1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግገው አዋጅ ተሻሻለ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 23 2017

አዋጁ "አሁን ባለበት ሁኔታ ለጊዚያዊ አስተዳደር ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ የሁለት ዓመት ከግማሽ ሲሆን ይህ መነሻ በትግራይ ክልል ካለው ነባራዊው ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ሆኖ ተገኝቷል" የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ነው። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ብልጅጌ ይህንኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ።ምክር ቤቱ በ1995 የወጣዉን ደንብ ያሻሻለዉ የትግራይ ክልል ጊዜያው አስተዳደርን የሥራ ዘመን ለማራዘም በማስፈለጉ ነዉ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ።ምክር ቤቱ ዛሬ ባደረገዉ ጉባኤዉ የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግገው አዋጅ ተሻሻሏል ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግገው አዋጅ ተሻሻለ

This browser does not support the audio element.

የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዐት ለመደንገግ በ1995 ዓ.ም የወጣው አዋጅ የትግራይ ክልል ጊዜያው አስተዳደርንየሥራ ዘመን ለማራዘም በማስፈለጉ ዛሬ በአብላጫ ድምጽ ማሻሻያ ተደረገበት።ነባሩ አዋጅ "አሁን ባለበት ሁኔታ ለጊዚያዊ አስተዳደር ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ የሁለት ዓመት ከግማሽ  ሲሆን ይህ መነሻ  ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የማይጣጣም" ሆኖ በመገኘቱ መሻሻሉ ተነግሯል።

በሌላ በኩል "አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዐፈ ጉባኤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቆይታ እስከ አንድ ዓመት ድረስ እንዲራዘም ሊወስን ይችላል" የሚል ማሻሻያ ተደርጓል።አዋጁ በክልሎች "የፀጥታ መደፍረስ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ ሲኖር" የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የሚያደርግ ነው።//

አዋጁን ለማሻሻል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች

ከ22 ዓመታት በፊት የተደነገገውንና የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግገውን አዋጅ ማሻሻል ያስፈለገው በሁለት ችግሮች ምክንያት ስለመሆኑ ተገልጿል።የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታን ለማራዘም ውሳኔ የሚሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚሰበሰብ መሆኑና የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታን ማራዘም ሲያስፈልግ በአጭር ጊዜ ስብሰባ በመጥራት ውይይት አድርጎ ውሳኔ ለመሥጠት የሚያስቸግር ስለሆነ የምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ የምክር ቤቱ ስብሰባ እስኪደረግ ድረስ አፈ ጉባዔው የጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ አንደኛው ነው።

 

አዋጁ "አሁን ባለበት ሁኔታ ለጊዚያዊ አስተዳደር ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ የሁለት ዓመት ከግማሽ ሲሆን ይህ መነሻ በትግራይ ክልል ካለው ነባራዊው ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ሆኖ ተገኝቷል" የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ነው። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ብልጅጌ ይህንኑ አብራርተዋል።

"በአዋጁ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የማይጣጣም ሆኖ በመገኘቱ በአዋጁ አተገባበር ወቅት ክፍተት ፈጥሯል"

 

ከአዋጁ ላይ የተሻሻሉ ፍሬ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ከዛሬ ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆነው ይህ የማሻሻያ ድንጋጌ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ" የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የሚያቋቁመው "ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የሚቆየው ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ነው" የሚለውን ይዟል።ሆኖም "አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዐፈ ጉባኤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቆይታ እስከ አንድ ዓመት ድረስ እንዲራዘም ሊወስን ይችላል" በሚልም አስቀምጧል።

አቶ ጌታቸዉ ረዳ።የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርን ላለፉት ሁለት ዓመታት የመሩት አቶ ጌታቸዉ በቅርቡ በሌላ ፖለቲከኛ ይተካሉ ተብሎ ይጠበቃልምስል፦ Solomon Muchie/DW

የማሻሻያ አዋጁ በሁለት ድምጽ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ከመጽደቁ በፊት "የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እስካሁን ምን ሠራ? የሚለው ለምን ለምክር ቤት ሪፖርት አልቀረበም" የሚል ጥያቄ ቀርቦበታል።  የተሻሻለው አዋጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጊዜያዊ አሥተዳደሩን የሥራ ኹኔታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በየ ሦስት ወሩ ያቀርባል በሚል መደንገጉ ተጠቅሶ ነው ይህ ጥያቄ የቀረበው።

 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐፈ ጉባኤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራ ሪፖርት ለፌደሬሽን ምክር ቤት የሚቀርብ መሆኑን በመጥቀስ ድንጋጌው በቀጥታ ምክር ቤቱን እንደማይመለከት በመጥቀስ እንዲያም ሆኖ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ለፓርላማው ማብራሪያ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

 

ከምክር ቤት አባላት ሌላሎች ጥያቄዎችም ቀርበው ነበር።

"ተቋቁሞ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር [የትግራይ] ለምን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የተንቀሳቀሱ የአስተዳደር አካላትን፣ የወታደራዊ አካላትን ለፍርድ አላቀረበም?"

አንድ የምክር ቤት አባል ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ በሽግግር ፍትሕ ሥርዓት የሚፈታ መሆኑን ጠቅሰዋል።የምክር ቤት አባላት ከዚህ ዐዋጅ ላይ ሦስት አንቀጾችን እና አምስት ንዑስ አንቀጾችን ብቻ ከማሻሻል ለምን አጠቃላይ አዋጁ ማሻሻል እንዳላስፈለገም ጠይቀዋል። ለዚህ ምላሽ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሯ ሀና አርዓያሥላሴ አሁን አንገብጋቢው ማሻሻያ ያስፈለገው አንቀጽ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን የሥራ ጊዜ የተመለከተው መሆኑን ገልፀዋል።

አዋጁ በፌደሬሽኑ አባል ክልሎችየፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የክልሎች የሕግ አስፈፃሚዎችና የዳኝነት አካላት ችግሩን መፍታት ሲሳናቸው በክልሉ ምክር ቤት ወይም ከፍተኛው አስፈፃሚ አካል ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲከሰት እንዲሁም በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ሲኖር በፌደሬሽን ምክር ቤት ትእዛዝ የፌዴራል መንግሥቱ የክልል ምክር ቤት እና የሕግ አስፈፃሚውን በማገድ ጊዜያዊ የክልል አስተዳደር እንዲቋቋም የሚቻልበትን አሰራር ደንግጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሳምንታት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በአንድ ዓመት ሊራዘም እንደሚችል እና የአመራር ለውጥም ሊኖር እንደሚችል አስቀድመው አስታውቀው ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW