የፓስፓርት ለማግኘት እና ለማደስ ያለ ችግር በኢትዮጵያ
ዓርብ፣ ኅዳር 7 2016አዲስ ለማግኘትም ይሁን ነባር ፓስፓርት ለማደስ አመልክተው ለረጅም ጊዜ ወረፋ በመጠበቅ ላይ የሚገኙ ወደ 200 ሺህ የሚደርሱ አመልካቾች እስከ ታህሣስ መጨረሻ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት ላይ መሆኑን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ። ከፓስፓርት እድሳትም ይሁን አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በሌብነትና ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ሕዝብን ያማረሩ ያላቸውን 38 የተቋሙን ሰራተኞችን እና 15 ደላሎችን መያዙን የገለፀው ተቋሙ ሕገወጥ መታወቂያ ይዘው የሚገኙ የውጭ ዜጎች ቁጥርም በአሳሳቢ ሆኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው የፓስፖርት አገልግሎት ዜጎች በቀላሉ የማያገኙት እና ለከፍተኛ እንግልት የሚዳረጉባቸው የሥራ መስኮች ውስጥ አንደኛው ሲሆን በመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞችም ይሁን በደላሎች ከፍተኛ እጅ መንሻ እየተጠየቀ ከሚፈልገው ጉዞ ሲደናቀፍ ይታያል። ተቋሙ በከፍተኛ ወጪ ከውጪ አሳትሞ የሚያስገባውን ፓስፖርት በሀገር ውስጥ የማተም ውጥን ስለመያዙ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ገልፀዋል። ፓስፖርትን በጉቦ
ፖስፖርት ለማውጣትም ይሁን ለማሳደስ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የሚሚግሬሽን አገልግሎት ዋና ምሥሪያ ቤት ከንጋት ጀምሮ መሰለፍ አዲስ ክስተት አይደለም።
ይህንን አገልግሎት ያገኙ ሁሉ እንግልቱን፣ ረጅም ወራት ወረፋ መጠበቁን ያውቁታል። "ለስምንት ቀን ሌሊት ዘጠኝ ሠዓት ላይ እየተሰለፍኩ ዘጠንኛው ቀን ሊደበድበኝ ነበር አስተባባሪው። ብዙ እንግልት ነበረው"
ለተቋሙ በቅርቡ ተሹመው በዋና ዳይሬክተርነት እያገለገሉ ያሉት ሰላማዊት ዳዊት መሥሪያ ቤቱ በርካታ የሌብነት ኔትዎርክ ያለበት ፣ ደላሎች በስፋት በውጭም በውስጥም የተንሰራፉበት፣ በርካታ ሰዎች በዚህ ችግር ውስጥ ወድቀው የተግኙበት ስለመሆኑ ከዚህ በፊት ገልፀው ነበር። "ቀውስ" ሲሉ የጠቀሱት እና የዜጎች ፓስፓርት የማግኘት መብት ችግር አሁን በስፋት እየታተመ እየገባ ባለው ፓስፖርት እየተቃለለ መሆኑን ፣ ወረፋ እየጠበቀ ያለው ወደ ሁለት መቶ ሺህ ፓስፖርት አመልካችም እስከ ታህሳሥ መጨረሻ እንዲያገኝ ጥረት ላይ መሆናቸውን ዛሬ ተናግረዋል።
"531 ሺህ 800 የፓስፖርት ደብተሮችን ከውጭ ተመርተው ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ አድርገናል" ብዙዎች ፓስፓርት ለማውጣትም ሆነ ለማደስ በደላሎች ማታለል እንደተፈፀመባቸው፣ ሙስና በግልጽ እየተጠየቁ ፓስፓርት ተሰርቶላቸው ከሀገር የወጡ ሰዎች ስለመኖራቸው ያንን የሚያውቁ ከዚህ በፊት ገልፀውልናል።ዉይይት፣ ሙስና በኢትዮጵያ
በሌላ በኩል አሁን አሁን የውጭ ጉዞ ያላቸው ሰዎች በአየር መንገድ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ያልተገባ እንግልት እንደሚደርስባቸውና ገንዘብም እየተጠየቁ ያሉ መኖራቸው ተጠቅሶ ያውቁት እንደሆን የተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሯ እየተጣራ እርምጃ የመውሰድ ሥራ እንደሚቀጥል ገልፀዋል። እስካሁን በተደረገ ማጣራት "53 ወንጀለኞች በወንጀል እንዲጠየቁ " ስለመደረጉም አብራርተዋል። ከፓስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የገንዘብ መቀበያ ሰነድ የሚሸጡ ፣ የኢሚግሬሽንን ሰነዶች በማስመሰል እና ቅድሚያ ታገኛላችሁ በሚል ማጭበርበር መኖሩን ፣ የተቋሙን የውስጥ ሰነዶችን ወደ ውጪ ማስወጣት ኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት የለያቸው ችግሮች መሆናቸውን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገልፀዋል።አዲሱ የአፍሪቃ ፓስፖርት
አሁን በብዙ ቁጥር ታትሞ ከገባው ፓስፖርት ውስጥ ለአዲስ አበባ አምልካቾች ቅድሚያ ስለመሰጠቱ፣ 15 ሺህ ገደማ የፓስፓርት አገልግሎት ጠያቂዎች ሰነዳቸው ታትሞ መጥቶ እንዲወስዱ ቢነገራቸውም እስካሁን ሄደው እንዳልወሰዱ፣ 122 ሀገራት የ "on arival" የሚባለው የቪዛ አሰጣጥ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ክፍት ስለመደረጉ ፣ 560 ሀሰተኛ ሰነድ የያዙ እና ከሀገር እንዳይወጡ እግድ ያለባቸው የትባሉ ሰዎች ጭምር ሊሸሹ ሲሉ በድንበር በኩል ስለመያዛቸውም በዛሬው መግለጫ ተነግሯል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ