1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የሆነው ኮከስ ጥሪ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ሰኔ 5 2017

ስድስት የፓለቲካ ድርጅቶችን ያሰባሰበው ኮከስ፦ «ለአገር አለመረጋጋት፣ ለእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት፣ ለፖለቲካዊ ትርምስ፣ ለኢኮኖሚታዊ ድቀትና ማኅበራዊ ቀውስ መባባስ» ምክንያት ይሆናሉ በሚል የጠቀሳቸው አካሄዶች እንዲገቱ ጥሪ አቀረበ ። መግለጫውን ያወጡት የኮከስ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ኢሕአፓ፣ ኦፌኮ ኅብር፣ ዎብን፣ ኦነግ እና መድረክ ናቸው።

የኮከስ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ከ16 አሁን ቁጥራቸው ሰባት ነው
የኮከስ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ከ16 አሁን ቁጥራቸው ሰባት ነውምስል፦ Solomon Muche/DW

ኮከስ በመግለጫው፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በያዘው አግላይ አካሄድ ቀጥሏል ብሏል

This browser does not support the audio element.

ስድስት የፓለቲካ ድርጅቶችን ያሰባሰበው ኮከስ፦ «ለአገር አለመረጋጋት፣ ለእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት፣ ለፖለቲካዊ ትርምስ፣ ለኢኮኖሚታዊ ድቀትና ማኅበራዊ ቀውስ መባባስ» ምክንያት ይሆናሉ በሚል የጠቀሳቸው አካሄዶች እንዲገቱ ጥሪ አቀረበ ። የምክክር ኮሚሽኑን አወቃቀር እና የተቋሙን የበላይ ኃላፊዎች አሰያየምና ገለልተኝነት በመቃወም የተመሰረተው ኮከስ ምክክር ኮሚሽን  የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን «የመፍትሔ ሀሳቦች ከመቀበል ይልቅ እንደተጻራሪና ተቃዋሚው በማየት በአግላይ አካሄዱ ቀጥሏል» ሲል ወቅሷል ። 

በሌላ በኩል«ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ [ቀጣዩን] ምርጫ ለማስፈጸም አንዳችም አስቻይ ሁኔታ» እንደሌለ የገለፀው ኮከሱ ገዢው ፓርቲ ከወዲሁ ዕያሳየ ነው ያለው «መንግሥታዊ መዋቅሩን የመጥቀም ፍላጎትና ዝግጅት ወደከፋ አደጋና ትርምስ እንዳንገባ በእጅጉ የሚያሳሥብና የሚያሰጋ» ነው ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን «የተሰጠውን ከፍተኛ ተግባርና ኃላፊነት በሕግ፣ በዕውቀትና እውነት፣ በነጻነትና ገለልተኝነት እንዲሁም በሚዛናዊነት ለመፈጸም ይቸገራል፣ አዋጁም ሆነ የኮሚሽኑ መቋቋም እንደገና ሊታይ ይገባል» በሚል አቋም ከጥቂት ዓመታት በፊት የተመሰረተው ኮከስ ለኮሚሽኑ ያቀረባቸው ሀሳቦች ችላ ተብለው ይልቁንም «እንደተጻራሪና ተቃዋሚ» መታየቱን ገልጿል ። በዚህ ምክንያት ኮሚሽኑ «በያዘው አግላይ አካሄድ ቀጥሏል» ሲልም ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

የኮከስ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ከ16 አሁን ቁጥራቸው ሰባት ነው

በ2015 ዓ.ም 16 የነበሩት  የኮከስ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች አሁን ቁጥራቸው ሰባት ነው ። ከእነዚህ መካከል በዚህ መግለጫ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር) ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ኮከሱ በምክክር ኮሚሽኑ ላይ የተፈጠረበትን ሥጋት አብራርተዋል።

«በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በትግራይ [ክልሎች] ያለው ነባራዊ ሁኔታም ሆነ ተጨባጭ ሁኔታ ለዚህ [ለምክክር ኮሚሽኑ ሥራ] አመቺ ሁኔታ በሌለበት አሁንም እናካሂዳለን፣ አሁንም አጀንዳ እየሰበሰብን ነው፣ አሁንም በአብዛኛው ሰብስበን ጨርሰናል የሚባለው ነገር የሚያስኬድ አለመሆኑን ለማሳየት» መግለጫ ማውጣታቸውን ገልፀዋል ።

የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሕብር) ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ኮከሱ በምክክር ኮሚሽኑ ላይ የተፈጠረበትን ሥጋት አብራርተዋልምስል፦ DW/G. Tedla

ኮከሱ ባነሳው ጉዳይ ላይ የምክክር ኮሚሽኑን ምላሽ ለማካተት ጥረት አድርገናል ። ከኃላፊዎቹ ሁለቱ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን በመግለፃቸው ለጊዜው ምላሻቸውን አላገኘንም ።  

ኮከስ ሌላው በመግለጫው ያነሳው «የምርጫ ቦርድ ወገኝተኝነትና ለገዢው ፓርቲ ታዛዠነት» ሲል የጠቀሰው ጉዳይ ነው። ቦርዱ ዛሬ ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ ሦስት አባላቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሾመውለታል። ኮከሱ ግን የቦርዱ አባላት ልምድ ላይ አስቀድሞ ጥያቄ አንስቷል ። 

«በወቅታዊው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የግጭትና ጦርነት ውጥረትና ሁለንተናዊ ውስብስብ ተጨባጭ ሁኔታ፣ አዲስ የክልሎቸ አወቃቀርና አደረጃጀት ሲታገዝ» [ቀጣዩን] ምርጫ ተከትሎ «ጣጣና መዘዝ» ይኖራል ሲልም አሳስቧል ። አቶ ግርማ በቀለ፦ «በሦስቱ ክልሎችም ምርጫ ለማስኬድ አስቻይ ሁኔታዎች የሌሉ በሆነበት ምን እየታሰበ ነው በዚህች ሀገር ውስጥ»? ሲሉ ጠይቀዋል ።

በሀገሪቱ «ሴራና ሸፍጥ እንደ ፖለቲካ ዕውቀትና ጥበብ» መያዙን የገለፀው ኮከስ ዋናው የችግሩ ምንጭም ይህ መሆኑን ጠቅሷል ።

የፀጥታ ችግር መኖሩን «አንክድም»፦ ምርጫ ቦርድ

ባለፈው ሳምንት መግለጫ የሰጡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 70 የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸውንና ከፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ ገልፀዋል ። 

የፀጥታ ችግር መኖሩን «አንክድም» ያሉት ሰብሳቢዋ የዛሬ ዓመት ለሚደረገው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ «አስቻይ ሁኔታ እንዲኖር እንፈልጋለን» ብለዋል ። ምርጫ ለማድረግ ከአንድ ወገን የሚመጣን የፀጥታ ግምገማ ብቻ እንደማይቀበሉ ሆኖም ችግር አለ ብለን ሥራችንን ትተን አንቀመጥም ማለታቸውም ይታወሳል ።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉምስል፦ Solomon Muchie/DW

"ምርጫን በፀጥታ ምክንያት ማድረግ የማንችል ከሆነ አናደርግም። ነገር ግን አስቻይ ሁኔታዎች ባሉበት ሁሉ ግን  በምርጫ ክልል ደረጃ በጥብቅ እየተከታተልን ዛሬ ቁጭ ብለን የዛሬ ዓመት ግንቦት ሰላም አይኖርም ብለን ምርጫ ቦርድ ሊቀመጥ አይችልም"።

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አካሄድ፣ ገለልተኝነት እና ሀቀኛ ተግባራትን የመፈፀምና ኃላፊነትን በአግባቡ የመወጣት ብቃት ላይ ጥያቄ ያነሳው ኮከስ ሁኔታዎች የማይስተካከሉ ከሆነ «የመጨረሻ ውጤቱ የአገር አለመረጋጋት፣ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ፣ፖለቲካዊ ትርምስ፣ ኢኮኖሚታዊ ድቀትና ማኅበራዊ ቀውስ መባባስ ነው» በማለት ሁሉም ባለድርሻዎች ከወዲሁ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አድርጓል ።

መግለጫውን ያወጡት  የኮከስ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች  የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር)፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ናቸው ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW