የየተራዘመው የፈረንሳይ የጡረታ መውጫ እድሜ የገጠመው ተቃውሞ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 2015
የፈረንሳይ መንግሥት በዚህ ዓመት ተግባራዊ ሊያደርግ ያቀደው የጡረታ መውጫ እድሜ ማሻሻያ ህዝቡን አስቆጥቷል። የጡረታ መውጫ እድሜን በሁለት ዓመት ያራዘመውን ማሻሻያ በመቃወም ባለፈው ሐሙስ በመላ ፈረንሳይ የስራ ማቆም አድማና ኃይል የቀላቀሉ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሏል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት የኢማኑኤል ማክሮ መንግሥት በፈረንሳይ የጡረታ መውጫ እድሜን ከእስካሁኑ 62 ወደ 64 ዓመት ከፍ የሚያደርግ የጡረታ ማሻሻያ በዚህ ዓመት ስራ ላይ እንዲውል ያጸደቀው ሕግ ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሏል። ባለፈው ሐሙስ የሠራተኛ ማኅበራት በመላው ፈረንሳይ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የጠሩዋቸው የተቃውሞ ሰልፎች በሀገሪቱ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ ገድበው ነበር።አመጽ በተቀላቀለባቸው በነዚሁ ሰልፎች በፖሊሶች ላይ ጉዳት ደርሷል። ተቃውሞው የንብረት ውድመትም አስከትሏል። በእለቱ በዋና ከተማይቱ በፓሪስ ከተማ ዙሪያ በ900 ስፍራዎች እሳት ተቀጣጥሎ ነበር። የበርካታ ህንጻዎች መስታወቶችም ተሰባብረዋል። የፓሪስ የጽዳት ሠራተኞች ስራ በማቆማቸው ምክንያት ያልሰበሰቡዋቸውን ቆሻሻዎች ጽንፈኛ ስርዓተ-አልበኞች የተባሉ ቡድኖች፣ በየስፍራው ከምረው ከተማዋን የቆሻሻ ማጠራቀሚያ አድርገዋታል። በተቃውሞ ሰበብ ካለፈው እሁድ እስከ ነገ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የብሪታንያው ንጉስ ቻርልስ ሶስተኛ የፈረንሳይ ጉብኝት ለሌላ ጊዜ እንዲገፋ ተደርጓል። ዩሮ ስታር በተባለው የፈረንሳይ የቤልጅየምና የብሪታንያ የባቡር አገልግሎት ሰጭ ኩባንያ ውስጥ የሚሰሩት የፓሪስ ነዋሪ አቶ ናቲ ብሩክ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ባለፈው ሐሙስተ ቃውሞውን ለመግለጽ የወጣው ህዝብ ቁጥር እስከዛሬ በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ከተገኘው ከፍተኛው ነበር ። በስራ ማቆም አድማ ምክንያት በዋና ከተማይቱ በፓሪስ ከተቋረጡት ልዩ ልዩ አገልግሎቶች መካከል የከተማዋ ጽዳት አገልግሎት አንዱ እንደነበርም ተናግረዋል። አቶ ናቲ የጡረታ እድሜ መራዘሙን ከሚቃወሙ የፈረንሳይ ሰራተኖች አንዱ ናቸው። እንደ አቶ ናቲ ሁሉ በርካታ የፈረንሳይ ሰራተኞች የተሻሻለውን ደንብ ይቃወማሉ ።በሐሙሱ ሰልፍ የተሳተፉት ስቴፋኒ ቤጋውድ በማሻሻያው አይስማሙም የጡረታ መውጫ እድሜ ማሻሻያውን ዋስትና የሚያሳጣ ነው ያሉት።
«የምናገኘው ከድኅነት ወለል በታች የሆነ ደሞዝ ነው።በወር 860 ዩሮ ነው የሚከፈለን ደኅንነት እንዳይሰማን እየተደረግን ነው። በትርፍ ጊዜያችን ለመስራት እየተገደድን ነው።ብዙ እንድንሰራ ተጠይቀናል፤እኛ ግን አንስማማም። አሁን ጠርዝ ላይ ነው ያለነው። አሁን በጣም የተወሳሰቡ ሁኔታዎች ውስጥ ነው ያለነው።የጡረታ ማሻሻያውም እንዲሁ። »
አመጽ በተቀላቀለበት የሐሙሱ ተቃውሞ 441 የፀጥታ ኃይሎች መቁሰላቸውን የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አስታውቋል። ከ450 በላይ ሰዎችም ታስረዋል። ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ላይ የሚገኙት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ልዩ ሕገ መንግሥታዊ ኃይላቸውን በመጠቀም በህዝብ ተወካዮች ድምጽ ሳይሰጥበት የጡረታ እድሜ ማሻሻያ ደንቡን ለማጽደቅ መሞከራቸው ያስነሳው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሏል። በርካታ ሰዎች ተካፍለውበታል ለተባለው ለዛሬው ተቃውሞ በመላ ፈረንሳይ 13 ሺህ የፀጥታ ኃይሎች መሰማራታቸውን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።ከመካከላቸው ግማሽ የሚሆኑት ፓሪስ ውስጥ ነበሩ። የአገር ጎብኚዎች መስህብ የሆነው ፓሪስ የሚገኘው የአይፍል ማማ በስራ ማቆም አድማው ምክንያት ተዘግቷል።የፓሪስ ጎዳናዎች ዛሬም ቆሻሻ እንደተከመረባቸው ነው። በአዲሱ ሕግ የጡረታ መውጫ እድሜ በሁለት ዓመት ከመራዘሙ በተጨማሪ፣ አንድ ሠራተኛ ሙሉ ጡረታውን ለማግኘት 43 ዓመት መሥራት ይኖርበታል።አለበለዚያ 67 ዓመት እስኪሞላው ድረስ መጠበቅ አለበት። የማክሮ መንግሥት ሕጉን ለማጽደቅ አንድ ረቂቅ ሕግ ድምጽ ሳይሰጥበት እንዲያልፍ ማድረግ የሚያስችለውን የሀገሪቱን ህገ መንግሥት አንቀጽ49 ንዑስ አንቀጽ 3ን በመጠቀም ነው። ሕጉን ለማስቆም በማክሮ መንግሥት ላይ ሁለት ጊዜ የመታመኛ ድምጽ ተስጥቶ ነበር ። ብዙሀኑ ባለመቃወማቸው ለማክሮ መንግሥት ሕጉን የማጽደቅ እድል ሰጥቷል።
በሐሙሱ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተካፈሉት ጀርሚ ፈርናንዴስ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 3 ለኔ ሕጋዊ አይደለም በማለት እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
«እንደሚመስለኝ መንግሥት ይህን ሕግ ያሳለፈበት መንገድ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ቢሆንም ፣ቢያንስ ለዚህ ለአምስተኛው ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ድምጹን ያልሰጠው የኔ ትውልድ ትክክል ነው አይልም። እኛ የተለየ አስተዳደር ነው የምንፈልገው። በኔ አመለካከት የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 3 ሕጋዊ አይደለም።
ተቃውሞው የበረታባቸው ማክሮ በተለይ በሰልፎቹ የተከሰቱ የኃይል እርምጃዎችን አጥብቀው አውግዘዋል። መንግሥታቸው ለዚህን መሰሉ አመጽ እንደማያጎበድድም አጽንኦት ሰጥተው ነው የተናገሩት
«ለኃይል እርምጃ እጃችንን አንሰጥም።አናደርገውም፤በዲሞክራሲ የኃይል እርምጃ የመውሰድ መብት የለም። ከፖሊስ ኃይሎቻችንም ስነ ምግባርን ሙሉ በሙሉ ማክበር ይጠበቃል። ይህም ሆነ ምርመራውከግልጽነት ጋር አብሮ መሄድ ይገባዋል። ይሄን ግን ብዙሀኑ ማኅበረሰብ ውስጥ ከሚሆነው ጋር አላወዳድረውም።ለኃይል እርምጃ እጃችንን አንሰጥም፤ሊገልጸው በሚችለው መንገድ ሁሉ በጥብቅ እናወግዘዋለን።»
ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ የምጣኔ ሀብትና የስራ አስተዳደር ባለሞያ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ይህን መሰሉ የጡረታ ደንብ ማሻሻያ በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአውሮጳ ሀገራትም ተግባራዊ እየሆነ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት የዚህ ምክንያቱ በነዚህ ሀገራት በእድሜ የገፋው ህዝብ ቁጥር መጨመርና የወደፊቱ ሰራተኛ ኃይል የወጣቱ ቁጥር ማነስ ነው። ይሁንና በአውሮጳ የጡረታ መውጫ እድሜ መራዘም የብዙ ሠራተኖች ፍላጎት አይደለም። ወደፊት ለጡረታ የሚከፈል ገንዘብ የለንም የሚሉት መንግሥታት ደግሞ የጡረታ መውጫ እድሜን ማራዘማቸውን ገፍተውበታል። የእርምጃው ተቃዋሚዎች መንግሥታት ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል።
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር