1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሪቶሪያዉ ስምምነትና የሰላሙ ፅናት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 23 2015

ሰሜን ኢትዮጵያን ያወደመዉ ጦርነትም የተለየ አልነበረም።የአንድ ሐገር ዉልዶች፣የአንድ ገዢ ፓርቲ አባላት፣የአንድ መንግስት አለቃ ምንዝር የነበሩት ፖለቲከኞች ስልጣን ለመነጣጠቅ ያበቀሉት ጠብ ሕዳር 3 2020፣( ከዚሕ በኋላ ያለዉ ዘመን በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዉጊያ ጭሮ ብዙዎች እንደገመቱት ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሰ ሕይወት አጥፍቷል

 Ethiopia I  “Enough With War - Let’s Celebrate Peace” in Addis Ababa
ምስል Office of Prime Minister of Ethiopia

የሰላም ስምምነቱና ሰላም

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግስት «የወዳጅነት አደባባይ» ያለዉ የአዲስ አበባ ሜዳ በወዲያኛዉ ሳምንት ዕሁድ ሚያዚያ (15፣2015) የሰላም አስፈላጊነት፣የኢትዮጵያዉያን አንድነት፣ ለአፍሪቃም አብነት መሆናቸዉ ተመሰከረበት።የቀድሞዉ የኬንያ ፕሬዝደንትና የአፍሪቃ ሕብረት የአደራዳሪዎች ቡድን አባል ኡሁሩ ኬንያታ አንዱ ነበሩ።

«ኢትዮጵያ፣ የተለያዩ ብሔሮችና ማሕበረሰቦች በሰላም በአንድ ባንዲራ ጥላ ስር እንዴት መኖር እንደሚችሉ ለአፍሪቃ አሐጉር ያሳየች ሐገር ናት።ዛሬም እንደምናየዉ ያንን የመሪነት ሥፍራ በድጋሚ ማሳየትን መርጣችኋል።»

በሳምንቱ ዕሁድ የወዳጅነት አደባባይ በጥይት ተደብድበዉ የተገደሉት የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ከፍተኛ ፖለቲከኛ የግርማ የሺጥላ አስከሬን ተሸኘበት።የፌስታ ሳምንት ሙሾ።ለምን?

የፕሪቶሪያዉ የሰላም ስምምነት የተፈረመበት 6ኛ ወር መነሻ፣ገቢራዊነቱ ማጣቃሻ፣ የኢትዮጵያ ሰላም እንዴትነት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ኢትዮጵያዊዉ የሕግ ባለሙያና የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅ ወያ እንደሚሉት የሰዎች በተለይ የሚተዋወቁ ወገኖች ልዩነት፣ ጠብና ጥላቻ ንሮ የመጀመሪያዋ ጥይት ከተተኮሶች በኋላ ሰዉ፣ እንደ ሰዉ የሚያስተሳስረዉ ነገር በሙሉ ይጠፋል።

የክልል መሪዎችና የከተማ ከንቲባዎች መቀሌን ሲጎበኙምስል Million Hailesilassie/DW

«የርስበርስ ጦርነት ሲጀመር ሰዎች ይኸ ወዳጅነት፣አብሮ ማደግ፣ አንዱ ለሌዉ አበልጅ ሆኖ የክርስትና አባት፣የክርስትና ልጅ ምናምን የምትለዉ ከመጀመሪያዉ ጥይት በኋላ ይጠፋል።ጠላትነት ብቻ እየጎላ ይመጣል።ስለዚሕ ጎረቤትሕን፣ የድሮ አበልጁሕን የምታዉቀዉን ሚዜ የሆንክለትን ሰዉ መግደል በጣም ይቀላል።---»

ሰሜን ኢትዮጵያን ያወደመዉ ጦርነትም የተለየ አልነበረም።የአንድ ሐገር ዉልዶች፣ የአንድ ገዢ ፓርቲ አባላት፣የአንድ መንግስት አለቃ ምንዝር የነበሩት ፖለቲከኞች ስልጣን ለመነጣጠቅ ያበቀሉት ጠብ ሕዳር 3 2020፣( ከዚሕ በኋላ ያለዉ ዘመን በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዉጊያ ጭሮ  ብዙዎች እንደገመቱት ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሰ ሕይወት አጥፍቷል።

አካሉ የጎደለዉን፣ የተደፈረ፣ ስብዕናዉ የተዋረደዉን በትክክል የቆጠረዉ የለም።ጦርነቱ በተደረገባቸዉ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የኃይማኖት ተቋማት፣የመሰረተ ልማት አዉታሮች፣ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።

አስከፊዉ ጦርነት እንዲቆም ያደራደሩና የተደራደሩ ወገኖች በተሸለሙበት ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን እንደመሰከሩት የጦርነቱ ጥፋት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ጦርነቱ የተጀመረበት ሁለተኛ ዓመት ሊዘከር ሳምንታት ሲቀሩት የታተመ አንድ የካናዳ ጋዜጣ እንደዘገበዉ በዚያን ወቅት በመላዉ ዓለም ይደረጉ ከነበሩ ግጭትና ጦርነቶች ሁሉ በርካታ ሕይወትና ሐብት በማጥፋት የሰሜን ኢትዮጵያዉን ጦርነት የሚስተካከል አልተገኘም።

ኦሌሼጎን አባሳንጆ ሲሸለሙምስል Office of Prime Minister of Ethiopia

በሰዉ ልጅ ጥንታዊ መኖሪያነት፣ የአዉሮጳ ቅኝ ገዚዎችን በማሸነፍ፣ በረጅም ርቀት ሩጫ  ዓለምን በጣሙን አፍሪቃን የምትመራዉ ሐገር በድርቅና ረሐብ በሚያልቅና በሚሰቃይ ሕዝብ የዓለም አንደኛ ከሆነች ዓመታት ተቆጥረዋል።አምናና ሐቻምና ደግሞ ባጭር ጊዜ የርስበርስ ጦርነት ብዙ መቶ ሺዎችን በማስጨረስ ከዓለም አንደኝቷን አስመስክራለች።የአዲስ አበባና የመቀሌ ገዢዎች ጦርነቱን ሆን ብለዉ የጎሳ ወይም የብሔር መልክና ባሕሪ ስለሰጡት በተለያዩ ጎሳ ተወላጆች መካከል ባጭር ጊዜ የማይታረቅ ቅራኔ ፈጥረዋል።በገንዘብ፣በዲፕሎማሲ፣በፖለቲካና ጦር ኃይል በዓለም ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፍ የሚችሉ የአረብና የዓለም ኃይላን  መንግስታት ከተፋላሚ ኃይላት አንዱን ወይም ሌለኛዉን እስከመደገፍ ደርሰዋልም።

ተፋላሚ ኃይላት ዉጊያዉን አቁመዉ እንዲደራደሩ ኢጋድ፣የአፍሪቃ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣የአዉሮጳ ሕብረት በተደጋጋሚ ጠይቀዉ ነበር።

በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ የምትደግፈዉ  ኃይል የበላይነቱን እንዲይዝ ከመፈለግ ይሁን-አይሁን በዉል ባይታወቅም ካንዴም ሁለቴ የሰየመቻቸዉ ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ መቀሌ ተመላልሰዋል።

የአፍሪቃ ሕብረት ነሐሴ 2021 በልዩ መልዕክተኝነት የሰየማቸዉ የቀድሞዉ የናጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሌሼጎን አባሳንጆ ከተፋላሚዎቹ ኃይላት በተጨማሪ የአፍሪቃ፣የአዉሮጳና የዩናይትድ ስቴትስን ባለስልጣናትን ለማነጋገር ከፕሪቶሪያ-ፓሪስ፣ ከብራስልስ ዋሽግተን ተመላልሰዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምሕርና የፖለቲካ ተንታኝ ሙከረም ሚፍታሕ በቅርቡ እንዳሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ጦርና ተባባሪዎቹ  በዉጊያዉ አዉድ የበላይነታቸዉን እስከሚያረጋግጡ ድረስ የነበረዉ የሰላም ጥረት ያስገኘዉ ዉጤት አልነበረም።

ሕዳር 21፣ 2021 ጦርነቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት አለፈዉ።የዚያን ቀን የተሰየመዉ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ከዓለም ከፍተኛ ጥፋት ከሚያደርሰዉ ጦርነት በላይ ቅድሚያ የሰጠዉ ርዕስ አልነበረም።

የአፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሼጎን አባሳንጆ ከአዲስ አበባ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ዘገባ ለሰላማዊ ድርድር «የዕድል መስኮት» ያሉት ተስፋ መኖሩን ጠቆሙ።

«እዚሕ አዲስ አበባ ያሉትና ሰሜን ያሉት ሁለቱም መሪዎች  ልዩነታቸዉ ፖለቲካዊ መሆኑን ፣መፍትሔም በድርድር የሚደረስበት ፖለቲካዊ እንደሆነ  በተናጥል ተስማምተዋል። ይሕ ለቀጠለዉ ቀዉስ ዘላቂ መፍትሔ በመፈለግ የኢትዮጵያ ሕዝብን ለመርዳት ሁላችንም በጋራ ልንጠቀምበት የሚገባ የእድል መስኮት ይከፍታል።ይሁንና ያለን የዕድል መስኮት በጣም ትንሽ፣ ጊዜዉም አጭር መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።»

ከጦርነቱ ጥፋቶች አንዱምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የኦባሳንጆ ተስፋ፣ ጥሪና ማስጠንቀቂያ ከተሰማ አንድ ወር ደፈነ።የሰላም መስኮቱ ግን አዛዉንቱ ፖለቲከኛ እንዳሉት እንደ ጠበበ ነዉ።ታሕሳስ 20፣ 2021 የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ጦር፣የአማራና የአፋር ልዩ ልዩ ኃይላት በሕወሓት ጠላታቸዉ ላይ መጠነ ሰፊ አፀፋ ጥቃት ከፈቱ።

ከአዲስ አበባ በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የነበረዉን ሕወሓት ወይም የትግራይ ኃይሎችን ጦር ምሽጎች እየሰባበሩ የአፋርና የአማራ ክልል ስልታዊ ቦታዎችን ባጭር ጊዜ ተቆጣጠሩ።አብዛኛዉ የሕወሓት ጦር ባንጻሩ  ወደ  ትግራይ ክልል አፈገፈገ።

የመንግስት ጦርና የተባባሪዎቹ  አፀፋ ጥቃት እያየለ ሲሔድ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጻፉት ደብዳቤ የሚቆይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቁ።

መጋቢት 24፣ 2022 የኢትዮጵያ መንግስት «ለሰብባአዊነት» ያለዉን የተናጥል ተኩስ አቁም አወጀ።ተኩስ አቁም በሕወሓት በኩልም ተቀባይነት በማግኘቱ እስከ ነሐሴ ድረስ ፀና።ከመጋቢት እስከ ነሐሴ በነበረዉ ጊዜ ሁለቱ ወገኖች ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸዉን በየፊናቸዉ አስታዉቀዉ ነበር።

ይሁንና በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከሚነገረዉ የድርድር፣የፖለቲካ ሸብረብ  ጀርባ የሁለቱ ወገኖች ጦር በየፊናዉ ሲዘጋጅ ቆይቶ ነሐሴ ላይ ከፍተኛ ዉጊያ ገጠሙ።የኢትዮጵያ መከላከያ ጦርና ተባባሪዎቹ ከደቡብ፣የኤርትራ ጦር ከሰሜን አቃርጠዉ የያዙት የሕወሓት ጦር፣ ከነሐሴ ማብቂያ እስከ ጥቅምት ማብቂያ በነበሩት ወራት ሽረንና ሌሎች የትግራይ ትላልቅ  ከተሞችንና አካባቢዎች ለጠላቶቹ እየለቀቀ ለመዉጣት ተገደደ።

ጥቅምት ማብቂያ 2022 ለአዲስ አበባና ለመቀሌ ፖለቲከኞች መንገዶች ሁሉ ወደ ፕሪቶሪያ አመሩ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የፀጥታ አማካሪ ሪድዋን ሁሴይና የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ ጌታቸዉ ረዳ የመሯቸዉ የሁለቱ ወገኖች ባለስልጣናት ከሳምንት ድርድር በኋላ «ግጭትን ማቆም» ያሉትን የሰላም ስምምነት ተፈራራሙ።ሕዳር 2፣ 2022።እንደገና ዋና አደራዳሪ ኦሌሼጎን ኦባሳንጆ።

 «ዛሬ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪቃ ቀንድ በርግጥ ለመላዉ አፍሪቃ የአዲስ ንጋት ጅምር ነዉ።»

ምስል UGC/AP/picture alliance

የሁለት ዓመቱ ጦርነት በሰላም ስምምነት ተዘጋ።የሰሜን ኢትዮጵያ ምድርን እያረሰ ጥይት ቦምብ ዘርቶ አስከሬን ያሳጭድ የነበረዉ የጠመንጃ ላንቃ ተዘጋ።

የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላና የሕወሓት ወይም የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ከሕዳር 7 እስከ 12፣ 2022 ናይሮቢ-ኬንያ ዉስጥ ባደረጉት ዉይይት የፕሪቶሪያዉን ስምምነት ገቢር የሚያደርጉበትን ዉል ተፈራረሙ።

የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት፣ የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ከኢትዮጵያ የሐገር መከላከያ ሠራዊት ዉጪ ያሉ  ኃይላትን ከትግራይ ማስወጣት፣ የትግራይ  የሽግግር መንግስት መመስረትን በግንባርቀደምትነት የሚያካትተዉ የስምነቱ አካል ባብዛኛዉ ገቢር ሆኗል።

ከጂጅጋ እስከ ባሕርዳር፣ ከሰመራ እስከ ሐዋሳ፣ ከጋምቤላ እስከ አዲስ አበባ የሚገኙ ሚንስትሮች፣ የምክር ቤት እንደራሴዎች፣ የክልል መስተዳድር፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ የኃያማኖት አባቶች፣የአባገዳ መሪዎች መቀሌን ይመላለሱበት ይዘዋል።

የጦርነቱ ለኳሽ፣ አዋጊ፣ አባባሾች ባደባባይ ሲሿሿሙ፣ሲሸላለሙ፣ ሲሞጋገሱ በግልፅ እያየን ነዉ።በጦርነቱ ያለቁ፣የቆሰሉ፣የተደፈሩና የተሰቃዩ ኢትዮጵያዉያን ግን እስካሁን አስታዋሽ፣ የሟች ቁስለኛ ወገኖች እንባ አባሽ አላገኙም።ባለፈዉ ሁለት ዓመት ዉስጥ ብዙዎች ደጋግመዉ እንዳሉት ሰላምን የማይፈልግ ከጦርነቱ ተጠቃሚ ብቻ ነዉ።ሰላም በመስፈኑ በጦርነቱ የተሰቃየዉ የትግራይ፣የአማራና የአፋር ክልሎች ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላዉ ኢትዮጲያዊ የማይደሰትበት ምክንያት የለም።ይሁንና የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎች በጦርነቱ የበላይነት ለማግኘት ጎሳን ከጎሳ እየለዩ ያቃቃሩት ሕዝብ ቂም ቁርሾ በፕሪቶሪያዉ ስምምነት ተፍቋል ማለት በርግጥ በሕዝብ ማላገጥ ነዉ።

የፕሪቶሪያዉ ስምምነት ሰነድ ልዉዉጥ ከግራ ቀደቀኝ ሪድዋን ሁሴይን፣ ኡሁሩ ኬንያታና ጌታቸዉ ረዳምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የብልፅግና ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ ግርማ የሺጥላና አንጋቾቻዉን በጥይት ደብድበዉ የገደሉት ወገኖች የኢትዮጵያ መንግስት እንዳለዉ «ፅንፈኛ ኃይላት» ወይም ሌሎች እንደሚሉት ሌሎች ይሆኑ ይሆናል።በታጣቂዎች መገደላቸዉን የካደ የለም። ገዳዮቹ የታጠቁት፣የተደራጁ፣ ያሴሩት፣ ፖለቲከኛዉን በመግደል ሊያገኙ ወይም ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልዕክት ግን የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት መዘዝ አይደለም ማለት መፍትሔ ፍለጋዉን እንበለ መፍትሔ  ያስቀረዋል።

ነጋሽ መሐመድ 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW