የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነትን የተመለከተ የሕዝብ አስተያየት ከአማራ ክልል
ዓርብ፣ ጥቅምት 22 2017በኢትዮጵያ መንግሥትና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የነበረውን ጦርነት ለማስቆም ያስችላል የተባለው የሠልም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተፈረመ 2 ዓመት ሊሞላው ነው። ባለፉት 2 ዓመታት የሠላም ስምምነቱ ምን ያክል ተግባሪዊ ሆነ? በስምምነቱ መሰረት ምን ያልተሰራ ቀሪ ሥራ ይኖራል? ስንል የአማራና የትግራይ ክልሎች የይግባኛል ጥያቄ ያሉባቸው አካባቢ ነዋሪዎችን ጨምሮ የሌሎች የአማራ ክልል የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎችን አስተያየት ጠይቀናል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ስምምነቱ በዋናንት ጦርነቱ እንዲቆም በማድረጉ ሞትንና የአካል ጉዳትን ቀንሷል፣ ሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲጓጓዝ አግዟል፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንገድ መክፈቱም በበጎ የሚታዩ እንደሆኑ አመልክተዋል።
እንወያይ፤ ኢትዮጵያ ሌላ ዙር ግጭትን ለመሸከም ጫንቃዉ አላት?
በሌላ በኩል በስምምነቱ መሰረት ያልተተገበሩ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በስምምነቱ መሰረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ይፈታሉ ቢባልም እንዲይውም ትጥቃቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል ነው ያሉት።
የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎችም ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ መፍትሔ እንደሚያገኝ በስምምነቱ የተገለፀ ቢሆንም ጥያቄው መልስ ሳያገኝ 2 ዓመታት መቆጠሩን አስረድተዋል። አካባቢዎቹ የራሳቸውን አስተዳደራዊ መዋቅር ይዘረጋሉ ቢባልም የተሰራ ነገር ባለመኖሩ ጉዳዩ ትኩረት እንዳላገኘ እንደሚሰማቸው አስተያየት ሰጪዎቹ በቅሬታ ተናግረዋል።
አንድ አስተያየት ሰጪ “የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ጦርነቱን ከትግራይ ወደ አማራ ክልል እንዲዛወር ምክንያት ከመሆን ውጪ ያመጣው አንዳችም ፋይዳ አልታየኝም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር