይ መለያየታቸውን ገፍተውበታል። ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ መቃቃር ባደገበት እና አንዳንዴም በቀድሞው ቅኝ ገዥ ሃይል ላይ ጠንካራ ንግግሮች በሚሰነዝሩበት የሳህል ሀገራት ውስጥ ይህ በግልፅ ይታያል። ሶስቱም ወታደራዊ ጁንታዎች እዚያ የሰፈሩትን የፈረንሳይ ወታደሮች አስወጥተዋል። እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በፀጥታ አጋርነት በሩስያ ላይ ከፍተኛ እምነት ነበራቸው። በዚህም ምክንያት የፈረንሳይ ወታደሮች የጦር ሰፈሮቻቸውን ለቀው ከቻድ፣ ከሴኔጋል እና ከአይቮሪ ኮስት ወጥተዋል።
በጋቦን የሚገኘው የጦር ሰፈር የአካባቢውን ወታደሮች ለማሰልጠን ብቻ ያገለግላል። የፈረንሳይ ጦር ያላት ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር አሁን ጅቡቲ ናት።የፈረንሳይ አፍሪካ ፖሊሲ ቁልፍ ግብ ሁል ጊዜ የፍራንኮ ደጋፊ የሆኑትን መንግስታት በተቻለ መጠን በስልጣን ላይ ማቆየት ነው ይላል ማቲያስ ባሴዳው። ካሜሩን አሁን በዚህ ረገድ ከመጨረሻዎቹ ባስኮች አንዱ ነው: "ነገር ግን ፖል ቢያ በስልጣን ላይ በማይኖርበት ጊዜ ምን እንደሚመስል ማየት አለብን."
ከፈረንሳይ ጋር የጠበቀ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ቀጥሏል
የፈረንሣይ እና የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ተጽእኖ እየቀነሰ ቢመጣም በፈረንሣይ እና በብዙ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንደ ጥሬ ዕቃ ማውጣት ያለ ስራ አሁንም እንደቀጠለ ነው። አንዳንድ ሱቆች እና የገበያ ሰንሰለቶች ፣ ነዳጅ ማደያዎች እና የተንቀሳቃሽ ስልክ አቅርቦትም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አሁንም በፈረንሳይ እጅ ናቸው።
በሁለቱ የምዕራብ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች የጋራ ገንዘብ «ሲኤፍኤ ፍራንክ» ተብሎ ይጠራል። የራሳቸውን የገንዘብ ፖሊሲ ከመፍቀድ ይልቅ ከዩሮ ጋር በቋሚ ምንዛሪ ተመን ስለሚያስተካከሉ እንደ ቅኝ ገዥ በየጊዜው ይተቻሉ።
በተመሳሳይ ጊዜ ግን በመካከላቸው የንግድ ልውውጥን እንዲኖር ያመቻቻል።ሲሉ ባስዴው ጠቁመዋል።«በፍራንኮፎን አፍሪካ ያለው የዋጋ ግሽበት በጣም ዝቅተኛ ነበር፣በተለይ በብሪታኒያ ተፅዕኖ ስር ከነበሩ ጎረቤቶቻቸው ጋር ሲወዳደር።» ሆኖም ባሴዳው የፈረንሳይ የተቀናጀ አካሄድ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገትን አደናቅፏል ብለው መፍረድ እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።
ከ65 ዓመታት ነጻነት በሁዋላ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው መንገድ ሄደዋል። - ይህ በተለይ ለብዙ ዜጎቻቸው እውነት ነው፡። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከውጭ ሀገር የሚላኩ የዳያስፖራ ገንዘብ ለአንዳንድ ሀገራት አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል። ለምሳሌ፣ ወደ 110,000 የሚጠጉ ሴኔጋላውያን በፈረንሳይ ይኖራሉ። በሴኔጋል፣ ወደ አገር ቤት ዘመዶቻቸው የሚላክ ገንዘብ በቅርቡ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከአሥር በመቶ በላይ ይሸፍናሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚላከው ገንዘብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ በቀጥታ ለገጠሩ ህዝብ እና አብዛኛውን ጊዜ ለድሆች እንደሚውል ይገመታል።ባለፉት 65 ዓመታት በፍራንኮፎን አፍሪካ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፣ቢያንስ በአንፃራዊነት የተሻለ ነው፡- በአብዛኛዎቹ አገሮች በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል፣አማካኝ ዕድሜ ጨምሯል፣የህፃናት ሞት ቀንሷል።
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ