የፕራግ ማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያዉያን አሸነፉ
እሑድ፣ ሚያዝያ 26 2017
በቼክ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ፕራግ ዛሬ የተካሄደውን የወንዶች ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሚ ብርሃኑ አሸነፈ። ለሚ ለሁለት ተከታታይ አመታት የፕራግ ውድድርን በማሸነፍ እስካሁን በፕራግ በተካሄዱ 30 ውድድሮች ክብረ ወሰኑን ያስጠበቀ የመጀመሪያው አትሌት ለመሆንም በቅቷል። ለሚ ውድድሩን ለመጨረስ የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ ነው። አትሌቱ ሁለተኛ ከወጣው ኬንያዊ ፊሊክስ ኪፕኮች ገና ከ 30ኛው ኪሎ ሜትር በፊት ተነጥሎ በመውጣት ያለ ማንም ተፎካካሪ ሊያሸንፍ ችሏል። ጃፓንያዊው ቴትሱያ ዮሮኢሳካ ከአራት ደቂቃ ገደማ በኋላ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ በርቀቱ የዓለም የሴቶች ክብረ-ወሰን በማሻሻል አሸነፈች
በሴቶች መካከል የተደረገው ውድድር እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ ልብ አንጠልጣይ ሆኖ ቆይቷል። በመጨረሻም ኢትዮጵያዊቷ ብርቱካን ወልዴ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ 55 ሰከንድ በሆነ ሰአት አሸናፊ ሆናለች። ከብርቱካን 30 ሰከንድ ብቻ በመዘግየት ኬንያዊቷ ኢቫሊን ቺርቺር ሁለተኛ በመግባት የማጠናቀቂያ መስመሩን ስታቋርጥ የሀገሯ ልጅ ፓስካልያ ቼፕኮጌ ሶስተኛ ሆናለች።
ኢትዮጵያውያን ባሸነፉበት የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ቻይና ሮቦቶች ከሰዎች አወዳደረች
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካዋ ማያሚ እያስተናገደች ባለው የግራንድ ስላም የሩጫ ውድድር በ1500 ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ ኃይሉ በድንቅ አጨራረስ አሸንፋለች። ፍሬወይኒ ርቀቱን ለመጨረስ 4:06.96 ወስዶባታል። በውድድሩ ብርቱ ፍክክር ያደረገችው አሜሪካዊቷ ኒኪ ሂልስ ሁለተኛ ስትሆን የወሰደባት ጊዜም 4:07.08 ሆኗል። በርቀቱ የጃማይካውን ግራንድ ስላም አሸናፊ የነበረችው ድርቤ ወልተጂ ሶስተኛ ወጥታለች።