1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 7 2010

በአቶ ኢሳያስ የተመራው ከፍተኛ የኤርትራ ልዑካን ቡድን  ዛሬ ጠዋት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ታዋቂ ግለሰቦች ስፖርተኞች እና አርቲስቶች ደማቅ አቀበባል አድርገውለታል። የአዲስ አበባ  እና አካባቢዋ ነዋሪዎችም ደስታቸውን በሆታ እና በጭፈራ ሲገልጹ ነበር። 

Äthiopien - Besuch des Präsidenten Isayas Afewerki aus Eritrea
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Ayene

የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝብ የተለያየ ህዝብ ነው ብለው የሚያስቡ ሀቁን የማያውቁ ናቸው አሉ። ከ22 ዓመታት በኋላ ለሦስት ቀናት ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት አቶ ኢሳያስ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተደረገላቸው የምሳ ግብዣ ላይ ባሰሙት ንግግር የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝብ አንድ ነው ብለዋል። 
«ከሁሉ አስቀድሞ አሁን የሚሰማንን ደስታ በቃላት ለመግለጽ ይከብደኛል። ስንናገር ታሪክ እየተሰራ ነው። የሞቱት ይኽን ሳያዩ አልፈዋል፤ ሆኖም  እኛ የዛሬዋን እለት ለማየት በመብቃታችን እድለኞች ነን። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝብ ሁለት ህዝብ ነው የሚሉ ሀቁን የማያውቁ ናቸው።»
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለአቶ ኢሳይስ እና ለልዑካን ቡድኑ ህዝቡ ላደረገው አቀባበል በብሔራዊ መንግሥቱ ስነ ስርዓት ላይ አቶ ኢሳያስን ለንግግር ከመጋበዛቸው በፊት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 
«ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የአዲስ አበባ እና የአካባቢዋ ህዝብ 24 ሰዓት ቢሰራለት ደማችንን ብናፈስለት በምንም  ዋጋ ልንከፍል የማንችለውን ፍቅር በተግባር አሳይቶን ሳንሰጠው ሳናገለግለው ሳንሰራለት ያከበረንን ህዝብ ብዙ መናገር ብፈልግም እንኳ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ መናገር ስለማልፈልግ እጅግ የተወደደድክና የተከበርክ በኢትዮጵያ ህዝብ የምትናፈቀው የሀገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት ወደ መድረክ መጥተህ ለህዝብህ መልዕክት እንድታስተላልፍ በታላቅ አክብሮት እጋብዛለሁ።»
አቶ ኢሳያስም በምላሹ ላሳያችሁን ልባዊ ፍቅር  እናመሰግናለን ብለዋል። በምሳ ግብዣው ላይ ዶክተር ዐብይ ከአንዲት እናት የተበረከተ የወርቅ ቀለበት ለአቶ ኢሳያስ ሰጥተዋቸዋል። ታዋቂው ሰዓሊ ለማ ጉያም የሳሉትን የርሳቸውን ምስል እንደሰጧቸው ተዘግቧል። አቶ ፍጹም አረጋ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ በትዊተር ገጻቸው በፎቶ አስደግፈው እንዳሰፈሩት ደግሞ የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ የተሸለመ ፈረስ፣ እንዲሁም ጦር እና ጋሻ ሸልመዋቸዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ዛሬ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክንም ጎብኝተዋል።ሀዋሳ ከተማ ሲገቡም የአካባቢው ህዝብ ደማቅ አቀባበል እንዳደረገላቸው የሀገር ውስጥ መገናና ብዙሀን ዘግበዋል። አቶ ኢሳያስ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ማብቃቱን በይፋ ባሳወቁ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። ከዶክተር ዐብይ አህመድ ያለፈው ሳምንቱ  የኤርትራ የሦስት ቀናት ጉብኝት በኋላ ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ በተስማሙት መሠረት የአዲስ አበባው የቀድሞ የኤርትራ ኤምባሲ በአቶ ኢሳያስ  ጉብኝት ወቅት ዳግም ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል። አዲስ አበባ ስታድዮም ፊት ለፊት የሚገኘው ይኽው ኤምባሲ አፋጣኝ  እድሳት እየተደረገለት መሆኑ ተዘግቧል።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW