የፕሬዝደንት ትራምፕ የዉጪ መርሕ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረዉ ተፅዕኖ
ማክሰኞ፣ ጥር 13 201747ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ትናንት ሰኞ ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥራቸውን በይፋ ጀምረዋል።እስካሁን በርከት ያሉ አዳዲስ ውሳኔዎች ላይ የፈረሙ ሲሆን የሻሯቸውም ሕግጋት ጥቂት አይደሉም።አሜሪካ ከኢትዮጵያ አንፃር በሚኖራት ግንኙነት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ጥቂት ሰዎች ፕሬዝዳንቱ ሥጋትም ተስፋም ይዘው የመጡ ስለመሆናቸው ገልፀዋል።
ጾታን በተመለከተ ያራመዱትን ውሳኔበበጎ የተመለከቱ የመኖራቸውን ያህል የአሜሪካን የልማት ድጋፍ በእጅጉ እንዳይቀንሱ ያሰጋል ያሉም አሉ።ትራምፕ ይህንኑ ዕድል ከአራት ዓመት በፊት አልፈውበታል።ፕሬዝዳንቱ በሀገራቸው "ሁለት ጾታዎች ብቻ" መኖራቸውን እና እነሱም ወንድ እና ሴት ብቻ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።
ይህ ለኢትዮጵያዊው የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ መሠረታዊ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ለውጥ ይመስላል።ጉዳዩ "የሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ስለሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ሥነ ምግባራዊ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል"።ይህ በሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም በበጎ የታየ ይመስላል።
ፕሬዝዳንቱ ሕገ ወጥ ሂደትን የተከተሉ ስደተኞችን አልታገስም ማለታቸው ለሌላኛው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራቂ አስተያየት ሰጪ የሀገሩን ደህንነት እንዳስቀደመ መሪ ክፋት ያለው አይደለም። ሆኖም ለሕክምና ፣ ለትምህርት፣ ለቤተሰብ ጥየቃ፣ በዲቪ የሚደረጉ ጉዞዎችም ጭምር ይቀጥላሉ የሚል እምነት አላቸው። ለኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች መፍትሔ ሊኖር እንደሚችልም አያይዘው ግምታቸውን ጠቅሰዋል።
"አሁን ያለው የውስጥ ቅራኔዎች፣ የውስጥ ግጭቶች የሚቋጩበት ዕድል ሊኖር ይችላል የሚል ግምት አለኝ"።የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኙ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና የማይቀር ስለመሆኑ ነው የሚገልፁት።
"የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ብዙ ነገሮች ላይ ጫና እንደሚወድቅበት ይታመናል።"
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራቂው የትራምፕ አስተዳደር የቻይናን የአፍሪካ የንግድ የበላይነት ለመቀናቀን ከተቻለም ለመግታት ኢንቨስትመንትን ሊያስፋፉ እንደሚችሉ እምነቱን ገልጿል።የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኙ ግን ትራምፕ የነጋዴ ባህሪ ያላቸው ፕሬዝዳንት ቢሆኑም ከወታደራዊ ድጋፍ ባሻገር በሰብዓዊ እና የልማት ድጋፍ ላይ ለየሀገራቱ የሚያደርጉት ተሳትፎ እና እገዛ ሊቀንሱ ይችላል።
እኒሁ ባለሙያ "ለግብጽ ሎተሪ ነው የወጣላት" ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል። እንደ አጠቃላይ አፍሪካን በሚመለከት ግን አፍሪካ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ዕይታ "እያለች ከሌለች የምትቆጠር ናት።"
ዩናይትድ ስቴትስን ለአራት ጊዜ ወይም ዙር ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ብቸኛው ሰው ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቤልት ሲሆኑ ከእሳቸው በኋላ አንድ አሜሪካዊ ለዚሁ ኃላፊነት ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንዳይችል በሕግ ተገድቧል።
ሰለሞን ሙጪ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ