1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ግምገማ

ሐሙስ፣ የካቲት 28 2016

በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ገቢራዊነት ላይ አሸማጋዩ የአፍሪካ ህብረት አፈጻጸሙን አዲስ አበባ ውስጥ ሲገመግም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ የአውሮጳ ኅብረት፣ ኢጋድ እና ዩናይትድ ስቴትስ በታዛቢነት ሂደቱን ይከታተላሉ ተብሏል፡፡

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፊርማ ላይ የተገኙት የደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር  የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ አቶ ሬድዋን ሁሴን የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ፣የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የህወሓት ተወካይ ጌታቸው ረዳ እንዲሁም የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉምዚለ ሚላምቦ ኩካ
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፊርማ ላይ የተገኙት የደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ አቶ ሬድዋን ሁሴን የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ፣የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የህወሓት ተወካይ ጌታቸው ረዳ እንዲሁም የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉምዚለ ሚላምቦ ኩካ ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ግምገማ

This browser does not support the audio element.

የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙትን ስምምነት አተገባበር መገምገም ጀመረ፡፡ ይህ የተሰማው በሁለቱ ወገኖች በኩል በስምምነቱ ሁለንተናዊ አተገባበር ላይ የተለያዩ የሚያወዛግቡ አስተያየቶችን መስጠታቸው ከቀጠሉ በኋላ መሆኑ ነው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች እና የትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የቆየው ደም አፋሳሽ ጦርነት እዲያበቃ የረዳውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ገቢራዊነት ላይ አሸማጋዩ የአፍሪካ ህብረት የእስካሁኑን አፈጻጸም አዲስ አበባ ውስጥ ለመገምገም ስብሰባ ሲቀመጡ፤ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮጳ ኅብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (IGAD) እና ዩናይትድ ስቴትስ በታዛቢነት ሂደቱን ይከታተሉታል ተብሏል፡፡ስብሰባው ከዛሬ ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚካሄድ ጥቆማዎች ብሰሙም የሂደቱ ዝርዝር ጉዳይን በተመለከተ ግን የተሰጡ ግልጽ ማብራሪያዎች የሉም፡፡ 

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፊርማበኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዥር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር ሲጨባበጡ ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images


ዶቼ ቬለ ስምምነቱን በተመለከተ የእስካሁን ሂደቱን ይገመግማል ስለተባለው ስለዚህ ስብሰባ ዝርዝር ጉዳዮች ከኢትዮጵያ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ባስነበቡት መረጃ ግን፤ የአፍሪካ ህብረት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ የረዳው የፕሪቶሪያው ስምምነት የእስካሁኑ አተገባበር የሚገመግም ስትራቴጂካዊ ስብሰባ መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡

 የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀምና ትችቱ
አቶ ጌታቸው በዚሁ ጽሁፋቸው “ይህ ፎረም ሁለቱ አካላት ማለትም የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአፍሪካ ህብረት የስምምነቱ ተወካዮች ጋር ተቀምጠው የስምምነቱ የእስካሁን አተገባበርን የሚገመግሙበት ነው” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ጌታቸው አክለውም የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (IGAD) እና ዩናይትድ ስቴትስ በታዛቢነት እንደሚቀመጡም አክለው ጠቅሰዋል፡፡ 
አቶ ጌታቸው አክለውም “ዘላቂ ሰላም በኢትዮጵያ እና በቃጣናው ማስፈን ከተቻለ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሙሉ አቅም ገቢራዊ በማድረግ የትግራይ ህዝብ ህገመንግስታዊ ፍላጎት ማሟላት ይቻላል” ሲሉም በጽሁፋቸው ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ይህ እንዲሆን የሚቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን ሲሉም አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ትናንት ማምሻውን ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክል ሐመር ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸውን አመልክቷል፡፡

በናይሮቢ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ግምገማ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 2022ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት የፖለቲከኞች አስተያየት

ልዩ መልእክተኛው በቆይታቸው የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ግምገማ ላይ እንደሚታደሙም ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የላከልን የኢ-ሜይል መረጃ አትቷል፡፡የውጭ መስሪያ ቤቱ መረጃ የፕሪቶሪያው ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ ለበርካቶች ሞት እና ለንብረት ውድመት ምክኒያት የሆነውን ጦርነት በመግታት የመሳሪያ ደምጽ እንዳይሰማ አይነተኛ ሚና መጫወቱን በአዎንታዊነት በማንሳት፤ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ግን ተጨማሪ ሂደቶች ያስፈልጉታል ሲል አስረድቷል፡፡ የስምምነቱ ቀሪ ስራዎች ትጥቅ በማውረድ የጸጥታ ኃይሎች መዋቅራዊ መቀላቀል( reintegration)፣ የሽግግር ፍትህ ሂደቶችን ማቀላጠፍ እና ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ወደ ቀዬያቸው መመለስ ናቸው ሲል ጠቁሟልም፡፡

ልዩ መልእክተኛው ሐመር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶችን መቋጨት በሚቻልበት መንገድ ላይ እንደሚወያዩም ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም በፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ላይ ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (IGAD) እና ሌሎች ዓለማቀፍ አጋር  ተቋማት ጋር እንደሚወያዩም ነው የተገለጸው፡፡
በጎርጎሳውያኑ 2022 መጨረሻ በፕሪቶሪያ በስምምነት የተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለበርካቶች እፎይታን የሰጠ መሆኑ በጉልህ ብነሳም፤ በአፈጻጸሙ ላይ ስምምነቱን የፈረሙ ሁለቱ ኃይሎች አልፎ አልፎም ብሆን ስወዛገቡ ይስተዋላል፡፡ የኤርትራ ሰራዊት ፈጽሞ ከሁሉም ትግራይ ክልል አከባቢዎች አለመውጣት፣ ከአወዛጋቢዎቹ የአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳን ግዛቶች የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ቀዬያቸው አለመመለስ እና የእርዳታ አቅርቦት ሁለቱን አካላት ካወዛገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡   

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW