1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓን አፍሪካ ክፍያ ሥርዓት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የኢትዮጵያን አባልነት ይጠባበቃሉ

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 14 2016

የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ኬንያ እና ጅቡቲን ጨምሮ አስር ሀገሮች የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓትን ተቀላቅለዋል። ይኸ የክፍያ ሥርዓት አፍሪካን በዓመት ከ5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊያድናት ይችላል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማይክ ኦግባሉ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ከተገናኙ በኋላ ኢትዮጵያ ሥርዓቱን እንድትቀላቀል ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Eshete Bekele/DW

የፓን አፍሪካ ክፍያ ሥርዓት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የኢትዮጵያን አባልነት ይጠባበቃሉ

This browser does not support the audio element.

ናይጄሪያዊው ማይክ ኦግባሉ ባለፈው ሣምንት ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ጋር ከተገናኙ በኋላ ለፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት ኢትዮጵያ የምትፈጥረውን “ከፍተኛ የኔትወርክ መስፋፋት” ዕድል እየተጠባበቁ ነው። ኦግባሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በሚመሩት አኅጉራዊ የክፍያ ሥርዓት የኢትዮጵያ መካተት “በምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እና እድገት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል” የሚል እምነት አላቸው።

ማይክ ኦግባሉ የአፍሪካ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና ጽህፈት ቤት፣ የአፍሪካ የወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ (African Export-Import Bank) እና የአፍሪካ ኅብረት በጥር 2015 በይፋ ሥራ ላይ ያዋሉት የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። ይኸ የክፍያ ሥርዓት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና የጀርባ አጥንት ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ኦግባሉ “ቀልጣፋ እና ዝቅተኛ ድንበር ተሻጋሪ የክፍያ ሥርዓት በማመቻቸት የአፍሪካን የንግድ እና የኤኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ ያለመ” ያሉትን የክፍያ ሥርዓት ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ላቅ ያለ ፍላጎት እንዳላቸው ሊንክድኢን በተባለ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቁመዋል። የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓትን አቶ ብዙነህ በቀለ የኢትዮጵያ ባንኮችን ከሚያቀናጀው እና በሚያዝያ 2008 ሥራ ከጀመረው ኢትስዊች ጋር ያመሳስሉታል። የዲጂ ፋይናንስ አፍሪካ መሥራች የሆኑት አቶ ብዙነህ ዘመናዊ የባንክ እና የክፍያ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት በኢትዮጵያ ባንኮች የተቋቋመው ኢትስዊች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመነገድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደረሰች

የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማይክ ኦግባሉ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ጋር ከተወያዩ በኋላ ኢትዮጵያ አኅጉራዊውን የክፍያ ሥርዓት ብትቀላቀል ከተሳለጠ የድንበር ተሻጋሪ ግብይት እና ዝቅተኛ የግብይት ወጪ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል ገልጸዋልምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

“በኢትዮጵያ ኢትስዊች ሁሉንም ባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አገናኝቶ ክፍያ ከአንድ ከፋይ በሌላ ተቋም ለሚጠቀም ወደሌላ ተከፋይ እንዲከፈል ያደርጋል። ልክ እንደዚሁ የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረጉ የንግድ እና ከንግድ ጋር የተያያዙ ክፍያዎችን ለማከናወን የinteroperability platform ነው” ሲሉ አቶ ብዙነህ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። 

የዚህ የክፍያ ሥርዓት አቀንቃኞች በድንበር ተሻጋሪ ግብይት ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን አዎንታዊ አስተዋጽዖ እየጠቀሱ “አብዮታዊ” እያሉ ያሞካሹታል። ይኸ የክፍያ ሥርዓት ዶላር ላይ ጥገኛ ሆኗል የሚባለውን የአፍሪካ የርስ በርስ ግብይት ነጻ ሊያወጣ ይችላል የሚል ተስፋም አለ።

“ዋናው ሥራው በሀገሮች መካከል ተናባቢ የክፍያ ሥርዓት መፍጠር እና የገንዘብ ዝውውሮቹን ማስተላለፍ ነው” የሚሉት አቶ ብዙነህ የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት የአፍሪካ ነጋዴዎች ዶላር፣ ዩሮ፣ ፓውንድ ወይም የንን የመሳሰሉ የውጭ ምንዛሪ ሳያስፈልጋቸው በሀገራቸው የመገበያያ ገንዘብ ክፍያ እንዲፈጽሙ ዕድል እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት በጥር 2015 ሥራ ላይ የዋለው መቀመጫውን በግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ባደረገው የአፍሪካ ወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ እና በአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ትብብር ነው። ምስል Afrexim-Bank

የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት ለአፍሪካ ነጋዴዎች እና ኩባንያዎች ውስብስቡን የገንዘብ ዝውውር ለማቅለል እና ወጪውን ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ለዚህ ደግሞ በአፍሪካውያን ግብይት ከፍ ያለ ትርፍ የሚያጋብሱ ወኪል ባንኮችን ማስወገድ ያስፈልገዋል።

አሁን ዓለም በሚከተለው አሠራር “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስመጪ ጋና ካለ አንድ ላኪ ልግዛ ቢል ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ባንክ በኩል በቀጥታ ጋና ላለው ላኪ ባንክ አይደለም የሚከፍለው። ይኸንን ማድረግ አይችልም። ምክንያቱም የአፍሪካ ባንኮች በወኪል ባንኮች (correspondent banks) አማካኝነት መሔድ አለባቸው” ሲሉ አቶ ብዙነህ ተናግረዋል።

የአሜሪካኖቹ ዌልስ ፋርጎ እና ሲቲ ባንክ፣ የስዊትዘርላንዱ ኤችኤስቢሲ፣ የጀርመኑ ዶይቼ ባንክ፣ ከብሪታኒያ ስታንዳርድ ቻርተርድ እና ባርክሌይስ ባንኮች በዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ በውክልና የባንክ ሥራ ላይ የተሰማሩ መካከል ናቸው።

እነዚህ በውክልና ሥራ የተሰማሩ ተቋማት በላኪ እና ተቀባይ ባንኮች መካከል ለሚሰሩት ገንዘብ የማቀባበል ሥራ ጠቀም ያለ የአገልግሎት ክፍያ ይጠይቃሉ። በአፍሪካ የወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ መረጃ መሠረት በወኪል ባንኮች በኩል ለሚከወን የንግድ ግብይት እና የገንዘብ ዝውውር አፍሪካ በየዓመቱ 5 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች።

የአፍሪካውያን የንግድ ግብይት ክፍያ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚፈጸመው የስዊትዘርላንዱ ኤችኤስቢሲ እና የጀርመኑ ዶይቼ ባንክ በመሳሰሉ ተቋማት በኩል ነው። በአፍሪካ የወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ መረጃ መሠረት በወኪል ባንኮች በኩል ለሚከወን የንግድ ግብይት እና የገንዘብ ዝውውር አፍሪካ በየዓመቱ 5 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች።ምስል Toby Melville/REUTERS

በዚህ አሰራር “የክፍያ ሥርዓቱ ዓለም አቀፍ ባንኮች ጋ በሚሔድበት ጊዜ የገንዘብ ዝውውሩ ከአፍሪካ ወጥቶ በሌሎች ሀገር process ተደርጎ ነው ተመልሶ የሚመጣው። እዚያ ያለው የprocessing cost፣ ለሲስተም እና ለአገልግሎት የሚከፈለው ክፍያዎች በሙሉ አፍሪካዎች በራሳቸው በሚሻሻጡት የዕቃ እና የአገልግሎት ዋጋ ላይ ይደመራል” የሚሉት አቶ ብዙነህ “ይኸ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን የርስ በርስ ንግድ ውድ ያደርገዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ይኸ አፍሪካውያን በገዛ ገንዘባቸው ድንበር ተሻግረው እንዲገበያዩ የሚደረግ ጥረት በበርካታ የአኅጉሪቱ ፖለቲከኞች ይሁንታ ቢያገኝም እንዲህ በቀላሉ የሚተገበር ግን አይመስልም። በሕጋዊው ሥርዓት የኢትዮጵያ ብር በሶማሊያ ዋጋ የለውም። የኤርትራ ናቅፋ በሱዳን ገበያ ዕቃ አይገዛም። አርባ ሁለት የመገበያያ ገንዘቦች ያሏት አኅጉር አንዱን ወደ ሌላው የምትመነዝርበት መደበኛ ስልትም አላበጀችም። የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማይክ ኦግባሉ የጀመሩት ጥረት ስኬታማ መሆን ይችል ዘንድ ለእንዲህ አይነት ችግሮች መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።

ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ወደ ውጭ አገራት መላክ የሚጨምረው የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ፈጠራ ዕቅድ

አቶ ብዙነህ “የባንክ አሠራሮችን ለማጣጣም መሠራት ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ የመገበያያ ገንዘቦቻችን ከአንዱ ወደ ሌላው የሚመነዘሩ አይደሉም። እሱን ለማለፍ የሚኬድባቸው መንገዶች እንኳን ምን አልባት በቀጥታ የእኛ መገበያያ ገንዘቦች እርስ በርሳቸው የሚመነዘሩበት ሁኔታ አሁኑኑ ላይኖር ይችላል” ሲሉ የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት የሚገጥሙትን ፈተናዎች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓትን ብቀላቀል ከብሔራዊ ባንክ በተጨማሪ የመንግሥት እና የግል ባንኮች እና እንደ ኢትስዊች ያሉ ተቋማት ሊሳተፉ ይችላሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የሆኑት ኬንያ እና ጅቡቲን ጨምሮ አስር ሀገሮች የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት አባል ናቸው። የአፍሪካ ሀገሮች በእርስ በርስ የንግድ ግብይታቸው ከዶላር ጥገኝነት ሊላቀቁ ይገባል የሚል ብርቱ አቋም ያላቸው የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ሀገር ኬንያ የክፍያ ሥርዓቱን በይፋ የተቀላቀለችው በመስከረም 2016 ነው።

የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማይክ ኦግባሉ ኢትዮጵያ የጅቡቲ እና የኬንያን መንገድ በመከተል አባል ብትሆን ከተሳለጠ የድንበር ተሻጋሪ ግብይት እና ዝቅተኛ የግብይት ወጪ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል ገልጸዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሊንክድኢን በተባለው ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት አባል ብትሆን ቀጠናዊ መዋዕለ-ንዋይ ልታገኝ፤ ከሌሎች አገሮች ጋር ትብብርን ልታበረታታ ትችላለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ሆነ ገዥው ማሞ ምኅረቱ በጉዳዩ ላይ እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም። ዶይቼ ቬለ ከባለሥልጣናቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሀገሪቱ “ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ” ከቻይና የፋይናንስ ተቋማት እንዲደራደር መወሰኑን አቶ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ

“ይኸ ለአፍሪካም አዲስ ጅምር ነው። ሒደቱ ቀስ በቀስ ነው መሔድ ያለበት” የሚሉት አቶ ብዙነህ ግን “ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ያሉ ከመገበያያ ገንዘብ፣ ከቁጥጥር ጋር ያሉ ጉዳዮች በጣም በጥንቃቄ [መያዝ አለባቸው።] ይኸ ነገር በሚመጣበት ጊዜ እንዴት መቆጣጠር እንችላለን? የሚለው ነገር ዝግጅት ሊያስፈልገው ይችላል” ሲሉ ይመክራሉ።

በፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት አተገባበር የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች የተሻለ መራመዳቸውን የሚጠቅሱት አቶ ብዙነህ “ብሔራዊ ባንኮቻቸው የተለያዩ መመሪያዎች አዘጋጅተዋል። ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ምን ምን ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው? ምን ዓይነት ጥንቃቄዎች ማድረግ ያስፈልጋል? ምን ዓይነት ነገሮች ላይ ደፍረን መግባት ይኖርብናል? የሚለውን” መማር እንደሚኖርባት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወደ ፓን አፍሪካ የክፍያ ሥርዓት “መግባት አስፈላጊ ነው። ይኸ ምንም ጥርጥር የለውም” የሚሉት አቶ ብዙነህ በቂ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW