የፖለቲካ ኢኮኖሚስቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ የቤት ሥራዎች ምንድናቸው?
ረቡዕ፣ መስከረም 14 2018
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በትክክለኛው ጎዳና እየተራመደ የሚገኝ ስለመሆኑ በጽናት ከሚሞግቱ ባለሥልጣናት አንዱ እዮብ ተካልኝ ናቸው። የቀድሞ መሥሪያ ቤታቸው ገንዘብ ሚኒስቴር እና አዲሱ ቢሯቸው ብሔራዊ ባንክ ከሌሎች አምስት ተቋማት ጋር ጳጉሜ 3 ቀን 2017 ባዘጋጁት መርሐ-ግብር እንግዶች ጋብዘው ሲያወያዩ “ያለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ጊዜ እንደማነሳው የትውልድ የልማት፣ የመበለጸግ መሻት ሊሳካ እንደሚችል ያየንባቸው ዓመታት ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ ብድር እና ርዳታ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ማሻሻያ ጫና የበረታባቸው ዜጎች ባይስማሙም እዮብ ግን ቢያንስ በአደባባይ ሲናገሩ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እየተቀየረ መሆኑን ደጋግመው ያስረዳሉ።
መንግሥታቸው “በ2018 የሚጨበጥ ተስፋ እናያለን፤ በ2023 አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሣሌት፤ ከአፍሪካ አምስት ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዱ ትሆናለች፤ በ2040 ከዓለም 20 ሀገራት ውስጥ አንደኛዋ ትሆናለች” የሚል ርዕይ መሰነቁን የገለጹት እዮብ “ኢትዮጵያን የማበልጸግ ሕልማችንን እናሳካለን’ ብለን ግልጽ ራዕይ ሠንቀን ነው የተነሳንው” ሲሉ ተናግረዋል።
የእዮብ “የብልጽግና መንግሥት” ዓላማ ግን የዋጋ ግሽበት ቀፍድዶ የያዘው፤ ለዜጎቹ ሥራ መፍጠር ተስኖት የሚያነክስ እና በዓለም ገበያ ከሚሸጠው ይልቅ የሚሸምተው የላቀበትን ኢኮኖሚ መቀየር ብቻ አይደለም። እንደ ፖለቲከኝነታቸው “ያላለቀ” የሚሉትን የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ መንግሥታቸው እንደሚያጠናቅቅ ያምናሉ።
ለኢትዮጵያውያን “የጋራ ሕልም እንዲፈጠር” የሚሹት የፖለቲካ ኢኮኖሚስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መስከረም 9 ቀን 2018 በሰጡት ሹመት የብሔራዊ ባንክ 11ኛ ገዥ ሆነዋል።
ሹመታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚደግፉም ሆነ አምርረው በሚኮንኑ ባለሙያዎች ዘንድ በዐይነ-ቁራኛ የታየ ነው። የፋይናንስ ጉዳዮች ተንታኙ ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “ትክክለኛ ምርጫ አይደለም። ነገር ግን ባሉት አማራጮች የተሻለ ምርጫ ነው” የሚል እምነት አላቸው።
እዮብ እንደ ተሳናባቹ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ሁሉ የባንክ ሥራ ልምድ የላቸውም። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ግርማ ብሩ በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት የብሔራዊ ባንክ የዳሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው ሲሠሩ በመቆየታቸው ለተቋሙ እንግዳ አይደሉም።
ከአምባሳደር ግርማ በተጨማሪ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉን የሚያካትተው የዐቢይ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ብሔራዊ ባንክ በቀድሞ ገዥው ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ እየተመራ ተግባራዊ ማድረግ ለጀመራቸው ለውጦች ቅርብ ናቸው።
መንግሥት መደበኛ እና ትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያዎችን ለማዋሐድ ሲወስን የብር የመግዛት አቅም በኃይል በመዳከሙ በተለይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የከረረ ትችት ዒላማ ነበሩ። የውሳኔው ተቃዋሚዎች የቀድሞውን የብሔራዊ ባንክ ገዥ “የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጉዳይ አስፈጻሚ” ሲሉ ይተቻሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማሞ እና እዮብን ለመሳሰሉ ባለሥልጣናት “የሚጨበጥ ተስፋ” ቢያሳዩም የሀገሪቱን ዜጎች አቅም የሚፈታተኑ ዳፋዎች አስከትለዋል። እዮብ ከመንግሥት ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ መሰናበታቸውን ያሳወቁት የማሞን ወንበር የተረከቡት ብሔራዊው ባንክ በርካታ የቤት ሥራዎች እያከናወነ በሚገኝበት ኹነኛ ወቅት ነው።
“የውጪ ምንዛሪ ሥርዓቱ መሬት ይርገጥ አይርገጥ አይታወቅም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ከሐምሌ 2016 ጀምሮ የውጪ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና በፍላጎት እንዲከወን የተላለፈው ውሳኔ “ማስቀጠሉ እና መሬት እንዲረግጥ ማድረጉ የእዮብ ሥራ ነው” ሲሉ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ባንክ በ2018 የዋጋ ግሽበትን ወደ 10% የማውረድ ዕቅድ አለው። በነሐሴ 2017 ሀገር አቀፍ የዋጋ ግሽበት 13.6% ሆኖ እንደተመዘገበ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት መረጃ ያሳያል።
የውጪ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ የሚሠማሩበት ሒደት፣ በራሱ በብሔራዊ ባንክ፣ በንግድ ባንክ እና በልማት ባንክ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ ማሻሻያዎችም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አዲሱ ገዥ እዮብ ተካልኝን የሚመለከቱ ናቸው።
እዮብ ከገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት በሱዳን ጎዳና ወደሚገኘው ቢሯቸው ሲያመሩ ብር የማተም ሥልጣኑ የተገደበ ብሔራዊ ባንክ ይጠብቃቸዋል። በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት “ከዚህ በኋላ ብሔራዊ ባንክ ምንም ዐይነት ብር አያትምም” የሚሉት የፕራግማ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርዕድ ብሥራት ቢያትም እንኳ ከመንግሥት ጠቅላላ በጀት 15% መብለጥ እንደማይኖርበት መደንገጉን ያነሳሉ። በዚያ ላይ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ለሚበደረው ገንዘብ ወለድ መክፈል ይጠበቅበታል።
ገንዘብ ሚኒስቴር ከረዥም ዓመታት በኋላ ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ ሳይበደር ያጠናቀቀው የበጀት ዓመት 2017 ነበር። የማዕከላዊው ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ሲሻሻል የተቀመጠው ገደብ መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲገጥመው ብሔራዊ ባንክ ብር እንዲያትም ከማድረግ ይልቅ ሌሎች አማራጮች እንዲያፈላልግ አስገድዶታል።
የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ በሁሉም ባንኮች የሚገኙ “ወደ 500, 000 የሚጠጉ” አዲስ እና ነባር የብድር ውሎች የሚመለከት ነው። በባንክ የሥራ ዘርፍ ግልጽነትን እና የሥጋት አስተዳደርን ለማጠናከር የተዘጋጁ ባዝል አንድ እና ባዝል ሁለት የተሰኙ ዓለም አቀፍ የባንኮች ቁጥጥር ማዕቀፎች ተግባራዊ ማድረግ ሌላው የብሔራዊ ባንክ የቤት ሥራ ነው።
ማዕቀፎቹ ለተጽዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች እና ለሚፈልጓቸው ደንበኞቻቸው እንዳሻቸቸው ሲያበድሩ የቆዩ ባንኮች ላይ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ያበጃሉ። ብሔራዊው ባንክ ሁለቱን ማዕቀፎች ተግባራዊ በማድረግ የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በቅጡ እንዲወጣ ጠንካራ የባለሙያዎች ቡድን እንደሚያስፈልገው አቶ መርዕድ አስረድተዋል።
አስር የሚደርሱ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸው እስከ ሰኔ 2018 ድረስ በብሔራዊ ባንክ በታዘዙት መሠረት 5 ቢሊዮን ብር ማድረስ አይችሉም ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ መርዕድ ተናግረዋል። እዮብ የሚመሩት ማዕከላዊ ባንክ የትናንሾቹን ባንኮች ዕጣ-ፈንታ የውህደት አቅጣጫ እና ፖሊሲ በማዘጋጀት የመወሰን ሥልጣን አለው።
ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ባንክ በመጪዎቹ ወራት በኢትዮጵያ መሥራት የሚፈልጉ የውጪ ባንኮችን ማመልከቻ መርምሮ ፈቃድ መስጠት ይጠበቅበታል። እነዚህን ሥራዎች “ቴክኒካል እና የገበያ እውቀት” የሚፈልጉ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ መርዕድ የብሔራዊ ባንክ ገዥ በቋሚነት “ገበያውን የሚያናግር፣ ከገበያው ጋር engage የሚያደርግ፤ የሚያዳምጥ፣ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ የሚረዳ” ሊሆን እንደሚገባ ይናገራሉ።
እዮብ በትምህርታቸው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ናቸው። ከአሜሪካው ጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ፖሊሲ የማስተርስ ዲግሪ፤ ከሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ኢኮኖሚ ፒኤችዲ ዲግሪ አላቸው። በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ሠርተዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚኒስትር ካውንስለር ማዕረግ ያገለገሉት እዮብ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ነው። በወቅቱ የቀድሞው ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ቢሾሙም የሠሩት ግን ለጥቂት ወራት ብቻ ነው። ላለፉት ሰባት ዓመታት ገደማ አሕመድ ሽዴ በሚመሩት የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የፊሲካል ፖሊሲ እና ፐብሊክ ፋይናንስ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ነበሩ።
በሚኒስትር ዴኤታነታቸው ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ ስታደርግ የቆየችውን ድርድር ሲመሩ ቆይተዋል። የግብር ማሻሻያዎች፣ የበጀት ዝግጅት እና አመዳደብን ጨምሮ በገንዘብ ሚኒስቴር የፊስካል ፖሊሲ አተገባበር ቁልፍ ሥልጣን ነበራቸው።
ብሔራዊ ባንክ “ገለልተኛ መሆን አለበት” የሚል አቋም ያላቸው ዶክተር አብዱልመናን የሀገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ የማተም ሥልጣን በተሰጠው ማዕከላዊ ባንክ ላይ የሚፈጠር ተጽዕኖ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩትን እዮብ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አድርጎ መሾም በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን የሚና ልዩነት እንዳያጠፋ ያሰጋቸዋል።
የፊስካል ፖሊሲ በሚያስፈጽመው ገንዘብ ሚኒስቴር እና የገንዘብ ፖሊሲ ጉዳይ በሚመለከተው ብሔራዊ ባንክ መካከል “ግልጽ የሆነ ድንበር ይሰመር” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ከገንዘብ ሚኒስቴር አምጥተህ የብሔራዊ ባንክ ገዥ በምታደርግበት ሰዓት የተቀላቀለ ሁላ ነው የሚመስለው” ሲሉ ይተቻሉ።
በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጅ ብሔራዊ ባንክ “አንጻራዊ ተቋማዊ ነጻነት” አግኝቷል። የዋጋ መረጋጋትን እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓቱን መረጋጋት እና ጤናማነት ማረጋገጥ ዋንኛ ዓላማዎቹ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ተቋሙ ተዓማኒነቱን ማስረገጥ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይሞግታሉ።
በገንዘብ ፖሊሲ ረገድ “ተዓማኒነት የሚመነጨው ያልከው እና የምታደርገው ነገር የሚጣጣም ከሆነ ሰው እያመነ ይሔዳል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “የዋጋ ግሽበትን እቀንሳለሁ ብለህ ተናግረህ በተግባር በተደጋጋሚ ካልተሳካልህ ማንም አያምንም። ተግባር እና ቃልን ማገናኘት የቻለ እንደሆነ ተዓማኒነቱ ይጨምራል” ሲሉ በምሳሌ አስረድተዋል።
እዮብ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ 45 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ናቸው። በነቀምቴ የምርጫ ክልል ተወዳድረው በማሸነፍ ገዥውን ፓርቲ ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። በብሔራዊ ባንክ ገዥነታቸው የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች እዮብ እና ፓርቲያቸው በኃይል የሚፈተኑባቸው ሊሆኑ ይችላሉ።
ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን የበለጠ ሲዳከም “የፖለቲካ ጫና አለው። የወለድ መጠን በጣም ከፍ ቢል የፖለቲካ ጫና አለው። መንግሥት የሚበደርበትም ወለድ በዚያው ደረጃ ነው ከፍ የሚለው” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን አስረድተዋል። “መንግሥት ገንዘብ ቢቸግረው ወደ ብሔራዊ ባንክ ፊቱን አያዞርም ወይ?” ሲሉ የሚጠይቁት ዶክተር አብዱልመናን የአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሥራ “ቀላል አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ