1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ ጦር ዘመቻ፤ማሊና ሶማሊያ

ሰኞ፣ ጥር 6 2005

ባጭር ቃል-ፈረንዮች ሶማሊያ ላይ ተሸነፉ።ከዓለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት ከአል-ቃኢዳ ጋር ያበረዉ፥ በአፍሪቃዉያን ጦር ዉጊያ የተዳከመዉ አሸባብ ባንፃሩ ታላቅ «ድል» አስመዘገበ።---ፕሬዝዳት ኦላንድ መፅናኛ ማሊ አለችላቸዉ

A French Rafale fighter jet lands in Ndjamena, Chad, before being deployed in Mali, in this picture provided by the French Military Communications Audiovisual office (ECPAD) and taken on January 13, 2013. Al Qaeda-linked Islamist rebels in Mali launched a counter-offensive on Monday after three days of strikes by French fighter jets on their strongholds in the desert north, vowing to drag France into a long and brutal ground war. Photo taken January 13, 2013. Mandatory Credit. REUTERS/Adj. Nicolas-Nelson Richard/ECPAD/Handout (FRANCE - Tags: MILITARY POLITICS TRANSPORT) ATTENTION EDITORS - THIS IMAGE WAS PROVIDED BY A THIRD PARTY THIS PICTURE IS DISTRIBUTED EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS AS A SERVICE TO CLIENTS. NO SALES. NO ARCHIVES. FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS. THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS. MANDATORY CREDIT
የፈረንሳይ ተዋጊ ጄት ማሊምስል Reuters


14 01 13

ለፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ሊቢያ የዋሽንግተን ለንደን፣ አቻዎቻዉን ያሳበሩባት፣የሪያድና የቀጠር ታማኞቻቸዉን ያስከተሉባት፣ ከሌሎች የተቋደሷት የጋራቸዉ ነበረች።ኮትዲቫር ግን በአቻ-ተከታዮቻቸዉ ፍቃድ፣ የብቻቸዉ።ለፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ሶማሊያ ወይም ሶሪያ ከሌሎቹ የሚቃመሷት የጋራቸዉ ነች።ማሊን ግን፣ሌሎችን የሚያስከትሉባት የብቻቸዉ አደረጓት።ኦሎንድ ሶማሊያ ላይ ቢያንስ ላሁኑ ከሸፈባቸዉ።ማሊ ላይ የሚወቁት፣ ሳርኮዚና ተሻራኪዎቻቸዉ የቃዛፊን ጥፋት-ከነሕይወታቸዉ ሲያጠፉ ሊቢያላይ የዘሩት ጥፋት-ምርት መሆኑ ነዉ ግራዉ።ለአንባገነኖች እብሪት፥ ለአክራሪዎች እብደት፣ ለምዕራቦች ፡ጥቅም ሚሊዮኖች መጥፋት፣መሰቃየታቸዉ ደግሞ ያሳዝናል።የአስተምሕሮቱ እንዴትነት ያጠያይቃል።ላፍታ አብረን እንጠይቅ።


DGSE በሚል የፈረንሳይኛ ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የፈረንሳይ የሥለላ ድርጅት ልዩ ጦር ባልደረባ ዴኒ አሌክስና ጓደኛዉ ሶማሊያ የገቡበት ዕለት፥ መንገድ፥ ሶማሊያ ዉስጥ የሠሩት ያኔም-አሁንም ድብቅ ነዉ።ዓላማቸዉ ግን ብዙ ያልተብራራ-ግን በግልፅ የሚታወቅ ነዉ።ሥለላ።


የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ሐምሌ-ሁለት ሺሕ ዘጠኝ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከማረካቸዉ ወዲሕ የአጋቾቹ አሸባሪነት፥ ኢሰባአዊነት፥ የታጋቾቹ መሰቃየት፥ ከታጋቾቹ አንዱ የማምለጡ ጀግንነት በየመገናኛ ዘዴዉ ሲፈጭ-ሲቦካ፥ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የሚደረገዉ ድርድር፥ የተወሰደና የሚወሰደዉ እርምጃ በሚስጥር እንደተያዘ ታጋቾቹን ያዘመቱት ፕሬዝዳት ሳርኮዚ በፕሬዝዳት ኦላንድ ተከቱ።

ኦሎንድ ሳርኮዚ እንዳዘመቱት አሸባብ እጅ የወደቀዉን ሠላይ ለማስለቀቅ ካለፈዉ አርብ ሌሊት የተሻለ ቀን አላገኙም ነበር።ማሊ ያዘመቱት ጦር የቀድሞ የሐገራቸዉን ቅኝ ተገዢ ሐገር ሰሜናዊ ግዛት የሚቆጣጠሩትን አማፂያንን በጄት-የመደብደቡ ዜና ሳይቀዘቅዝ፥በዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶች የታጀቡት የፈረንሳይ የጦር ሔሊኮብተሮች ሶማሊያን የአየር ክልል እየገመሱ ከሚሹት ደረሱ።

«የከባድ ተኩስ ድምፅ ከእንቅልፋችን ቀሰቀሰን» አሉ አንድ የቡሎ ማረር ከተማ ነዋሪ።«ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ነበር» አከሉ።ከተማይቱ ላፍታ ተንቀረቀበች።በዩናይትድ ስቴትስ ጦር የታገዘዉ የፈረንሳይ ልዩ ኮማንዶ ጦር አስራ-ሰባት የአሸባብ ተዋጊዎችን መግደሉ ተነግሯል።ታጋቾን ግን አላስለቀቀም።ምናልባትም አስገድሎት ይሆናል።የአንድ ባልደረባዉን አስከሬን ይዞ፥ ሌላ ቁስለኛዉን ለማዉጣት እንኳ ጊዜ-አጥቶ ወደመጣበት እብስ አለ።

መከላከያ ሚንስትር ኢቭ ለ ድርዮ ምክንያት አላጡም።

«አፀፋዉ ጥቃት ከጠበቅነዉ በላይ ጠንካራ ነበር።በተለይ ከባድ መሳሪዎቹን ከግምት አላስገባናቸዉም ነበር።ዴኒ አሌክስ ለሰወስት ዓመት ከመንፈቅ ሰብአዊነት በጎደለዉ ሁኔታ እንደታገተ ነዉ።እሱን ለማስለቀቅ ያደረግነዉ ድርድርም መና ነዉ የቀረዉ።እዚያ እንደታሰረ እርግጠኞች ነበርን።(አካባቢዉን) ያጠቃነዉም እሱን የማስለቀቅ ግዴታ ሥለነበርብን ነዉ።»

ባጭር ቃል-ፈረንዮች ሶማሊያ ላይ ተሸነፉ።ከዓለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት ከአል-ቃኢዳ ጋር ያበረዉ፥ በአፍሪቃዉያን ጦር ዉጊያ የተዳከመዉ አሸባብ ባንፃሩ ታላቅ «ድል» አስመዘገበ።የአሸባብ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ፕሬዝዳት ሳርኮዚ ያዘመቱት ሰላይ ወታደር ዴኒ አሌክስ አልሞተም።የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ግን ሞቷል ባይ ናቸዉ።

አሌክስ ኖረም-ሞተ ለፕሬዝዳት ኦላንድ መፅናኛ ማሊ አለችላቸዉ።የማሊዉ ዉጥንቅጥም ልክ እንደ ሱማሊያዉ ሁሉ ሳርኮዚ ከሊቢያ ምሥቅልቅል ያስተረፉት ነዉ።መሠረቱ ግን፥ የአዉሮጳ በተለይ የፈረንሳይ ቅኝ ቀዢዎች ሰሜን እና ሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃን ከረገጡበት ጊዜ ጀምሮ የሚታይ ሩቅ፥ ታሪኩም ረጅም ነዉ።

ለፕሬዝዳንት ኦላንድና ለተባባሪዎቻቸዉ ግን ረጅሙ ታሪክ አሰልቺ፥ ትክክለኛዉ ምክንያትም ዋጋቢስ ነዉ።ሰሜናዊ ማሊን የሚቆጣጠሩ ሐይላትም ከማሊ አልፈዉ ፈረንሳይን የሚያሰጉ አሸባሪዎች ናቸዉ።


«ከአሸባሪዎች ጋር የሚደረገዉ ዉጊያ ፈረንሳይ ዉስጥም ሁሉንም አይነት የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስገድድ ነዉ።የመንግሥት ሕንፃዎች በሙሉ እና የመገናኛ አዉታሮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸዉ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጠይቄያለሁ»

የበርበር ነገድ አባል የሆነዉ የቱአሬግ ጎሳ ለፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች አሜን ብሎ የገበረበት ዘመን የለም።አግ መሐመድ ዋዉ ቴጉይዳ ካሴን የመሩት የቱአሬግ ተዋጊ ሐይል በ1880 በፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎችና በአካባቢዉ ተባባሪዎቻቸዉ ላይ የከፈተዉን ጥቃት ለመደፍለቅ የፈረንሳይ ጦርና ተባባሪዎቹ ድፍን አስር ዓመት መዋጋት ግድ ነበረበት።

የቱአሬግ ነገድ በብዛት የሠፈረባቸዉ ማሊና ኒጀር እንደ ብዙዎቹ ቅኝ ተገዢ የአፍሪቃ ሐገራት ሁሉ በፈረንሳዮች ፍቃድና ይሁንታ የየራሳቸዉን ባንዲራ ቢሰቅሉም የፓሪሶችን ጥቅም፥ፍላጎትና ትዕዛዝ ከማስፈፅም አለማለፋቸዉ፥ ነፃነቱ ለቱአሬጎች «ያዉ በገሌ» አይነት ቅሬታና ኋላም ቁጣን ነዉ የቀሰቀሰዉ።

በዚሕም ሰበብ ከ1962 ጀምሮ የባማኮና የንያሚ ገዢዎችን አጋዛዝ በመቃወም በተደጋጋሚ አምፀዋል። አመፃቸዉ በፈረንሳይ በሚታገዙት ገዢዎች በተደፈለቀ ቁጥር መሸሺጊያቸዉ ደቡብ ምሥራቅ አልጄሪያ፥ ደቡብ ምዕራብ ሊቢያ እና ሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ ነዉ።

የሊቢያዉ ገዢ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ትሪፖሊ ላይ ከተጠናከሩ በሕዋላ ደግሞ ሊቢያ ለቱአሬግ ተወላጆች መሸሸጊያ ብቻ ሳትሆን የጥሩ ገቢ ምንጭ፥ ጥራ ሥራ-ማግኚያ፥ ጥሩ መኖሪያ፥ በወታደርነት መሠልጠኛ፥ መቀጠሪያም ሐገር እንደሆነች ከቃዛፊ ዉድቀት ቀጥለለች።

በፕሬዝዳት ሳርኮዚ አስተባባሪነት፥ በፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እና በጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ድጋፍ ሰጪነት ሊቢያ የዘመተዉ የምዕራባዉን ጦር ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከረጅም ዘመን አጋዛዛቸዉ ጋር ሲያጠፋ የጋዛፊ ጦር ባልደረባ የነበሩት የቱአሬግ ተወላጆች ከነ-ሙሉ ትጥቃቸዉ ወደ ሰሜን ማሊ ገቡ።እና አዲስ አመፅ።

የመግሪብ አል-ቃኢዳ ከሚባለዉ አሸባሪ ቡድን የተገነጠሉ ሐይላት፥እና የሌሎች አሸባሪ ድርጅት አባላት ሰሜናዊ ማሊ ዉስጥ መመሸጋቸዉ አያጠያቅም።የሰሜን ማሊን አብዛኛ ግዛት ከመንግሥት ጦር የማረኩት፥ የሚቆጣጠሩት ግን አንሳር ዲን እና MNLA በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠሩት ሐይላት ናቸዉ።ሁለቱም ቡድኖች በሊቢያ ጦር ዉስጥ እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ በደረሱ የጦር መኮንኖች የሚመሩ፥ በቅጡ የታጠቁ ሐይላት ናቸዉ።

ቃዛፊንና ሥርዓታቸዉን እስከ መግደል ብቻ ባለመዉ በሊቢያ አማፂያንና በምዕራባዉን ደጋፊያቸዉ ጦርና በቃዛፊ ታማኞች መካካል በተደረገዉ ዉጊያ በሺ የሚቆጠሩ ሊቢያዉያንን ተገድለዋል።በቢሊን የሚቆጠር ሐብት ንብረት ወድሟል።ቱአሬጎችን ጨምሮ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አፍሪቃዉያን ተበትነዋል።መቶዎችን ለባሕር ሲሳይ ዳርጓል።

ዘመቻዉ በራሷ በሊቢያና በአካባቢዉ ሐገራት የወደፊት ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረዉ አሉታዊ ተፅዕኖ ከቁብ ስላልገባ የሰሜን ማሊ ሕዝብ ሁለተኛዉ ገፈት ቀማሽ ሆኗል።ሰሜናዊ ማሊን የሚያብጠዉ ጦርነት በሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ተገድሏል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገመተዉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አድም ተሰዶ፥ አለያም ተፈናቅሎ የዉጪ እርዳታ ጥገኛ ነዉ።

እንደ ፓሪሶች ሁሉ፥ ፓሪሶች ጦር ያዘመቱባቸዉ የማሊ አማፂያን አሁንም ለሌላ ጥፋት ይፎክራሉ።

«ለፈረንሳዮች የምናስተላልፈዉ መልዕክት፥ ጉዳዩ አሁንም በእጃችሁ ነዉ።የጠላትነት እርምጃችሁን አቁሙ።ይሕን ካላደረጋችሁ ግን የልጆቻችሁን መቃብር እየማሳችሁ፥ ወደ ገሐነብ እየሰደዳችኋቸዉ ነዉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈዉ ሐሙስ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀዉ ዉሳኔ ቁጥር 2085 ከወታደራዊ ዘመቻዉ በፊት በአማፂያንና በማሊ ጊዚያዊ መንግሥት መካካል የሚደረገዉ ድርድር እንዲቀጥል ይደነግጋል።

የአንሳር ዲን እና የMNLA ቡድናት ተወካዮች ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ላለፈዉ ሐሙስ ቀጠሮ ነበራቸዉ።ዋጋዱጉ-ቡርኪናፋሶ ዉስጥ ይደረጋል የተባለዉ ድርድር በግልፅ ባልተነገረ ምክንያት ወደ ጥር አጋማሽ መዛወሩ በተሰማ ማግስት ግን ሰሜናዊ ማሊ በፈረንሳይ ጄቶች ትጋይ ገባች።


የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ «ፖለቲካዊ ሒደት» ያሉትን የማሊን ተቀናቃኞችን የማደራደሩን ጥረትና መንግሥታቸዉ እንደሚረዳ አስታዉቀዋል።

«የጀርመን ተዋጊ ወታደሮች በዉጊያዉ ይሳተፋሉ ማለት ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም።ይሁንና የፖለቲካዊዉን ሒደት ለማገዝ ዝግጁ ነን።»

ቬስተርቬለ «ፖለቲካዊ ሒደት» ያሉትም ሆነ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድርድር እንዲቀድም መወሠሰኑ ወይም፥ተፋላሚዎችን ለማደራደር ሌላ ቀጠሮ መያዙ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ከእንግዲሕ የሚፈይደዉ መኖሩ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

ሰወስት ሺሕ ጦር ለማዝመት ከተዘጋጁት ከምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ አባል ሐገራት መካከልም ናይጄሪያና ሴኔጋል በሺሕ የሚቆጠሩ ወታደሮች አዝምተዋል።ፕሬዝዳት ሳርኮዚ ሎራ ባግቦን አሳስረዉ የኮትዲቯርን የመሪነት ሥልጣን ያስረከቧቸዉ አላሳኔ ዋተራም የሐገራቸዉ ጦር እንዲዘምት አዘዋል።

በወርቅ ማዕድን ከአፍሪቃ የሰወስተኝነቱን ደረጃ የያዘችዉ፥ በጥጥ፥ በማንጎ ምርቷ የታወቀችዉ ሰፊ፥ ደሐ፥ በረሐማ፥ ወደብ አልባዊቱ ሐገር የተደገሰላት ጦርነት ወዴት እንደሚያመራት ከግምት በላይ መናገር ላሁኑ በርግጥ ስሕተት ነዉ።በጣልቃ ገብ ጦሩ ዘመቻ፥ በዉጊያ ፉከራዉ መሐል የሚነገረዉ ድርድር እና ፖለቲካዊ ሒደት፥ ከአስራ-አንድ አመት ጦርነት በሕዋላ ከአፍቃኒስታን ታሊባኖች ጋር የሚደረገዉ አይነት ማለት ከሆነ ግን አስራ-አንድ ዓመት መጠበቅ ይኖርብናል።ለዛሬ ይብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ


















የማሊ ስደተኞች-ቡርኪናፋሶምስል DW/Peter Hille
የአንሳር ዲን ተዋጊዎችምስል Romaric Ollo Hien/AFP/GettyImages
ፕሬዝዳንት ኦላንድምስል AP
የፈረንሳይ ተዋጊ ጄት ማሊምስል Reuters
ታጋቹ ዴኒ አሌክስምስል picture-alliance/dpa/IntelCenter
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW