1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አማራ ክልል በፋኖ ኃይሎችና በመንግሥት ወታደሮች ውጊያው ቀጥሏል ተባለ

ዓርብ፣ ጥቅምት 7 2018

ሰሞኑን በፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ መኖሩ ተገለጠ ። በውጊያው የፋኖ ኃይሎች ተጨማሪ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውም ተገልጧል ። የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ «ጽንፈኛ» ሲሉ የገለጡት ኃይል ትንኮሳ ከመፈጸም ውጪ በየቦታው የመዋጋት አቅም የለውም ብለዋል ።

በአማራ ክልል መልክአ ምድር
በአማራ ክልል መልክአ ምድርምስል፦ Esayas Gelaw/DW

ውጊያ በአማራ ክልል

This browser does not support the audio element.

ትናንትና ምሽትን ጨምሮ ሰሞኑን በፋኖ ኃይሎች እና ኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች መካከል በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ መኖሩ ተገለጠ   በውጊያው የፋኖ ኃይሎች ተጨማሪ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውም ተገልጧል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ «ጽንፈኛ» ሲሉ የገለጡት ኃይል ትንኮሳ ከመፈጸም ውጪ በየቦታው የመዋጋት አቅም የለውም ብለዋል ።

የፋኖ ኃይሎች በሰሜን ወሎ ዞን 

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን በነበሩ ውጊያዎች  የፋኖ ኃይሎች  በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ተገለጠ ።  ደቡብ ጎንደ እና ሰሜን ወሎ መገናኛ ቦታ በሆነችው ጨጨኾ ነዋሪ የሆኑ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፦ ጨጨኾ፣ ዘቢጥ፤ ገረገራ እና አፍላቂትን ጨምሮ ዙሪያውን የፋኖ ኃይሎች እንደያዙት ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። 

የፋኖ ኃይሎች በሰሜን ወሎ ዞን ብቻ ስድስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን ደግሞ የጨጨኾ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሻለቃ ሚኪያስ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ትናንት የመንግስት ወታደሮች ራያ ቆቦ በሚባል ቦታ ተኩለሽን አልፎ ሙጃ እና ኩልመስክን ለመቆጣጠር ሙከራ ቢያደርጉም ብርቱ ጉዳት እንደደረሰባቸውም አክለዋል ። «ፋኖዎች ወደ ኋላ እንደማፈግፈግ አሉለት፥ ተስቦ ገዥ ቦታ ሲገባ የስበት ማእከልን በመጠቀም አንድ ሠራዊት እንኳን ይዞ አልወጣም» ብለዋል ።

የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር

የመከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ጌትነት አዳነ ስለ ሁኔታው እንዲነግሩን በእጅ ስልካቸው ደውለን ብናጠይቃቸውም ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን በኩል ካልመጣ መልስ እንደማይሰጡ ዐሳውቀዋል ። የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ «ጽንፈኛ» ሲሉ የገለጡት ኃይል ትንኮሳ ከመፈጸም ውጪ በየቦታው የመዋጋት አቅም የለውም ብለዋል ። የተለየ ዝርዝር የሚሰጡት ነገር እንደሌለ በመጥቀስም ቀጣዩን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

«የተለየ መረጃ አድርገን የምንነግረው የለም ለሚዲያ የሚሆን፥ ጽንፈኛው ቡድን በየቦታው ትንኮሳ ነው የሚፈጽመው እንጂ ቆሞ የመዋጋት አቅም አደረጃጀትም የለውም» ሲሉም አክለዋል ። 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Solomon Muchie/DW

ሌላ የፋኖ ታጣቂ በበኩላቸው፦ በሰሞኑ ውጊያ ሣንቃ፣ ዘቢጥ እና ዲባላን የመሳሰሉ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን ገልጠዋል ። «በፋኖ ቁጥጥር የገቡ ብዙ ወረዳዎች፤ ብዙ ቀበሌዎች አሉ አሁን ሰሞኑን በተደረገው [ኦፕሬሽን]ማለት ነው ። ጨጨኾ፤ ሣንቃ፣ ዘቢጥ፣ ዲባላ እና እነዚህ የመሳሰሉ ቦታዎች ያለበት የእኛ ኃይል ነውም ብለዋል ።

ውጊያው በአሁኑ ወቅት

ሰሜን ወሎ ላስታ ብልብላ ነዋሪ የሆኑ ሌላ አንድ ነዋሪ ያሉበትን አካባቢ ለረዥም ጊዜ የፋኖ ኃይሎች እንደተቆጣጠሩ በመግለጥ በሰሞኑ ውጊያ  በአካባቢያቸው እንዳልነበር ተናግረዋል ። «ያው አሁን ሰላምነው ለዚህ ሁለት ቀን ያህል» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ። 

በዛሬው ዕለትም ሰሜን ወሎ ሣንቃ የሚባል ቦታ ትንሽ ከፍ ብሎ በቅሎ ማነቂያ በሚባል ቦታ ዛሬም ውጊያ እንደነበር ተገልጧል ።  ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ለመጠየቅ የክልሉ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው ጋር በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ብንደውልም ጥሪያችን ምላሽ አላገኘም ። በፋኖ ታጣቂዎች ተያዙ ስለተባሉ ቦታዎችም ሆነ በሰሞነኛው ውጊያ ስለተከሰቱ ጉዳዮች ዶይቸ ቬለ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ማግኘት አልቻለም ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW