1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የካበተ ልምድ ጠቀመ ወይስ ጎዳ?

ሰኞ፣ ጥር 12 2017

የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ ባለፉት ሁለት ዓመታት አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የ65 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ አስታጥቃለች።አሜሪካዊዉ ግን የኒዮርኳ ነዋሪ እንዳሉት በኑሮ ዉድነት፣በሥራ ዋስትና እጦት፣ ሥጋት ተዉጧል

እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር 1970 ጀምሮ ፕሬዝደንት እስከሆኑበት እስከ 2021 ድረስ የአዉራጃ ምክር ቤት፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል፣ የኮሚቴ መሪ፣ ሕግ አርቃቂ፣እጩ ፕሬዝደንት፣ምክትል ፕሬዝደንት
ጆሴፍ ሮቢኔቴ ባይደን ትንሹ፣ የዩናይትድ ስቴትስ 46ኛ ፕሬዝደንት።ፕሬዝደንት ባይደን ሥልጣን ከመያዛቸዉ በፊት ለ50 ዓመታት ከአሜሪካ ፖለቲካ አልተለዩም።ምስል Stephanie Scarbrough/AP/picture alliance

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የካበተ ልምድ ጠቀመ ወይስ ጎዳ?

This browser does not support the audio element.

ዩናይትድ ስቴትስ ከ2017 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ለዓለም ትልቅ ሥልጣን በሁለት አዛዉንቶች መሐል ተቃርጣ ትራምፕ-ባይደን፣ ባይደን-ትራምፕ እንዳለች ዓለምን  ግራ ቀኝ እንደከፈለች ነዉ።ከእንግዲሕም የፕሬዝደንትነት ሥልጣንን ለቅቀዉ ዳግም ሥልጣን በመያዝ ከ1893 ወዲሕ የመጀመሪያዉን ፖለቲከኛ መርሕ እንደተከተለች-ትራምፕ እያለች ዓለምን እንዳስከተለች አራት ዓመት ትቀጥላለች።ጆ ባይደንን ግን ከ50 ዓመታት በኋላ ከፖለቲካዉ አሰናብታለች።ረጅም ዘመን ካስቆጠረዉ ከባይደን መርሕ- ምግባር ጥቂቱን አንስተን፣ አስተምሕሮቱን ጠቃቅሰን እንሰናበታቸዉ።

በከ1970 ጀምሮ የአዉራጃ ምክር ቤት፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል፣ የኮሚቴ መሪ፣ ሕግ አርቃቂ፣እጩ ፕሬዝደንት፣ምክትል ፕሬዝደንት፣ ከ2021 ጀምሮ እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ ፕሬዝደንት ነበሩ።55 ዓመት።ጆሴፍ ሮቢኔቴ ባይደን ትንሹ።

የዳበረዉ ዕዉቀትና የካበተዉ ልምድ ዉጤት

 

በ2021 የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ሲረከቡ የዶክተርነት ማዕረግ የጫኑበት የሕግ ዕዉቀት፣ እንደ ምክር ቤት እንደራሴ፣ እንደ እጩ ፕሬዝደንት፣ እንደ ምክትል ፕሬዝደንት ለ50 ዘመን ያካበቱትን የፖለቲካ ልምድ የዚያቺን የዓለም ልዕለ ኃያል ሐገርን ሕዝብ አንድነት፣ የዓለምን ሠላምና  ደሕንነት ለማስከበር ያዉሉታል ነበር-የብዙዎች ተስፋ።ግን የዋሽግተኑ ወኪላችን አበበ ፈለቀ እንደታዘበዉ ተስፋዉ የወለፊንድ ባርቋል።

«የቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነትን ማብቃት፣ የዎተርጌትን ቅሌት፣ በርካታ አሜሪካ የተሳተፈችባቸዉን ጦርነቶች በፖሊሲ አዉጪነት ሲያግዙ የኖሩ በምክትል ፕሬዝደንትነት ያስተዳደሩ----ያም ሆኖ ግን ወደ ሥልጣን ሲመጡ በአሜሪካ ታሪክ ዉስጥ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ምሥቅልቅል    

የኮኒከቲከት ነዋሪ ግን ባይደን ሥልጣን ሲይዙ የነበረዉን ተስፋ ገቢር አድርገዉታል ባይ ናቸዉ።

«ብዙ ነገር አድርገዋል።የከባቢ ዓየርን ለማስጠበቅ እኔ የማስበዉን አድርገዋል።በተለይ አሜሪካ በዓለም ያላትን ሥፍራ አስከብረዋል። የኔቶን አንድነት አጠናክረዋል።»

የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርም ባለፈዉ ጥቅምት ይሕን መስክረዋል።

«በርስዎ መሪነት የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ትብብር ተጠናክሯል።ወዳጅነታችን ከመቼዉም ጊዜ የበለጠ ተቀራርቧል።ሚስተር ፕሬዝደንት ለጀርመን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለዎት ለግማሽ ምዕተ-ዓመታት ያክል እናዉቃለን።አሁን ደግሞ ጀርመን በፋንታዋ የርስዎን ዉለታ ታስታዉቃለች።በሐገሬ ስም «ሚስተር ፕሬዝደንት አመሰግናለሁ ልበል።

የኒዮርኳ ነዋሪ ግን «ዩክሬን ለኔ ምን ያደርግኛል ይላሉ።

ከግራ ወደ ቀኝ የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ባለፈዉ ጥቅምት ለአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የጀርመንን ታላቅ ሽልማት ባለፈዉ ጥቅምት ሲሸልሙምስል Matthias Schrader/AP/picture alliance

«ከትርምስ በስተቀር ምንም ያየሁት ነገር የለም።ለእደኔ አይነቱ ተራ ሰዉ የምንፈልገዉ የኑሮ ዋስትና፣ሥራና ደሕንነት ነዉ።ሥለዩክሬን አያገባንም።»

ባይደን ፤ ጥሩ ጀማሪ መጥፎ ፈፃሚ

የኒዮርክ ከተማ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ባይደንን ጥሩ ጀመሪ ግን መጥፎ ፈፃሚ አይነት ይሏቸዋል።ሁሉም አላበሉም።ጆ ባይደን ምክትል ፕሬዝደንት በነበሩበት ዘመን ፓሪስ ላይ የተፈረመዉን የዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ስምምነትን ፕሬዝደንት ትራምፕ አፍርሰዉት ነበር።ባይደን  አሜሪካንን የስምምነቱ አካል አድርገዋል።በፕሬዝደንት ትራምፕ ዘመን በሥጋት ተሞልቶ የነበረዉን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሐገራትን ወዳጅነት ባይደን አጠናክረዉታል።

ሩሲያ በ2022 ዩክሬንን ስትወር ባይደን አዉሮጶችን አስተባብረዉ ሩሲያን በማዕቀብ ቀጥተዋል።ለዩክሬን ጠንካራ የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ፣ የገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ ድጋፍና ወታደራዊ ሥልጠና ሰጥተዋል።አስጥተዋልም።

ዓለምንም እንደ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን አሜሪካ የምትመራዉና የሞስኮ-ቴሕራን-ፒዮንግ ዮንግ ካራካስ-ምናልባትም የቤጂንግ በሚባለዉ ሕብረት ለሁለት ገምሰዉታል።

የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ ባለፉት ሁለት ዓመታት አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የ65 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ አስታጥቃለች።አሜሪካዊዉ ግን የኒዮርኳ ነዋሪ እንዳሉት በኑሮ ዉድነት፣በሥራ ዋስትና እጦት፣ ሥጋት ተዉጧል።እንደገና አበበ ፈለቀ።

«ሌላዉ ትልቁ ነገር አሜሪካ በሁለት-ሶስት ጦርነቶች መልቲ ቢሊዮን ዶላር እያወጣች ሥትዋጋ የእንቁላል ዋጋ 500% አድጓል እዚሕ አገር።የቤቶች ዋጋ የትዬለሌ ጨምሯል ኢንተረስት ሬት አታገኝም።ኢንፍሌሽን ከደሞዝ ጭማሪ በላይ ነዉ።ሰዉ እዚሕ አሜሪካ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነዉ የነበረዉ።ሰዉ እዚሕ ተቸግሮ እያለ አሜሪካ በማያገባት ጦርነት ዉስጥ ገብታ ማቧቸሯ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነዉ ያለዉ።የኤኮኖሚ ድቀቱ፣ የወደቀ የዉጪ ግንኙነት ፖሊሲዉ መሠረታዊ ችግር ተደርጎ ሊታይ ይችላል።»

የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ከ2022 ጀምሮ አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ለዩክሬን መንግሥት 65 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጦር መሳሪያና ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች።ምስል Efrem Lukatsky/AP/picture alliance

ፕሬዝደንት ባይደን ሥልጣን እንደያዙ የኮሮና ሥርጭትን ለመግታት የወሰዱት እርምጃ ብዙ ተወድሶላቸዋል።ያረጁና ያፈጁ የአሜሪካ የመሠረተ ልማት አዉታሮችንና መንገዶችን ማስጠገናቸዉንም ብዙዎች ያደንቃሉ።በሴናተርነት ዘመናቸዉ ለብዙ ዘመናት የሠሩና የመሩት የዉጪ ግንኙነት ጉዳይ ኮሚቴን ነዉ።እንደ ፕሬዝደንት ጨርሶ ያሽመደመዱትም የትልቂቱን ሐገር ትልቅ የዉጪ መርሕን ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ከአፍቃኒስታኑ የታሊባን ቡድንና ከተባባሪዎቹ ጋር  20 ዓመት ተዋግተዋል።

የባይደን የዉጪ መርሕ ዉድቀት-ከአፍቃኒስታን እስከ ጋዛ

ባይደን ለአሜሪካ ተባባሪ መንግሥታት እንኳን በቅጡ ሳያማክሩ አፍቃኒስታን ለታሊባን አስረክበዉ፣ ለ20 ዓመት ለአሜሪካ ያገለገሉ፣ የተባበሩ፣በታሊባን የሚታደኑ አፍቃኒስታናዉያንን ጥለዉ የአሜሪካ ጦር ከአፍቃኒስታን እንዲወጣ አዘዙ።የባይደን የዉጪ መርሕ ዉደቀት ያኔ በግልፅ ጀመረ።የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ሲጫር ቀጠለ።

የጋዛ እልቂት፣ የሊባኖስ ዉድመት፣የየመን ጥፋት፣የኢራን-እስራኤል-አሜሪካ ፍጥጫ፣ የአሜሪካ-ቻይና ሽኩቻ እያለ ዉድቀቱ ይግተለተል ገባ።

«ምናልባት ጆ ባይደን ጥንቅቅ አድርገዉ ሊያዉቁ ይገባል የሚባለዉ መስክ የዉጪ ጉዳይ ነዉ።ምክንያቱን ሴናተር በነበሩበት ዘመን የዉጪ ጉዳይና የደሕንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ነዉ የነበሩት።በርካታ የዓለም ጉዳዮችን በቃላቸዉ አጥንተዉ የሚያዉቁ ሰዉ ናቸዉ።ግን የጣላቸዉ በተለይ አሜሪካ ከአፍቃኒስታን የወጣችበት መንገድ እጅግ በጣም ምስቅልቅል ነበረ።----»

ጋዛዎች ከትናንት ቀትር ጀምሮ ከእስራኤል ቦምብ፣ሚሳዬል መድፍ አዳፍኔ ድብደባ፣ አፈሳ፣ እመቃና የረሐብ ቅጣት ተንፈስ ብለዋል።ለ15 ወራት የታገቱ እስራኤላዉያንም ከዘመድ ወዳጆቻቸዉ ጋር መገናኘት ጀምረዋል።

እልቂት-ፍጅት፣ ጥፋት እገታዉን ያስቆመዉን ስምምነት እስራኤልና ሐማስ እንዲቀበሉ ጫና ያደረገችዉ አሜሪካ መሆንዋ በርግጥ አላነጋገረም።ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ባይደንና አዲስ መጪዉ ፕሬዝደንት ትራምፕ ምስጋናዉን ለማግኘት እየተሻሙ ነዉ።የባይደን አስተዳደርን መርሕ ላለፉት 15 ወራት በቅርብ የተከታተሉ እንደሚሉት ግን በተለይ እስራኤል ተኩስ አቁሙን የተቀበለችዉ በትራምፕ ጫና እንጂ በባይደን ግፊት አይደልም።

በዚሕም ብሎ በዚያ እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣የአዉሮጳ ሕብረትና ብሪታንያ በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ጥቅምት 7፣ 2023 እስራኤልን ወርሮ 1200 ያክል የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎችን ገድሏል።በመቶ የሚቆጠሩ አግቷል።

የሐማስን ጥቃት ለመበቀል የያኔዉ የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት «የሰዉ አዉሬዎች» ባሏቸዉ የጋዛ ፍልስጤሞች ላይ እስራኤል በከፈተችዉ መጠነ-ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከ46 ሺሕ በላይ ሰዎችን ገድላለች።ከ11 ሺሕ የሚበልጡ ፍልስጤማዉያን አንድም አስከሬናቸዉ አልተገኘም አለያም ያሉበት አይታወቅም።

ሐኪሞች፣ ጋዜጠኞች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞች፣ ርዳታ አቀባዮች ዕለት በዕለት ተገድለዋል።ከመቶ ሺሕ የሚበልጥ ሕዝብ ቆስሏል።በሺ የሚቆጠሩ ታስረዋል።2.3 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የጋዛ ህዝብ ከ90 ከመቶ የሚበልጠዉ ካንድ ጊዜ በላይ ተፈናቅሏል።በረሐብ፣ በዉሐ ጥማት፣በመድሐኒት እጦት ተገርፏል።

በፍልስጤማዉያን ላይ የሚፈፀመዉ ግድያ፣ ግፍ እመቃ እንዲቆም የአብዛኛዉ የዓለም ሕዝብ በተከታታይ ያደባባይ ሰልፍ ጮኋል።መንግሥታት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሕልቆ መሳፍት የሌላቸዉ የመብት ተማጋች ድርጅቶች፣ ማሕበራት፣ ታዋቂ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች በይነዋል።

የዓለም የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የሰዎች እኩልነት አብነቷ ሐገር መሪ ግን ዲፕሎማቶቻቸዉን ባዉረፕላን እያመላለሱ የጦር መሳሪዎቻቸዉን በመርከብና በአዉሮፕላን ወደ እስራኤል ያግዙ ነበር።

እስራኤልና ሐማስ የጋዛን ጦርነት ለማቆምና የታገቱና የታሰሩ ሰዎችን ለመልቀቅ ከተስማሙ በኋላ የጋዛ ሕዝብ 15 ወራት ካስቆጠረዉ ድብደባ፣ እልቂትና ረሐብ ተንፈስ ብሏል። ምስል Abed Rahim Khatib/dpa/picture alliance

ጥናቶች እንደጠቆሞት ከጥቅምት 7 ቀን 2023 ወዲሕ ዩናይትድ ስቴትስ ለእስራኤል ያስታጠቀችዉ ጦር መሳሪያ 17.9 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል።

የባይደን ጥፋት ለሚመሩት ፓርቲም ተርፏል

የጋዛዉ እልቂት መዘዝ ወደ ሰሜን እስራኤልና ሊባኖስ ተሻግሮ ሺዎችን አጥፍቷል።ኢራንና እስራኤልን አታኩሷል።የመንን ከቀዉሱ ሞጅሮ አሜሪካኖችን ለቀጥታ ዉጊያ ዳርጓል።አበበ እንደሚለዉ ደግሞ የባይደን የዉጪ መርሕ ዉድቀት እራሳቸዉ ባይደን ለሚመሩት ፓርቲም ዉድቀትን ተርፏል።

«በተለይ የጋዛ ጦርነት አረብ አሜሪካዉያንን ከራሳቸዉ ፓርቲ ጋር ያጋጨ።እንዲያዉም እኚሕ ሰዉ ከአሜሪካ ፖሊሲ ይልቅ የእስራኤል ጉዳይ አስፈፃሚ ናቸዉ እሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል።---»

የኩባዉ ስደተኛ እንደሚሉት ደግሞ መጠየቅ ያለበት ችግሩ ባይደን ሌላዉን አካባቢ ወይም አሜሪካንን ጎዱ አልጎዱ አይደለም።መጠየቅ ያለበት በራሳቸዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ላይ ምን ያሕል ጥፋት አደረሱ ተብሎ ነዉ።

«ችግሩ ምን ያሕል መጥፎ ነገር ሰሩ አልሰሩ አይደለም።ችግሩ የራሳቸዉን ፓርቲ ምን ያሕል ጎዱ ነዉ።የፓርቲዉን መስመር ምን ያሕል አወለካከፉት ነዉ።»

ዕዉቁ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሥልት ቀያሽ ጄምስ ካርቪሌ «የጆ ባይደን ታሪክ በአሜሪካ ፖለቲካ ከታዩ ትላልቅ ድቀቶች አንዱ ነዉ።» ይላሉ።«እዉነቴን» ቀጠሉ የፖለቲካ አዋቂዉ «በጣም አንፀባራቂ፣ ተወዳጅና የተከበረ ጡረታ በኖራቸዉ ነበር።ግን ሰዉዬዉ የሚገባቸቸዉ አልሆኑም።» እያሉ።እና የ82 ዓመቱ አዛዉንት የ54 ዓመትt ፖለቲካ አለቀ፣ደቀቀ።የተቀረዉ ዓለምም ዋሽግተን ነፋስ ወደሚቦንበት ዘንበል፣ ዘንጠፍ፣ ዘርጋ እንዳለ ይቀጥላል።እስከ መቼ አናዉቅም።ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW