1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ሥርዓተ-ቀብር ተፈጸመ

ሐና ደምሴ
እሑድ፣ ጳጉሜን 3 2016

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የሥልጣን ክፍፍል እና በሕገ-መንግሥቱ ጽኑ ዕምነት የነበራቸው እንድሪያስ እሸቴ ከተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢሕአዴግ ተሰሚነት የነበራቸው የፖለቲካ ፈላስፋ ነበሩ። እንድሪያስ “እኩልነትን እና ፈቃደኛነትን ምሰሶ ያደረገ አንድነት መተማመንን መተዛዘንን ስለሚያስከትል ዘላቂ ወንድማማችነትን ሊያፈራ ይችላል” የሚል እምነት ነበራቸው።

ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ
ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ “እኩልነትንና ፈቃደኛነትን ምሰሶ ያደረገ አንድነት መተማመንን መተዛዘንን ስለሚያስከትል ዘላቂ ወንድማማችነትን ሊያፈራ ይችላል” የሚል እምነት ነበራቸው።ምስል Ulrike Koltermann/dpa/picture-alliance

ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ በቤተሰቦቻቸው አንደበት

This browser does not support the audio element.

የፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ሥርዓተ-ቀብር ዛሬ እሁድ በአዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ። ፕሮፌሰር እንድሪያስ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ነሐሴ 23 ቀን 2016 ነበር።

ሥርዓተ-ቀብራቸው ከመፈጸሙ በፊት በፕሬዝደንትነት በመሩት እና ባስተማሩበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ራስ መኰንን አዳራሽ የስንበት ሥነ-ሥርዓት ተካሒዷል። በመርሐ ግብሩ ርዕሰ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው ተገኝተዋል።

እንድሪያስ የካቲት 23 ቀን 1937 ከእናታቸው ወይዘሮ መንበረ ገብረ ማርያም እና ከአባታቸው አቶ እሸቴ ተሰማ በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። እናታቸው “አንድ ሰው” ብለው ይጠሯቸው እንደነበር ታናሽ ወንድማቸው ናፖሊዮን እሸቴ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“እንደ እንድሪያስ ለገንዘብ ግድ የሌለው ሰው አላውቅም” የሚሉት ናፖሊዮን “በጣም ደግ፣ ያለውን አንስቶ የሚሰጥ ሰው ነው። በሰው መካከል ልዩነት የማያውቅ፤ ደሀ አይልም፣ ጌታ አይልም። ሁሉን ዕኩል የሚያይ” ነበር ሲሉ ወንድማቸውን ዘክረዋቸዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የታሪክ ፍልስፍና ውስጥ ከፍ ብለው ለመጠራት የበቁት እንድሪያስ ቤተሰባቸውን እና አበባ የሚወዱ ሽቅርቅር እንደነበሩ ወንድማቸው ይመሰክራሉ።

የታናሽ እህታቸው አምሳለ እሸቴ ልጅ የሆኑት ዶክተር ሉሊት አበራ “ጨዋታ አዋቂ” እንደነበሩ የሚመሰክሩላቸው አጎታቸው “በጣም ደግ፣ ምንም ነገር ለእኔ የማይል” ሲሉ ይገልጿቸዋል። ፕሮፌሰር እንድሪያስ “ወንድማማችነት፣ ፍቅር፣ ደግነት እና መተሳሰብ ያለበትን ኢትዮጵያ በጣም የሚናፍቅ ነው” የሚሉት ዶክተር ሉሊት “ኢትዮጵያን እንደ አንድ ቤተሰብ” አድርገው ይመለከቱ እንደነበር አስረድተዋል።

“እንድሪያስ የራሱ ሰው ሆኖ አያውቅም” የሚሉት ታናሽ ወንድማቸው ኤርሚያስ እሸቴ “በጣም መልካም ሰው ነው” የሚሏቸው ፕሮፌሰር እንድርያስ የራሳቸው ጥሪት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር እንድሪያስ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ተወልደው ባደጉት አራት ኪሎ በሚገኘው ምኒሊክ ትምህርት ቤት ነው።

በ16 ዓመታቸው ወደ አሜሪካ አቅንተው በማሳቹሴትስ ግዛት በሚገኘው ዊሊያምስ ኮሌጅ ፍልስፍና ተምረዋል። እንድሪያስ በሥመ-ጥሩው የል ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ትምህርት ጥናታቸውን አጠናቀዋል። በዊሊያምስ ኮሌጅ፣ በየል፣ ብራውን፣ ካሊፎርኒያ፣ ፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲዎች እና በሐርቫርድ ኮሌጅ በመምህርነት አገልግለዋል።

ለትምህርት በተጓዙበት አሜሪካን ሀገር በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ የሲቪል መብቶች እንዲከበሩ በተለይ በጥቁር የለውጥ አራማጆች በተደረጉ ትግሎች ውስጥ ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያን ፖለቲካ አካሔድ የቀየደው የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳትፎ የነበራቸው እንድሪያስ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር (ESUNA) አመራሮች መካከል አንዱ ነበሩ።

ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ ነበሩምስል dapd

የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ጨምሮ ለውጥ ፈላጊ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ባነሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተደረጉ ክርክሮች ውስጥ ቀዳሚ ሚና ነበራቸው። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዘውዳዊ መንግሥት ለመቃወም ተማሪዎች በአሜሪካ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲቆጣጠሩ መሪ ከነበሩ መካከል አንዱ እንድሪያስ እሸቴ ናቸው።

50 ዓመታት፦ የኢትዮጵያ አብዮት ውርስ ምንድነው?

እንድሪያስ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት መንግሥቱ ኃይለማርያም ይመሩት የነበረው ደርግ መንግሥት በ1983 ከሥልጣን ሲወገድ ነበር። በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ዝግጅት ሒደት ንቁ ሚና የነበራቸው እንድሪያስ “በአዲሲቱ ኢትዮጵያ ለዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና የበከሉና የተፈታተኑ አያሌ በደሎችን ለማስወገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕድል ተገኝቷል” የሚል እምነት ነበራቸው።

በኢትዮጵያ በተተከለው ፌድራላዊ የመንግሥት አወቃቀር “ሕዝቦች በየደረጃው የራስ ገዝ መብት ባለቤት ሆነዋል፡፡ በፌደራል መንግሥት ውክልናቸው፣ እኩልነታቸውንና ነፃነታቸውን በአገር ደረጃ ማስከበር ይችላሉ” ሲሉ በሕዳር 1999 የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲከበር ባቀረቡት ዲስኩር ሞግተዋል።

በፖለቲካ አቋማቸው አወዛጋቢ የነበሩት እንድሪያስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለስምንት ገደማ አመታት በፕሬዝደንትነት መርተዋል። ከዩኒቨርሲቲው ኃላፊነታቸው ከለቀቁ በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ ነበሩ።

በሥራ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እና ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር አጥብቀው የሚኮንኑ አልያም የማይቀበሉ የፖለቲካ ኃይሎች ለአንድሪያስ እሸቴ ቀና አመለካከት አልነበራቸውም። በኤርትራ ጉዳይ ላይ የሰጡት አስተያየት ለኃይለኛ ተቃውሞ ዳርጓቸዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ሳሉ ከ300 በላይ ተማሪዎች የተባረሩበት ውሳኔም ዛሬም ድረስ ከሚወቀሱባቸው ጉዳይ አንዱ ነው። 

 

ሐና ደምሴ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW