1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የፕላስቲክ ፌስታል ይዘው በተገኙት ላይ ከፍተኛ ቅጣት የሚጥለው አዋጅ አንድምታ

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2017

ተለያዩ የሸቀጥ እቃዎች መጠቅለያነት የሚውለውን ማንኛውንም አይነት ፌስታል ይዞ መገኘት ከሁለት እስከ አምስት ሺህ ብር የሚያስቀጣው አዋጅ፤ ዜጎች በቂ ግንዛቤ ባልያዙበት ጉዳይ ለቅጣት የሚዳርግ ነው በሚል እየተተቸ ነው፡፡

Äthiopien Plastiktüten
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የፕላስቲክ ፌስታል ይዘው በተገኙት ላይ ከፍተኛ ቅጣት የሚጥለው አዋጅ አንድምታ

This browser does not support the audio element.

 

ለተለያዩ የሸቀጥ እቃዎች መጠቅለያነት የሚውለውን ማንኛውንም አይነት ፌስታል ይዞ መገኘት ከሁለት እስከ አምስት ሺህ ብር የሚያስቀጣው አዋጅ፤ ዜጎች በቂ ግንዛቤ ባልያዙበት ጉዳይ ለቅጣት የሚዳርግ ነው በሚል እየተተቸ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ33ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ ከሰሞኑ ያጸደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅማንኛውም ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ ከተገኝ ከ2-5 ሺህ ብር እንዲቀጣ ይደነግጋል፡፡

ያመረተ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ለገበያ ያቀረበ ወይም የሸጠ፣ ለንግድ ዓላማ ያከማቸ ወይም ይዞ የተገኘ ደግሞ ከ50 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር ባለው የገንዘብ መቀጮ እና ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንዲቀጣም አዋጁ አስቀምጧል፡፡ባለሙያዎች ግን አስቀድሞ የግንዛቤ ስራዎች ላይ በስፋት መስራት እና ተተኪ አገልግሎት የሚሰጡ ምርቶችን ማቅረብ ላይ መስራት ይገባል ባይ ናቸው ፡፡በውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኩል ለምክር ቤቱ የቀረበው የአዋጁ ይዘት ከተብራራ በኋላ በምክር ቤቱ አባላት ሙሉ ድምጽ ነው የፀደቀው፡፡ 

የህጉ መጽደቅ መልካም ጎኑ ይበዛል በሚል አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአከባቢ ጥበቃ ፕሮፈሰር ተሾመ ሶሮምሳ የወጡትን ህግጋት ግን ወደ ተግባር ማስገባት ትኩረት ልሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ "ህጉ ትሩ ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ተሾመ፤ እንደ ሩዋንዳ ያሉትን አገራት ከአፍሪካ እንዲሁም እንደ ቬይና እና ኒውዮርክ ያሉ አገራትን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ለ1000 ዓመታት እንኳ የማይበሰብሰው የፕላስቲክ ከሬጢቶች በአከባቢ ላይ የሚያደርሱትን ብክለት አብራርተዋል፡፡

በአዲሱ አጅ ለተለያዩ የሸቀጥ እቃዎች መጠቅለያነት የሚውለውን ማንኛውንም አይነት ፌስታል ይዞ መገኘት ከሁለት እስከ አምስት ሺህ ብር ያስቀጣል,ምስል፦ Solomon Muchie/DW

አሁን በፕላስቲክ ከረጢቶች ክልከላ ላይ የወጣውን ህግ አግባብነት እና ህጉን ተከትሎ የተጣሉ ቅጣቶች መኖራቸውም አግባብነቱ እንደሚጎላ በመግለጽ በአሁናዊ ሁኔታ በአዲሱ ረቂቅ የተቀመጠ የመቀጮ ገንዘብ ግን የተጋነነ ሳይሆን እንዳልቀረ አንሰርተዋል፡፡ "በዚህ በእኛ ህግ የፀደቀው ይዞ የተገኘ ሰው ላይ ከሁለት-አምስት ሺህ የሚል ነውና ቅጣቱ ትንሽ ልበዛ የሚችል ይመስለኛል” በማለትም አሁን ህጉ ከጸደቀ በኋላ ህጉን ወደ ተግባር በመክተት ህብረተሰቡን ከማማረር አስቀድሞ በግንዛቤ ላይ ሰፊ ስራ መስራት ብሎም ለዚህ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

የፕላስቲክ ከረጢቶች ለአከባቢ ጥበቃ ጠንቅ መሆናቸው ግልጽ ነው በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በፊናቸው፤ አንዳንድ የቆዩ ልማዶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ልነሱ የማይችሉበት እድል በመኖሩ የህጉ አላማ ህብረተሰቡን በመቅጣት ገቢን ከማሰባሰብ ይልቅ ተኪ ምርቶችን በማቅረብ ግንዛቤ መስጠቱ ላይ ልያተኩር ይገባል ባይ ናቸው፡፡ "እንዲህ ያለ ህግ ሊወጣ ነው

ከሚል ጀምሮ አስቀድሞ ግንዛቤ በሰፊው ሊያስጨብጥ ይገባል” የሚሉት ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ የቅጣት መጠኑም ደሃ የሚባል ማህበረሰብ በሚበዛበት ሀገር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ብሎም የህጉ አላማ በመቅጣት ገቢን ከማሰባሰብ ይልቅ ተኪ ምርቶችን በማቅረብ እና ግንዛቤን በማስቸበጥ ላይ ማተኮር ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ሥም ጌቱ

ሽዋዬ ለገሠ

ፀሀይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW