1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) አጠቃቀም ሕግ እና ሥጋቶቹ

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2018

ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ወይም "ፌስታል" መጠቀምን፣ ማምረትን እና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን የሚከለክለው ሕግ የሰጠው የዝግጅት ጊዜ ሊያበቃ አንድ ወር ቀርቶታል። ሕጉ ምርቶቹ የሚያደርሱትን የጤና፣ የአካባቢ ብክለት፣ የንጽሕና እና ተያያዥ ችግሮች ለማስቀረት በሚል ምክንያት የተደነገገ ነው።

Äthiopien Plastiktüten
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ለፕላስቲክ ከረጢት ምርቶች የወጣው ህግ እና ያስከተለው ስጋት እና አንድምታው

This browser does not support the audio element.

የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) አጠቃቀም ሕግ እና ሥጋቶቹ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ወይም "ፌስታል" መጠቀምን፣ ማምረትን እና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን የሚከለክለው ሕግ የሰጠው የዝግጅት ጊዜ ሊያበቃ አንድ ወር ቀርቶታል።

ሐምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም የጸደቀው አዋጅ ምርቶቹ የሚያደርሱትን የጤና፣ የአካባቢ ብክለት፣ የንጽሕና እና ተያያዥ ችግሮች ለማስቀረት በሚል ምክንያት የተደነገገ ነው።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ያስቀመጠው የስድስት ወራት የሽግግር ጊዜ በመጪው ጥር 23 ይጠናቀቃል። በዘርፉ የተሰማሩ የፕላስቲክ አምራቾች ማህበር ግን ይህ ጉዳይ አሁንም ዳግም እንዲጤን እየጠየቀ ነው።

ሐምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው "ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶች ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ" የሚከለክለው አዋጅ የፕላስቲክ ከረጢትወይም "ፌስታል" የሚባሉ የፋብሪካ ምርቶችን መጠቀምን፣ ማምረትን" ጭምር የሚከለክል ነው።

እነዚህን ምርቶች የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ የተገኘን ማንኛውንም ሰው ለገንዘብ ቅጣት የሚዳርገው ይህ ሕግ የኢትዮጵያን የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ክምችት፣ መልሶ አጠቃቀም እና አወጋገድን ሥርዓት የማስያዝ ዓላማ ያለው መሆኑ ተጠቅሶ ነው የቅጣት ድንጋጌዎችን ያካተተው።

ሕጉ የፕላስቲክ ምርቶች የሚያደርሱትን ዘርፈ ብዙ የአካባቢ ብክለት፣ የንጽሕ፣ የጤና እና ተያያዥ ችግሮች ለማስቀረት ያለመ ነውም ተብሎለታል።

ሕጉን የማጽፈፀም ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከመጪው ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እነዚህን የተከለከሉ ምርቶች ይዘው የሚገኙ ሰዎች ላይ ቅጣት እንደሚጀምር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የፕላስቲክ ከረጢት የሚሰጠው አገልግሎት

ኢትዮጵያ ውስጥ ከከተሞች እስከ የገጠር መንደሮች፣ ከአነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች እስከ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት የፕላስቲክ ከረጢት የሌለበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል። በሁሉም ስፍራ ይገኛል። የምግብም ይሁን የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስም ይሁን አነስተኛ መጠን ያላቸው የእህል እና የግብርና ምርቶች ግብይቶች ያለ ፕላስቲክ ከረጢት ወይም ፌስታል የሚሆንም አይደለም።

አቶ በረከት ገብረሕይወት የኢትዮጵያ ፕላስቲክና ጎማ አምራቾች ማኅበር አባልና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅን በተመለከተ የተቋቋመ ኮሚቴ አስተባባሪ ናቸው። እሳቸው እንደነገሩን ስስ የፕላስቲክ ምርቶች ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያገበያ እና ግብይት ውስጥ ሰፊ ቦታ አላቸው። ምርቶቹም "ከሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር በጣም የተቆራኙ" ናቸው።

ትዮጵያ ውስጥ ከከተሞች እስከ የገጠር መንደሮች፣ ከአነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች እስከ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት የፕላስቲክ ከረጢት የሌለበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ደረጃቸውን ጠብቀው የሚመረቱት መታገዳቸው አግባብ አይደለም

በአዋጁ እንደተጠቀሰውም ሆነ በተግባር እንደሚታየው የፕላስቲክ ምርቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው እና ጥቅማቸው አብቅቶ ወደ ቆሻሻነት ሲቀየሩ በመሬት እና አፈር ላይ፣ በአካባቢ እንዲሁም በጤና ላይ ችግሮችን ይዘው ይመጣሉ። ለረጅም ዓመታት ከአፈር ጋር ተዋህደው ወደ ብስባሽነት የማይለወጡ መሆኑ ቀዳሚው ጉዳት ስለመሆኑ ይጠቀሳል። ይህም የመሬትን ምርታማነት ያሳጣል። በዚህም እርሻን ያውካሉ፣ የአትክልትና እጽዋትን ዕድገትም ይገታሉ። 

በየመንገድ ስርቻው ተጥለው የሚታዩ የፕላስቲክ ኮዳዎች ብዙ ናቸው። ከየቤቱ ከሚወጡ ደረቅ ቆሻሻዎችመካከል አብዛኛዎቹ ፕላስቲክ ነክ ቁሶች ናቸው። የውኃ መፋሰሻዎች እና ቱቦዎች በሚያስጨንቅ ኹኔታ በፕላስቲክ ቆሻሻዎች መደፈንና መዘጋት ይገጥማቸዋል። አቶ በረከት ገብረሕይወት እንደሚሉት ግን እገዳው በጥራት የሚመረቱትንም ያጃመለ መሆን የለበትም።

ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው እንደ ሀገር ከሚወገደው የቆሻሻ ክምችት ከ200 እስከ 250 ሺህ ቶን የሚገመተው የፕላስቲክ ተረፈ ምርት ነው። ይህም ምርቶቹ እያሳደሩት ያለውን ተጽዕኖ አስከፊ እንዳደረገው ታምኖበታል። አቶ በረከት ገብረሕይወት ግን በሚመርተው የፕላስቲክ ውጤት ምክንያት ይደርስ የነበረን የጤና በካይነት እየቀረፍን መጥተናል ሲሎ፣ አልፎም ዘርፉም የማይናቅ የዕድገት ድርሻ ያለው መሆኑን በመዘርዘር ሕጉ አሁንም ቢሆን እንደገና ይታያል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

ለሕጉ መውጣት ልምድ የተወሰደባቸው ሀገራት ተገቢነት

የፕላስቲክ ከረጢቶች ኬንያን በመሰሉ ጎረቤት ሀገራት በጠንካራ ካኪ ወረቀቶች እና በጨርቅ በሚዘጋጁ ምርቶች  ተክተዋል። የኢትዮጵያ ፕላስቲክና ጎማ አምራቾች ማኅበር አባልና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅን በተመለከተ የተቋቋመ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ በረከት ገብረሕይወት ዛሬ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ልምድ ወሰደችባቸው የተባሉ ሩዋንዳን የመሰሉ ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የፕላስቲክ አጠቃቀም ትክክለኛ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም።

የፕላስቲክ ከረጢቶች ኬንያን በመሰሉ ጎረቤት ሀገራት በጠንካራ ካኪ ወረቀቶች እና በጨርቅ በሚዘጋጁ ምርቶች  ተክተዋል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የፕላስቲክ ከረጢት አምራች የነበሩ ባለሃብቶች የቀጣይ ዕጣ ምን ይሆን?

አምራቾቹ ሌላው እያነሱት ያለው መከራከሪያ አንድ የሥራ መስክ ወደ ሌላ ኹኔታ ይቀየር ሲባል ለባለሃብቱ ከሦስት እስከ አራት ዓመት የሚወስድ በቂ የመሸጋገሪያ ጊዜ ሊሰጥ ይገባ ነበር የሚለው ነው። ይህ አለመሆኑ ባለሃብቶች በፋብሪካዎቻቸው ያቀፏቸውን ሰራተኞች የሥራ ዋስትና ያሳጣል፣ ይህም ለከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አለፍ ሲልም ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሊዳርግ ስለሚችል ከዕገዳ በመለስ ያለው አማራጭ ይታይ የሚል መከራከሪያ አስነስቷል።

ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢትን የመጠቀሚያ ጊዜ ድንገት ከመቆሙ በፊት ሕጉ ሐምሌ 2017 ቢፀድቅም ስድስት ወራት የሽግግር ጊዜ የተሰጠ ሲሆን ጊዜው ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያበቃ ለመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያስታወቀው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንከዚያ ዕለት በኋላ የፕላስቲክ ከረጢት ወይም "ፌስታል" የሚቀምን፣ የሚያመርትን እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባን አካል መቅጣት እንደሚጀምር አስታውቋል።

ጥያቄው ግን እንዴት እና በምን መልኩ? የሚለው ነው። የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ አቡኔ ከማለዳ ጀምሮ ማብራሪያ እንዱሰጡን ደጋግመን ጠይቀናቸው ነበር። ስብሰባ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ መልሰው እንደሚያገኙን የገለፁ ቢሆንም እስከ አመሻሹ ድረስ መልሰን ልናገኛቸው ባለመቻላችን የተቋሙን ምላሽ ማካተት አልቻልንም።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW