የፖለቲከኞች ከእስር መለቀቅና የእነዶ/ር ወንድወሰን የፍርድ ቤት ውሎ
ዓርብ፣ መጋቢት 6 2016በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሠፋ መዝገብ ስር ከተካተቱት 53 ተከሳሾች መካከል 21ዱን በተመለከተ ዛሬ ፍርድ ቤት ሦስት ውሳኔዎችን አሳለፈ ። የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የሦስተኛ ጸረ ሽብር ችሎት ዛሬ ባዋለው ችሎት አቃቤ ሕግ ተከሳሾች በአካል ሳይሆን በፕላዝማ ችሎት ይታደሙ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል ።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የሦስተኛ ጸረ ሽብር ችሎት ዛሬ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሠፋ መዝገብ ስር ከተካተቱት ተከሳሾች መካከል 21ዱን በተመለከተ ሦስት ውሳኔዎችን አሳለፈ ። ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ያስተላለፈውን ውሳኔ ለመመልከት ከ21ዱ ውጪ ቀሪ ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው መወሰኑንም ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰለሞን ገዛኸኝ ዛሬ ለዶይቸ ቬለ በስልክ ተናግረዋል ። አቃቤ ሕግ ተከሳሾች በአካል ሳይሆን በፕላዝማ ችሎት ይታደሙ ሲል ያቀረበውን ጥያቄም ውድቅ ማድረጉንም ገልጠዋል ።
«እንግዲህ የሚቀጥለው ሚያዝያ 17 ላይ የተቀጠረው ምንድን ነው? አንደኛ የአቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ እንዲቀርብ፤ ሁለተኛ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው የጋዜጣውን ጥሪ ሪፖርት ውጤት ለመጠባበቅ በማለት ሁለተኛ ትእዛዝ ነው። ሦስተኛው ምንድን ነው? ችሎት ውስጥ የሚረብሹ ከሆነ፤ ችሎት ውስጥ ድምፅ የሚያሰሙ ከሆነ ሌላ ብይን እንሰጣለን፤ ግን ለዛሬው የአቃቤ ሕግን አቤቱታ አልተቀበልነውም ። ስለዚህ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ችሎቱን በአካል ቀርበው እንዲከራከሩ በማለት ብይን ሰጥቷል ።»
ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሠፋ መዝገብ ስር ከተካተቱት 53 ተከሳሾች በተጨማሪ የአራቱ የምክር ቤት አባላት ተከሳሾችም ጠበቃ ናቸው ። የአቶ ክርስቲያን ታደለ፤ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ ዶ/ር ካሣ ተሻገር እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ጉዳይን በተመለከተም ከሐምሌ 28 ጀምሮ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቶ ሲከታተሉ ቆይተዋል ። ትናንት ከእስር ስለተፈቱት ደምበኛቸው ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ግን «በመታወቂያ ዋስ» ከመውጣታቸው ውጪ ዝርዝር መረጃ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
«የዶ/ር ካሣ እና የአቶ ዮሐንስ ቧያለው ያለመከሰስ መብት ቀደም ብሎ ተነስቷል ። እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባሉም አቶ ታዬ ደንደኣን ጨምሮ ማለት ነው ። ከዚያ በኋላ እንግዲህ በትናንትናው ዕለት የአቶ ክርስቲያን ታደለን የአለ መከሰስ መብት ፓርላማው አንስቷል ። በእርግጥም በፓርላማው ላይ ባይሆንም ቀጥሎ ግን ምንድን ነው ያደረገው? ከሰአት አካባቢ ያው በወረቀት ዋስ [መታወቂያ] ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ እንዲወጡ ተፈቅዷል ተብሎ ከፌዴራል ወንጀል ምርመራ ክፍል ወጥተው ወደ ቤታቸው ገብተዋል ። »
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ከእስር ስለተለቀቁበት ሒደት ለመናገር አስቸጋሪ መሆኑንም ጠበቃቸው አክለው ገልጠዋል ።
« የፍርድ ሒደት አይለም ። ፍርድ ቤት ስላልቀረቡ ስለ ፍርዱም ላወራም አልችልም ። ምክንያቱም ዋስትናም ከሆነ በዋስትና ጉዳይ ክርክር ማድረግ ነበረብን ። እነሱንም ማግኘት አልቻልንም ። በተደጋጋሚ ጊዜ ግን እንድናገናቸው ጠይቀን ነበር ። ያው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ ስለሆነ ማግኘት አትችሉም ስለተባለ፤ እነሱም ፍርድ ቤት ስላልቀረቡ የአፈታታቸው ሁኔታ የፍርድ ሒደቱ ምን ይመስላል ለሚለው አስተያየት ለመስጠት በጣም እቸገራለሁ ።»
ያለመከሰስ መብታቸው በምክር ቤት ትናንት የተነሳው ደምበናቸው አቶ ክርስቲያን ታደለን በተመለከተም ቀጣዩን ብለዋል ።
«የክልል ምክር ቤትም የአዲስ አበባ ምክር ቤትም ይሁን የፌዴራሉ ምክር ቤት ዛሬ ያቀረቡት ምክንያት ክስ እንከሳለን ነው ። ክስ እንከሳለን ከሆነ ያው ቻርጅ ይኖራል ማለት ነው ። ያ ከተደረገ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ያስከትላል ማለት ነው ።ወደ ፍርድ ቤት መቅረብን ካስከተለ ደግሞ ያው ብቻቸውን አይከራከሩም ። በጠበቃ ይከራከራሉ ። እኛም አብረናቸው ጉዳዩን እንከራከራለን ብለን ነው የምናስበው ።»
ፍርድ ቤቱ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን መዝገብ ስር ተከሳሾችን ጉዳይ ለማየት ሚያዝያ 17 ቀጠሮ መስጠቱንም ጠበቃ ሰለሞን ተናግረዋል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የሶማሌ ክልል የቀድሞው ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) እንዲሁም የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው መፈታታቸው ተዘግቧል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር